የአንጋፋው ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ የቀብር ስነስርዓት በየካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል

የአንጋፋው ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ የቀብር ስነስርዓት ዛሬ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:30 ሰዓት በየካ ሚካኤልን ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል::(የሠዓሊ ጥበብ ተርፋ አጭር የሕይወት ታሪክ)
ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ ከአባታቸው አቶ ተርፋ ማመጫ እና ከእናታቸው ወ/ሮ አበበች ተፈራ በ1941 ዓ.ም. በሐረር ከተማ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እና በሐረር መድኃኔአለም ተምረዋል፡፡
በ1961 ዓ.ም. በቀድሞው አዲስ አበባ ሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት በአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በመግባት በ1965 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ በተማሪነት ዘመናቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ያቁዋቁዋሙትን የአስራ ስድስቱ ሠዓልያን ማሕበርን ለሦስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት መርተዋል፡፡
ከ1965 እስከ 1973 ዓ.ም. በሐረር መድኃኔአለም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በሥዕል መምህርነት አገልግለዋል፡፡
ከ1973 እስከ 1976 ዓ.ም. ድረስም በኩራዝ አሳታሚዎች ድርጅት በመጽሐፍ ሽፋን ሠዓሊነትና ኢሉስትሬተርነት ሰርተዋል፡፡
ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ ከ1961 እስከ 2016 ዓ.ም. 35 የግል፤ 26 የቡድን በድምሩም 61 ኤግዚቢሽኖችን በሃገር ውስጥ እንዲሁም በካናዳ፣ ዩኤስ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ስፔይን፣ ስዊዘርላንድ ከማሳየት በተጨማሪም በርካታ ሬሲደንሲ እድሎችና እና ሽልማቶችን ተቀብለዋል፡፡
ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብን መልክ ካስያዙ ቀደምት ሠዓልያን በመቀጠል ሥነ-ጥበባዊ ነጻነትን በልምምድ በማዳበርና በመተግበር አሻራቸውን ካሳረፉ የሃገራችን እውቅና ታታሪ ከሆኑ ግንባር ቀደም ሠዓልያን መካከል አንዱ ናቸው፡፡
በዘመናቸው ከነበሩ ጸሐፍት፣ ኃያስያንና ምሁራን ጋርም ስለ የኢትዮጵያ ዘመናዊነትና ዘመናዊ ሥነ-ጥበብ ሰፊ ንባብና ውይይት በማድረግ ጉልህ አበርክቶት ነበራቸው፡፡
ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ ለተፈጥሮ በተለይም ዕጽዋትን ለመንከባከብ፣ ለፍልስፍና፣ ለንባብና ለሥነ-ጥበብ ጥልቅ ፍቅር፣ ትጋትና አክብሮት ነበራቸው፡፡ በጨዋታ አዋቂነታቸውና እውቀታቸውን በማካፈል በነበራቸው ቀናዒነት በብዙ ወዳጅ ዘመድና ወጣቶች ተወዳጅ ነበሩ፡፡
ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ የሁለት ልጆችና የሁለት ልጅ ልጀች አያትም ነበሩ፡፡
ሠዓሊ ጥበብ ተርፋ በተወለዱ በ76 አመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም በመጋቢት 23 በድንገት አርፏል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe