የቴኮም አገልግሎት ፈቃድ የጨረታ ሒደት በየካቲት ወር እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ የቴኬኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጡና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚያከናውኑ ሁለት ድርጅቶችን ወደ ገበያው ለማስገባት የጨረታ ሒደቱ በመስከረም ወር እንደሚጀመርና በጥርና የካቲት ወራት 2013 ዓ.ም. ከአሸናፊ ድርጅቶች ጋር ስምምነት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ አገልግሎ ሰጪዎች ክፍት ለማድረግና የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻን በከፊል ለመሸጥ በታቀደው መሠረት እስካሁን የተሠራውን ሥራ እንዲሁም የወደፊት ዕቅዶችን አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሰኞ ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደ የውይይት መድረክ ላይ ዕቅዶቹንና ክንውኖቹን ያስረዱት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የቴሌኮም ዘርፉን በአገልግሎት ሰጪነት የሚቀላቀሉ ድርጅቶችን ለማስገባት የጨረታ ሒደት የቴክኒክ ብቃትን ከገንዘብ አቅርቦት ጋር ባጣመረ መልኩ በመስከረም ወር ይፋ እንደሚሆን የገለጹ ሲሆን፣ ውጤቱም በጥር ወይንም የካቲት ወር ተገልጾ ከአሸናፊው ጋር ስምምነት ይደረጋል ብለዋል፡፡

ይኼ ጨረታ ክፍት ሆኖ የሚቆየው ከ40 እስከ 50 ላሉ ቀናት እንደሆነ የጠቆሙት ኦዮብ (ዶ/ር)፣ ለጨረታ የሚቀርቡ ተጫራቾች የሚያቀርቧቸውን ሰነዶች መገምገምና አሸናፎዎችን መለየት ከዚህ በኋላ የሚከናወን እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ሥራ የሚሠራ አማካሪ ቡድን እንደተቀጠረም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮ ቴሌኮም ለውድድር ዝግጁ እንዲሆን ሥራዎች መሠራታቸውን ያስታወቁት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ድርጅቱ በውስጡ ያሉት የአገልግሎትና የመሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች ሙሉ ለሙሉ ባይለዩም ተለይተው እየሠሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ከዚህ ባለፈም 40 በመቶ የሚሆነው ድርሻው ለሽያጭ ስለሚቀርብ ለዚህ ብቁ የማድረግ ተግባራትም መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ሥራ የሚሩ አማካሪ ድርጅቶች ተቀጥረው የቴሌኮም የዋገ ትመና እንደተከናወነም በመድረኩ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች መኖራቸውን ለማወቅም በወጣው የፍላጎት መግለጫ ማስታወቂያ 12 ድርጅቶች ፍላጎታቸውን መግለጻቸው የተነገረ ሲሆን፣ ለገበያ የሚቀርበው የአገልግሎት መስጫ መስመር ስፋት (ስፔክትረም) ምን ያህል እንደሆነና የዚህ ተመንም ምን ያህል እንደሆነ በሚስጥር በተለያዩ አማካሪዎች፣ የግል ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ተጠንቷል ተብሏል፡፡

በአገሪቱ ገብተው የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት ያላቸው በርካታ ድርጅቶች በመኖራቸውና የመንግሥት ሚስጥሮች እየደረሷቸው ስለነበር በርካታ ውይይቶች በሚስጥር እንዲደረጉ እንደተወሰነ ያስታወቁትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በድፍረት እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ሆነው ቢሮ ከፍተው ወራተኛ መቅጠር የጀመሩ ድርጅቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በዘለለም፣ ዘርፉ ከደኅንነት ጋር ግንኙነት ስላለውም በጥንቃቄ መከፈት ስላለበት የማይፈለጉና ያንን ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ድርጅቶች እንዳይገቡ ጥንቃቄ እየተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም 60 በመቶ በመንግሥትና በኢትዮጵያውያን እጅ እንደሚቆይና አምስት በመቶ የሚሆነው ድርሻ ደግሞ በርካታ ሰዎችን በሚያሳትፍ መልኩ ለኢትዮጵያውያን እንደሚሸጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡ ሪፖርተር

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe