የታሸጉ ምግቦችና መጠጦችን አዘውትሮ በመውሰድ የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች እየጨመሩ ነው ተባለ

ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጽያ በፋብሪካ ተቀነባብረው የታሸጉና ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችና መጠጦችን አዘውትሮ በመውሰድ ምክንያት የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች እየጨመሩ መምጣታቸውን ጤና፣ ልማት እና ፀረ- ወባ ማህበር አስታወቀ።

ኢትዮጽያ በብዛት የሚገቡና በፋብሪካ ተቀነባብረው የታሸጉ፣ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችና መጠጦች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን የገለጸው ማህበሩ፤ እነዚህን ምርቶች አዘውትሮ በመውሰድ ምክንያት የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች እየጨመሩ እንደሚገኙ ገልጿል።
እነዚህ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ከፍተኛ ጨው፣ ስኳር፣ የሚረጋ ዘይትና ቅባት ይዘት ያላቸው ሃይል ሰጪ መጠጦችንና ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ ከልክ በላይ ለሆነ ውፍረት፣ ለካንሰር፣ ለልብ ሕመም፣ ለስትሮክ፣ ለዓይነት 2 የስኳር ሕመም እንደሚያጋልጥም ገልጿል።
የእነዚህ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችና መጠጦች ሰፊ አቅርቦት ወይም በገበያ ላይ እንደልብ መገኘት እንዲሁም ልቅ ማስታወቂያዎች በብዛት ተጠቂሚዎች እንዲሸምቷቸው ያደርጋልም ተብሏል።
በኢትዮጵያ ከልክ በላይ የሆነ ጨው መጠቀምን ጨምሮ ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ስርዓት ምክንያት በዓመት 32 ሺሕ 362 ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ያስታወቀው ማህበሩ፤ በዚህም ከአጠቃላይ የአገሪቱ የሞት መጠን 43 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚመጣ መሆኑን አመላክቷል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት አንድ ሰው በቀን ከአምስት ግራም ያላለፈ ጨው እንዲጠቀም የሚመክር ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ያለው የአንድ ሰው የጨው ፍጆታ ግን በቀን 8 ነጥብ 3 ግራም መሆኑም ተነግሯል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe