ዴሞክራቶች የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ዶናልድ ትራምፕን ከስልጣን እንዲያነሷቸው ግፊት እያደረጉ ነው።
በተለይ የአሜሪካ ኮንግረስ አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በካፒቶል ሂል ከነበረው ሁከት ጋር በተያያዘ በነበራቸው ሚና ከነጩ ቤተ መንግስት የስልጣን ጊዜያቸው ሳያበቃ እንዲነሱ በምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ላይ ጫና እያደረጉ ነው ተብሏል።
ህግ አውጪዎችም በ25ኛው የአሜሪካ የህገ መንግስት ማሻሻያ መሰረት ፕሬዚዳንቱ ለቢሮው ባለመመጠናቸው ከስልጣን እንዲነሱ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ሀሳብ አዘጋጅተዋል።
ሆኖም ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ይህን ውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው እየተነገረ የሚገኘው።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ሀሳቡን ውደቅ ካደረጉ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎቻቸውን ወደ ካፒቶል ሂል እንዲያመሩ በመቀስቀሳቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው የአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ድምፅ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሪፐብሊካኑ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዴሞክራቶችና ቁጥራቸው እያደገ በመጣ የሪፐብሊካን አባላት ሁከትን በመቀስቀስ ክስ እየቀረበባቸው ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት በካፒቶል ሂል በነበረው ሁከት ምክንያት የፖሊስ አባልን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ዶናልድ ትራምፕ በካፒቶል ሂል በነበረው ሁከት ትዊተርን ጨምሮ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ከታገዱበት ጊዜ ጀምሮ ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም ተብሏል።