የአንጋፋው ድምፃዊ ክራርና በገና ደርዳሪ አለማየሁ ፋንታ በህክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 1/ 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፥ ስርዓተ ቀብራቸው በገነተ ፅጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ከቀኑ 9 ሰዓት ተፈፀማል።
ጋሽ አለማየሁ ፋንታ ድምፃዊ፣ የግጥምና ዜማ ደራሲ፣ መሰንቆና ዋሽንት ተጫዋች፣ ክራርና በገና ደርዳሪ፣ የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ መምህርም ነበሩ፡፡
ትውልድ እድገታቸው ዋግኸምራ ሰቆጣ የሆነው አንጋፋው ሙዚቀኛ የኢትዮጵያን የባህል ሙዚቃ በመወከል በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በኢስያ ተዟዙረዋል።
በእንግሊዝ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያና በሌሎች የአውሮፓ ሃገራትም ተዟዙረው ሙዚቃችንን ለማስተዋወቅ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የባህል ሙዚቃው አምባሳደርም ተሰኝተዋል።
በዲቁናም ለ5 አመታት ያገለገሉት አንጋፋው በማንጎራጎር ምርጫዬ ዲቁናዬን አፈረስኩት ብለው እንደሚፀፀቱ ለሸገር ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ ጭምር እንዲህ አንስተውታል፡፡
= “እቱ ባንቺ ነገር – ባንቺ የተነሳ
ድቁናዬም ቀረ – ዳዊቱም ተረሳ፡፡
እቱ ዲቁናዬ – ዳዊቴ አንቺ ነሽ
ብደግም ብደግም የማልሰለችሽ”።
ጋሽ አለማየሁ ፋንታ በፔንታቶኒክ ስኬል የተመሰረተ ሙዚቃን ሲያብራሩ የእውቀት ጥልቀት ርቀታቸው ይገርመኛል፡፡
በማሲንቆ በእንግሊዝኛ ቃና ሙዚቃውን በዚሁ ስኬል እየተጫወቱ ሲያብራሩት መስማት የሙዚቃ ትምህርት ቤት የመገኘት ያህል ይሰማኝ ነበር ሳደምጣቸው፡፡
“ቅኝት ማለት መሰረተ ድምፅ ነው” እያሉ መምህርነታቸው ያይላል መሰለኝ ትዝታ፣ ባቲ፣ አምባሰል እና አንቺ ሆዬ እያሉ ልዩነታቸውን እያዜሙ በጣዕም ሲያብራሩ የሚገርም ነው፡፡
ለምሳሌ “አበብ አበባዬ _ መስከረም ጠባዬ” የሚለው የእንቁጣጣሽ ዘፈን በአንቺ ሆዬ መሰረተ – ድምፅ ፈርጅ ውስጥ እንደሚወድቅ በእውቀት ዘና ብለው ሲያብራሩ እንደመስማት ሀሴት ውስጥ የሚከት የለም፡፡
የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ በተለያየ የዓለም ማዕዘን ዞረዋል፤ ብዙ ባይታወቁበትም ከትያትር እና ፊልም ዘርፉም አልቦዘኑም፡፡
ሙዚቃን የጀመሩት በሀገር ፍቅር ቴአትር ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 አመታት ሰርተዋል፡፡ ከዚያ በፊት ከውዳሴ ማርያም እስከ ዜማው ድረስ፤ አንቀፀ ብርሃንን፣ መልክዐ ማርያምና መልክዐ ኢየሱስን፣ መስተጋበ ክስተተ አርአያምን፣ ዝማሬ መዋሲትን እስከ ጾመ ድጓ ድረስ የቤ/ክርስቲያን ትምህርትን ተከታትለዋል፡፡
የኪነ ጥበቡ ሰው ከሽሽግ ቸኮልም ጋር ተጫውተዋል ቴአትር – “ነቤው ና ነቤው ና!” እያሉ ባለውቃቢ ገጸ ባህሪን ወክለው በሀገር ፍቅር ቆይታቸው ተጫውተዋል፡፡
መዲና እና ዘለሰኛውን ዜማ በቅጡ አውቆ ለይቶ የሚያዜም እና ያስተማረ፤ ሁለቱም ከግጥም አንስቶ እስከ ዜማቸው ይለያያሉ ይሉናል – ጋሽ አለማየሁ፡፡
= “ይንገር አይንገር ምን አውቃለሁ
መላኩንስ ልኬዋለሁ”። = ይህ መዲና ግጥም ነው፤ ስንት ሀረጎች እና ስንኝ እንዳለውም በቀላሉ ይታወቃል፡፡
= “እኔስ ፍረድ ቢሉኝ አምላክ ተሳስቷል
ሞት በደለኛ ነው አንድ ሰው ለምስል ቆሞ ቢቀር ምነው” = ይህ ደግሞ ዘለሰኛ ግጥም ነው፡፡
= “አዳራሹ ሰፊ በሩ አልጠበባችሁ
በተራበ ተራ ምነው መግባታችሁ” = እንግዲህ ይሄም የግጥም አገጣጠም የዘለሰኛ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ እያሉ ማብራሪያቸውንጽሲቀጥሉ፡-
= “ስማኝ ልንገርህ አትስነፍ
ተው እየሰራህ እለፍ”። = ይህ ደግሞ መዲና ነው፡፡
እንዲህም አሉ ነፍስኄር ጋሽ ፋንታ _ የግጥሙ ምጣኔ ዜማውን ይወስነዋል፤ ይህም ዜማው እንዳይሰበር ያደርገዋል፡፡
ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከማስተማርም በትይዩ፥ የባህል ሙዚቃን በስርአተ ትምህርት እንዲመራ Curriculum በመቅረጽ ጉልህ ሚና ነበራቸው።
ጋሽ አለማየሁ በ1968 ዓ.ም ከዳካር የኔግሮ አርትስ ፌስቲቫል ሽልማት ከዩኔስኮ ለሙዚቃ ስራዎቻቸው እውቅና (Recognition by UNESCO an Analogy of African music) እንደሰጣቸው ይታወሳል፡፡
ከኮሪያ ስፕሪንግ ፍሬንድ ሺፕ አርት ፌስቲቫል ዲፕሎማ እና የክብር ሜዳሊያና መሰል በርካታ ሽልማቶችንም አግኝተዋል::


