የናይጄሪያ አርብቶ አደሮች ለምዕራብና ለሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት መሆናቸው ተነገረ

ፈላታ በመባል የሚታወቁ የናይጄሪያ አርብቶ አደሮች ለምዕራብና ለሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት መሆናቸው ተገለጸ፡፡ አርብቶ አደሮቹ ከጥቅምት እስከ ታኅሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የሱዳንና የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው በአማራ፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በኩል እንደሚገቡ፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰርና በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት አቶ ገናናው አግተው ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

በ1962 ዓ.ም. በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር መታየታቸውን የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፣ የክረምቱን መውጣት ተከትለው አገር ውስጥ እንደሚገቡና በጋውን በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እንደሚያሳልፉ ያስረዳሉ፡፡

በሕገወጥ መሣሪያ ዝውውር ዓይነተኛ ተዋናይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የፈላታ አርብቶ አደሮች፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኙ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ማሳዎችንም እያጠፉ ነው ተብሏል፡፡

በክልሉ መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ውስጥ በ4,000 ሔክታር መሬት ላይ ጥጥ፣ ሰሊጥና ማሽላ የሚያለሙት አቶ ወርቅነህ ህሩይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተያዘው ዓመት ብቻ ሁለት ጊዜ ገብተው በአካባቢው የሚገኙ ማሳዎችን አውድመዋል፡፡ የደረሰ ማሽላ ከየማሳው መብላታቸውን፣ ለመለቀም የደረሰ ጥጥ ረጋግጠው ማበላሸታቸውን፣ በተጨማሪም በየማሳው የሚሠሩ ሠራተኞች ላይ ተኩስ ከፍተው ጉዳት ማድረሳቸውን፣ በቅርቡም በእሳቸው ማሳ ላይ የሚሠራ አንድ ሰው በቀስት ተመቶ ለከፋ ጉዳት መዳረጉን ገልጸዋል፡፡

‹‹በእኛ ላይ ትልቅ ጉዳት እያደረሱ ነው፤›› የሚሉት አቶ ወርቅነህ፣ አንዳንድ ጊዜ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ከብቶች እየነዱ እንደሚገቡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በኮቴያቸውና በከብቶቻቸው ፍግም አደገኛ አረሞችን ወደ እርሻ ማሳዎች እንደሚያዘምቱ አስረድተዋል፡፡

በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎችም በተመሳሳይ የፀጥታ ሥጋት የሆኑት ፈላታዎች ዲንደር የሚባለውን የሱዳን ብሔራዊ ፓርክ አቋርጠው ከላይ ነፍስ ገበያ በሚባል፣ እንዲሁም ከታች ደግሞ ኦሜድላ በተባለ ሥፍራ አድርገው ወደ አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ እንደሚገቡ ይነገራል፡፡ ከዲንደር ፓርክ 74.5 ኪሎ ሜትር የጋራ ድንበር ያለው የአልጣሽ ፓርክ 2,665 ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሚሰፋ የሚናገሩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ገናናው፣ ፈላታዎች ለአገሪቱ ትልቅ የፀጥታ ሥጋት መሆናቸውን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ መጨመሩን ይናገራሉ፡፡

በአንድ ጊዜ 2,000 የሚሆኑ ሰዎች ከ500 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ከብቶችን እየነዱ ድንበር ሲያቋርጡ፣ የነዋሪዎችን የግጦሽ ሥፍራ ከመጋፋት ባለፈ ከፍተኛ ግጭት ይፈጥራሉ ተብሏል፡፡ ከ1991 ዓ.ም. ወዲህ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ብቻ 61 ኢትዮጵያዊያን በግጭቱ ሕይወታቸው ማለፉን፣ በፈላታዎች ወገን ደግሞ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውን ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፡፡ አልፎ አልፎ በሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱም ተመልክቷል፡፡

በጋውን በአልጣሽ ፓርክ ውስጥ ለማሳለፍ ወደ ፓርኩ ሲገቡ የፀጥታ አካላት እንዳያገኙዋቸው ዱካቸውን ማጥፋታቸው፣ ለፓርኩ ትልቅ አደጋ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ሰዎች ዱካቸውን ተከትለው እንዳይደርሱባቸው ሲሉ በፓርኩ ውስጥ እሳት በመልቀቅ የፓርኩን ተፈጥሮአዊ ሀብት እያጋዩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፓርኩ ከ500 እስከ 900 ሜትር ከባህር ጠለል ከፍ ብሎ የሚገኝ፣ ሙቀታማና በእሳት ለመጥፋት ጊዜ የማይፈጅበት ጥቅጥቅ ደን ያለበት መሆኑንም አክለዋል፡፡

ፈላታዎች ሳርና ቁጥቋጦዎችን በእሳት ካጠፉ በኋላ ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ ሆነው የሚቆዩ ዛፎችን እየጨፈጨፉ ለከብቶቻቸው እንደሚመግቡ ገልጸዋል፡፡ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ እንደ ድኩላ፣ አጋዘን፣ ሚዳቋና ፌቆ የመሳሰሉ የዱር እንስሳትን አድነው እንደሚበሉ፣ አንበሶችን እንደሚገድሉ፣ ዝሆኖችን ገድለው ጥርሳቸውን እንደሚሸጡም አስረድተዋል፡፡

ወቅቱን ጠብቀው የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ጥፋት የሚያስከትሉት የናይጄሪያ ከብት አርቢዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ የፀጥታ ሥጋት የሆኑት፣ ሱዳን ጠበቅ ያለ ሕግ ካወጣች በኋላ እንደሆነ አቶ ገናናው ጠቁመዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ፈላታዎች በሱዳን መሬት ከብቶቻቸውን ሲያስግጡ ከተገኙ ገንዘብ እንዲከፍሉ የሚደነግግ ሕግ ሱዳን አውጥታለች፡፡ ዲንደር ፓርክ ውስጥ ከተገኙ ደግሞ ካሉዋቸው ከብቶች ግማሾቹ ስለሚወረሱባቸው፣ በጋውን አልጣሽ ፓርክ አሳልፈው ክረምቱን በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ በምትገኝና በአመዛኙ የኢትዮጵያ በሆነችው አቡኒ የምትባል ሥፍራ ቆይተው በጥቅምት ወር ስለሚመለሱ ይህም ዋነኛው የፀጥታ ችግር ነው ተብሏል፡፡

‹‹አቡኒ ውስጥ በቋሚነት እየኖሩ ነው፤›› የሚሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፣ ፈላታዎች በጎሳ መሪዎች እንደሚተዳደሩ ይናገራሉ፡፡ መሪዎቻቸውን ገታ ብለው የሚጠሩ መሆናቸውን፣ ስምንት የታወቁ መሪዎችን መርጠው እንደሚተዳደሩ፣ አደም ገታ፣ ቡባ ገታና በሽር ገታ ከታዋቂዎቹ መሪዎቻቸው መካከል መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ከአሥር ወራት በላይ እንደሚቆዩ የሚናገሩት የመተከሉ አልሚ አቶ ወርቅነህ፣ ፈላታዎች ወደመጡበት የሚመለሱት ክረምት ሲገባ ወይም ከብቶቻቸውን የሚናከስ ነፍሳት ሲዛመት ነው ይላሉ፡፡ ሰፋፊ እርሻዎችን ከማውደም ባለፈ ለነዋሪዎችም የሥጋት ምንጭ ናቸውና አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe