የአልበሽር ፀሐይ እየጠለቀች ይኾን?

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከሰሞኑ የተነሳባቸው ሕዝባዊ ተቃውሞ መጨረሻው ምን እንደሚሆን ለመገመት ቢያስቸግርም ኹኔታዎች ግን ሰውየው ላይ እየከበዱ እንደሚሔዱ የሚጠቁም ነው፡፡ ለሠላሳ ዓመት በስልጣን ላይ የቆዩት አልበሽር በሰሞኑ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች የ‹ይውረዱልን› ጥሪ ቀርቦባቸዋል፡፡

የተቃውሞ ታሪክ በሱዳን

የዘንድሮውን ተቃውሞ የቀሰቀሰው የዳቦ እና የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ኹኔታ መጨመሩ ይሁን እንጂ ሱዳን ለእንዲህ ዓይነት ተቃውሞዎች አዲስ አይደለችም፡፡ እ.ኤ.አ በ1964 በካርቱም ዩኒቨርሲቲ በሚማሩ ተማሪዎችና በፖሊሶች መካከል በተካሔደ ግጭት የጀመረው አለመረጋጋት የወቅቱን ወታደራዊ መሪ ኢብራሒም አቡድ ከስልጣን ለማውረድ የደረሰ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ በ1985 የተነሳው ተቃውሞ ደግሞ በመሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ የዋጋ መጨመርን ተከትሎ የመጣ ነበር፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ የወቅቱን መንግሥት መሪ ጃፋር ኒሜሪ ከስልጣን ለማውረድ ያስገደደ ነበር፡፡ ‹በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ያለፈችው ሱዳን የዘንድሮውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በምን ዓይነት ምዕራፍ ትቋጨው ይሆን?› የሚለው ጥያቄ የተለያዩ መላምቶች እያሠጠ ይገኛል፡፡

የ1964ቱ ተቃውሞ የተነሳባቸው ኢብራሒም አቡድ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ የአምስት ቀናት የተቃውሞ ሰልፍ ብቻ በቂያቸው ነበር፡፡ በፕሬዚዳንት ኒሜሪ ላይ የተነሳው የ1985ቱ ተቃውሞ ደግሞ የፕሬዚዳንቱ ሞኛሞኝነት ተጨምሮበት ከስልጣን እንዲነሱ ዳርጓቸዋል፡፡ ገና በተቃውሞው መነሻ ቀናት ወደ አሜሪካ መጓዛቸው የጠነከረ የ11 ቀናት ተቃውሞ እንዲጠብቃቸውና ከስልጣን እንዲነሱ ምክንያት ኾኗቸዋል፡፡ የአሁኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር ከቀድሞዎቹ መሪዎች ጋር ሲነፃፀሩ ከ18 በላይ ቀናት በቆየ ተቃውሞ ውስጥ እንኳን ፅኑ ሆነው መቆየት የቻሉ ናቸው፡፡ ከስልጣን ቢወርዱ በዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የተቆረጠባቸው የእስር ማዘዣ ተግባራዊ እንደሚሆን በመፍራታቸው ነው ስልጣናቸውን የሙጥኝ ብለው መኖር የመረጡት፡፡

የ1964ቱ እና የ1985ቱ ተቃውሞዎች የሱዳንን ሰሜናዊ ክፍል ባጥለቀለቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረትና ታላላቅ ማኅበራት የታገዙ ነበሩ፡፡ ታጣቂ የአመፅ ቡድኖችም በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ተዛምተው ነበር፡፡ በቀደሙት ኹለት ተቃውሞዎች የወታደራዊው ጦር ጣልቃ ገብነት ዴሞክራሲያዊት ሱዳንን ለመፍጠር በሚል ለወቅቱ መንግሥታት መውደቅ የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ የአልበሽር ዘመኑ ወታደራዊ ጦር ግን ለሱዳን ፖሊስ የሚያገለግል በመሆኑና በሠራቸው ጥፋቶች ምክንያት አልበሽር ከወረዱ እርሱም በጦር ወንጀለኝነት የሚጠየቅ በመሆኑ ዝምታን መርጦ የዘንድሮው ተቃውሞ እንዲራዘም የድርሻውን አበርክቷል፡፡ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ የማይናቅ ሚና ያላቸው እስላማውያንም በፓርቲዎቻቸው በኩል ከዚህ ቀደም በነበራቸው ጥንካሬ ፖለቲካው ላይ አለመሳተፋቸው የአልበሽር መንግሥት ላይ የተነሳው ተቃውሞ በአጭር እንዳይቀጭ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ኾኗል፡፡

የዘንድሮው መራር ተቃውሞ

ሕዝባዊ ተቃውሞው ከተቀሰቀሰበት ቀን ጀምሮ 816 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ አህመድ ቢላል ዑስማን ተናግረዋል፡፡ 118 ህንፃዎች የፈራረሱ ሲሆን ከእነኚህ መካከል አሥራ ስምንቱ የፖሊስ ናቸው፤ 15 የዓለማቀፍ ተቋማት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮም በአጠቃላይ 194 ተሽከርካሪዎች የእሳት ሲሳይ ተደርገዋል፡፡ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ላለፈው አንድ ዓመት በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ በቆየችው ሱዳን የምግብና መድኃኒት ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ የአሁኑን ተቃውሞ የቀሰቀሰው የዳቦ ዋጋ መናር ሲሆን የአንዲት ዳቦ ዋጋ ከአንድ የሱዳን ፓውንድ ወደ ሦስት ፓውንድ ማሻቀቡ ነው፡፡ የመንግሥት አካላት በተቃውሞው የሞቱት ዜጎች ቁጥር 19 ብቻ መኾናቸውን ሲገልጹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም በበኩሉ የሟቾች ቁጥር 39 መድረሱን አስታውቋል፡፡

የአልበሽርን መነሳት የሚሹት ተቃዋሚዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያደረጓቸውን ሰልፎች ተከትሎ የመንግሥት ደጋፊዎችም አደባባይ ወጥተው ‹በሽር ስልጣን ላይ እንዲቆይ እንፈልጋለን› ብለዋል፡፡ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር ሲልም መንግሥት የተቃውሞ ፖለቲካ አመራሮችን፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶችን ማሠሩ ነው የተነገረው፡፡ በርካቶች በማኅበራዊ ድረገጽ የተቀባበሉት የተቃውሞ ሰልፍ ቪዲዮም ‹‹ነፃነት!፣ ሠላም!፣ ፍትሕ!›› እና ‹‹አብዮት በሕዝብ ምርጫ የምትካሔድ ናት!›› የሚሉ መልዕክቶች የተላለፉበት ነበር፡፡ ሰልፈኞች በፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ የተተኮሰባቸው መሆኑም ተነግሯል፡፡ ብሪታንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና ኖርዌይ በጋራ ባወጡት መግለጫ የሱዳን መንግሥት በሚነሳበት ተቃውሞ ላይ የሚወስዳቸው የኃይል እርምጃዎች ያሳሰባቸው መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በሞቱት ዜጎች ጉዳይ ላይ ምርመራ እንዲካሔድ ጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ምርመራ የሚያካሒድ ኮሚቴ እንደሚቋቋም አሳውቀዋል፡፡

አልበሽር – ከትናንት እስከ ዛሬ

ለሀገሪቱ መንግሥት ቅርብ ናቸው የሚባሉ 22 የፖለቲካ ቡድኖች አል በሽር ስልጣን እንዲለቁ ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም ፕሬዚዳንት አልበሽር ግን መንግሥታቸው የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመቅረፍ እየሠራ መኾኑን መናገር ብቻ ነው የመረጡት፡፡ እ.ኤ.አ በ1989 በኢስላማውያን በተደገፈ የመንግሥት ግልበጣ ስልጣን የያዙት የቀድሞ ጄኔራሉ አል በሽር በቅርቡ ከወታደሮች ጋር ባደረጉት ንግግር ‹‹ጦሩ ሀገሪቱንና ስኬቷን እንጂ ከሐዲዎችን እንደማይደግፍ ስለምናውቅ ምንም ችግር አይገጥመንም›› ብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1944 በግብርና ይተዳደሩ ከነበሩ ወላጆች የተገኙት አልበሽር በግብጽና በካርቱም ወታደራዊ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1989 በጠቅላይ ሚኒስትር ሳዲቅ አል – ማህዲ ላይ የተካሔደውን መፈንቅለ መንግሥት በስኬታማነት ከመሩ በኋላ ‹ሪቮሉሽናሪ ኮማንድ ሴንተር ፎር ናሽናል ሳልቬሽን› የተባለውን የወቅቱን የሽግግር መንግስት በሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡ እስላማዊ ሕግ የኾነውን ሸሪአ ተቋማዊ ካደረጉና እ.ኤ.አ በ1990 ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ካጠፉ በኋላ በ1993 ጊዜያዊውን መንግሥት በማጥፋት ራሳቸውን የሱዳን ፕሬዚዳንት በማድረግ ሾመዋል፡፡ ላለፉት 30 ዓመታትም የማጭበርበር ተቃውሞ በሚነሳባቸው ሦስት ምርጫዎች እያሸነፉ እዚኽ ደርሠዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በኋላ ሀገሪቱ ባካሔደችው ፕሬዚዳንታዊና ፓርላማዊ ምርጫ 75 በመቶ ድምጽ በማግኘት ካለተቀናቃኝ የስልጣን መንበራቸውን አደላደሉ፡፡ በ2000 ደግሞ በተቃዋሚዎች ተቀባይነት ባላገኘ ምርጫ 90 በመቶ በማግኘት ማሸነፋቸው ተነገረ፡፡ እ.ኤ.አ በ2003 በዳርፉር የሚገኙ የተለያዩ ብሔሮች የሀገሪቱ መንግሥት ጥቁር አፍሪካውያን ላይ ያደላል በማለት በመንግሥትና ‹ጃንጃዊድ› በሚባሉት በመንግሥት የሚደገፉ የአረብ ታጣቂዎች ላይ ያነሱትን አመፅ ለማስቆም በወሰደችው እርምጃ ሱዳን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዘር ጭፍጨፋ ፈፅማለች በሚል ክስ እ.ኤ.አ በ2009 ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሠን አልበሽር ላይ በዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸዋል፡፡ በዚህም ስልጣን ላይ እያሉ በፍርድ ቤቱ የተከሰሱ የመጀመርያ ሰው ኾነዋል፡፡ በዘር ጭፍጨፋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ200 እስከ 400 ሺህ እንደሚደርስ የተለያዩ ምንጮች ቢጠቁሙም ‹የዘር – ጭፍጨፋ› በሚለው ቃል የማይስማማው የሀገሪቱ መንግሥት በበኩሉ የሟቾች ቁጥር 10 ሺህ መሆኑን ነው የሚያምነው፡፡ ማዘዣው ከወጣባቸው ከ19 ቀናት በኋላ ወደ ኤርትራ የተጓዙት አል በሽር ከዚያ በኋላም በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ፣ ሊቢያ፣ ኳታር እና ግብፅ ሔደዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምዕራባውያን ኃይሎች የሚዘወር ‹አሻንጉሊት› ነው የሚሉት አልበሽር የድርጅቱን የእርዳታ ተቋማትም ከሀገራቸው አስወጥተዋል፡፡ ዓለማቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአልበሽር ላይ ለኹለተኛ ጊዜ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱም ይታወሳል፡፡

እጣ ፈንታቸው ምን ይሆን?

ላለፉት 30 ዓመታት ጎረቤት ሀገር ሱዳንን እየመሩ የቆዩት የ75 ዓመቱ ኦማር ሀሠን አልበሽር ባለፉት ሳምንታት በሀገራቸው ዜጎች የገጠማቸው ተቃውሞ መጨረሻው ምን እንደሚሆን አልለየለትም፡፡ ሕዝባዊ አመፁ በወታደራዊ ኃይሉ ታግዞ እርሳቸው በመጡበት የመንግሥት ግልበጣ መንገድ በኃይል ከስልጣን ይወርዱ ይኾን? ሕዝባዊ ተቃውሞው ጎልብቶ በፈቃደኝነት ከስልጣን እንዲወርዱ ያስገድዳቸው ይኾን? ወይስ ተቃውሞው በኃይል ተቀጭቶ ጨለማ ያጠላበት የአልበሽር ተስፋ መልሶ ያንሠራራል?

መጪው ጊዜ የእነኚህን ሁሉ ጥያቄዎች መልስ ይዟል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe