የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ሠራተኞቹ በሥራ ቦታ በዋትስአፕ እንዳይጠቀሙ እግድ ጥሏል።
ምክር ቤቱ በዋትስአፕ መልዕክቶችን መለዋወጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም በማለት መተግበሪያውን ከማንኛውም የመንግሥት ኮምፒውተሮች፣ ላፕቶፕ እና ስልካቸው ላይ እንዲሰርዙ እና ከቢሮ ውጭም ቢሆን ዋትስአፕን እንዳይጠቀሙ ለሠራተኞቹ መመሪያ ሰጥቷል።
መንግሥታዊ ምሥጢሮች እና የሥራ መረጃዎች በሰርጎገብ የመረጃ ጠላፊዎች እጅ እንዳይገባ ለመከላከል የምክር ቤቱ ሠራተኞች መተግበሪያውን ከስልኮቻቸው እንዲሰርዙ አዝዟል።
በዋትስአፕ ምትክም እንደ ‘ሲግናል’ እና ‘ማይክሮሶፍት ቲምስ’፣ ‘ቻት ጂፒቲ ፕላስ’፣ ‘ዊከር አይ ሜሴጅ’ እና ‘ፌስ ታይም’ የተባሉ የመልዕክት መላላኪያ እና የተግባቦት መተግበሪያዎችን እንዲጠቀሙ ምክረ ሐሳብ አስቀምጧል።
ይህንን ውሳኔ ተከትሎም የዋትስአፕ መተግበሪያን በባለቤትነት የሚቆጣጠረው የሜታ ኩባንያ ቃል አቀባይ፣ ኩባንያው በምክር ቤቱ ውሳኔ እንደማይስማማ ገልጸዋል።
ዋትስአፕ ምክርቤቱ አስተማማኝ ናቸው ካላቸው ሌሎች መተገበሪያዎች የተሻለ የደኅንነት ዋስትና ይሰጣል ነው ያሉት።
በመሆኑም ምክር ቤቱ ይህንን ሁኔታ ከግምት በማስገባት በዋትስአፕ ላይ የጣለውን እገዳ እንደሚያነሣ ተስፋ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

