”የንባብ ባህል አለን ለማለት እቸገራለሁ”

ታምራት ኃይሉ የቁምነገር መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሲሆን፤ በህትመት ሚዲያው ዘርፍ ላለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት መጽሔት ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ም/ቤት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ በመሆን እየሠራም ይገኛል፡፡ አሁን ደግሞ በዲጅታል ሚዲያ አማካኝነት በዌብሳይት የጽሑፍ ሥራዎችን ይሠራል፡፡
‹‹ንባብ ለጋዜጠኛ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው›› የሚለው ታምራት፤ ‹‹አንባቢ ነኝ ብዬ ባልኩራራም፣ ከንባብ የተነጠለ ሕይወት አለኝ ለማለት አልችልም›› ይላል፡፡ በተቻለ መጠን ለሥራው አጋዥ የሆኑ የተለያዩ መጻሕፍትን እንደሚያነብ ይገልፃል፡፡
‹‹በታሪካችን የንባብ ባህል አለን ለማለት እቸገራለሁ›› የሚል ጠንከር ያለ አስተያየት የሚሰጠው ታምራት፤ የደራስያን ሥራዎች ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች በሚፈለገው መጠን ተነበዋል የሚል እምነት እንደሌለው ይናገራል፡፡ አያይዞም፤ ‹‹ መጻሕፍት፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች የሚሸጡበት ቅጅ ብዛት ሲታይ ያሳዝናል›› ይላል፡፡
‹‹በመሆኑም የንባብ ባህልን ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወን አለባቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ መንግሥት በወረቀት ዋጋ ላይ የጣለውን ታክስ ማንሳት ይኖርበታል›› የሚል አስተያየት አለው፡፡ ኅብረተሰቡ በአነስተኛ ዋጋ የኅትመት ውጤቶችን የሚያገኝበት መንገድ ቢመቻች ብሎ እንደሚያስብ ገልፆልናል፡፡
‹‹ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ ቤተ መጻሕፍትን ሲገነባ እንመለከታለን፡፡ ቤተ መጻሕፍቱ የሚገነባበትን 1/10 ኛውን በጀት ለደራስያን መጻሕፍት ማሳተሚያ ተዘዋዋሪ ፈንድ ቢመደብ፣ ምናልባት ከዚህ በኋላ መጻሕፍት ቤቶቹ አዳዲስ መጻሕፍትን፣ አዳዲስ ታሪኮችን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ መጻሕፍት ቤቶቹ የድሮ መጻሕፍት ብቻ ይዘው ይቆያሉ ብዬ አስባለሁ፡፡›› ይላል፡፡
‹‹አብዛኛውን ጊዜ የምከታተለው የዘመኔን ጀግና ደራስያን ሥራዎችን ነው፡፡ ከነዚህ ባሻገር ወደ ኋላ መለስ ብዬ የቀደምት ደራስያን ሥራዎችንም አደንቃለሁ፡፡ ከማደንቃቸው የዘመናችን ደራስያን ሥራዎች መካከል የተወሰኑትን ምርጫዬ አድርጌአቸዋለሁ፤ ያላነበባችሁ እንድታነቡዋቸው እጋብዛለሁ››
1 አጥቢያ – ዓለማየሁ ጋላጋይ
2 ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር – ታገል ሰይፉ
3 ባርቾ – ሕይወት እምሻው
4 ከአሜን ባሻገር- በዕውቀቱ ስዩም
5 ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ- ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ
******
ከዝግጅት ክፍሉ፡- FM 97.1 Addis ”ለተሻለ ነገ እናንብ” በሚል ልዩና ረዥም የንባብ ዘመቻ, ከየካቲት 17 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በማካሄድ ላይ ሲሆን፤ በቂ የንባብ ልምድ ያላቸው የኢትዮጵያ ልሂቃንን ተሞክሮ በተከታታይ በማጋራት ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ ደግሞ የተዳከመውን የንባብ ልምድና ስሜት በመቀስቀስና በማነቃቃት ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም ተግባሩ ጣቢያው አድናቆትና ምስጋና ይገባዋል፡፡ እኛም ከላይ የቀረቡትን የንባብ ተሞክሮዎች መጠነኛ አርትኦት አድርገንበት ማውጣታችንን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe