የአዲሱ ኮሮና ቫይረስ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች

የአዲሱ ኮሮና ቫይረስ የበሽታ ስሜትና ምልክቶች

ገና ከመጀመሪያው የሚከሰቱት ምለክቶች
ትኩሳት፣ ሳል፣ ቁርጥማት ናቸው
ወደ ኋላ ግን የትንፋሽ ማጠር ስሜት፣ የደረት ህመም ያስከትላል፡፡ ማለትም የሳንባ ምች (ኒሞንያ) ላስተዋለ ሰው እነዚህ ስሜትና ምልክቶች ከመደበኛው ጉንፋን ወይም ኢንፍሉዌንዛም የተለዩ አይደሉም፡፡ እነዚህ ስሜቶች ደግሞ ታማሚው ለቫይረሱ ከተጋለጠ በሁለት ቀናት ውስጥ ወይም አስከ ሁለት ሳምንት (14 ቀናት ባለው ጊዜ የሚከሰቱ ናቸው፡፡ እንግዲህ ለዚህ ነው እሰከ ሁለት ሳምንት ወደኋላ ተጋልጠው ከሆነ በዚህ ቫይረስ ሊያዙ ይችላል የሚል ጥርጣሪ የሚኖረው፡፡ ወደ ህክምና ቦታ ሲዘልቁ ይህ ጥያቄ ሊቀረብልዎትም ይችላል፡፡
አዲሱ ቫይረስ መነሻው
በተለያዩ የህክምናና የጤና መፅሄቶች እንደተዘገበው፣ ይህንን ችግር ለአለም ህዝብ ያካፈለቸው ራሷ ቻይና ስትሆን፡፡ በሽታው ተነሳ የተባለበት ቦታ፣ ዉሀን በሚባል ክፍለ ሀገር፣ ነገሩ አንዲህ ነው በተህሳስ ወር አጋማሽ፣ በዉሃን፣ ሁቤ በሚባል ከተማ ያልታወቅ በቫይረስ አማከኝነት የሚከሰት የሳንባ ምች በሽታ የተያዙ ሰዎች ሰብሰብ ባለ ቁጥር ይታያሉ፡፡ የነዚህ ሰዎች አክታ በላቦራቶር ሲመረመር፣ ከዚህ በፊት ያልታየ አዲስ ቫይረስ መኖሩ ይረጋገጣል፡፡ ዝርያው ግን የኮሮና ቫይረስ ነው፡፡ ለዚህ ነው የ2019 አዲሰ ኮሮና ባይረሰ የተባለው 2019 n-cov፡፡ ይህ ምርመራ ሲደረግ በወቅቱ፣ የጤና ባለሙያተኞችን ጨምሮ ወደ 800 ሰዎች መያዛቸው ይታወቃል፡፡ ቻይኖቹ በፍጥነት ሁኔታው ለአለም ህዝብ ማስታወቃቸው እንዲመሰገኑ አድርጓቸዋል፡፡ ችሎታቸውም የሚገርም ነው፡፡ አያድረገውና በኛ…(አልጨርሰውም)፡፡
ታዲያ ይህ ቫይረስ ከእንስሳት ወደ ሰው ተሻግሮ ይሆን በማለት ክትትሉ፣ በከተማው ውሥጥ ባለው የአሳ መሸጫ ሱቅ አካባቢ ነበር፡፡ ነገር ግን ወደኋላ እንደታየው ከአሳ መሸጫ ገበያው ሰፋ ብሎ በሌሎች ቦታዎች መገኘቱ ታወቀ፡፡
መሸጋገሪያ መንገድ
ትልቁ ፍራቻ ደግሞ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል ወይ ነው፡፡ ዘግየት ብሎም ቢሆን ከሰው ወደ ሰው መተላለፉ ተረጋገጠ፡፡ ሌለው ችግር፣ እንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚያስተላልፈው በህመም ላይ እያለ ነው ወይስ የህመም ስሜት ሳይሰማው ነው የሚለው፣ ለጤና ባለሙያተኞችና ለሌሎችም ቢሆን አብይ ጥያቄ ነው፡፡ ያልታመመ ሰው፣ ግን ለቫይረሱ የተጋለጠ፣ ቫይረሱን ሌላ ሰው የሚያስተላልፍ ከሆነ፣ ለቁጥጥርና ወይም ሥርጭቱን ለመገደብ ይከበዳል፡፡ እንደተፈራውም፣ ከጀርመን በኩል በቀረበ ሪፖርት፣ የበሽታው ስሜት በውቅቱ ያልነበራት ሴት ለሌሎች ማስተላለፏ ይረጋገጣል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከቻይና ወደ ጀርመን ለሥራ የሄደች ሴትዮ ከጀርመን ኑዋሪዎች ጋር ስብሰባ አድርጋ ወደ አገሯ ትመለሳለች፡፡ ከተስበሳቢው አንዱ ቀለል ያለ የሳል በሽታ ይዘውና ወዲያው ግን ያገግማል፡፡ ሲትዮዎ ግን ወደ አገሯ ስትመለስ፣ ትታመምና ምርመራ ሲደረግ፣ ቫይረሱ እንዳለባት ይታዋቃል፡፡ ይህ ሲሆን ሁል ጊዜ የሚደረግ፣ contact investigation የሚባል ከትትል ይደረጋል፡፡ ይህ ከአባለዘር በሽታዎች ጀምሮ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሳንባ ነቀርሳን ጨምሮ፣ ለአካባቢው የመንግሥት አካል ሪፖርት ሲደረግ፣ መንግሥት፣ ተጋለጡ የሚባሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር በመያዝ ክትትልና ምርመራ የሚያደርግበት የተለመደ አሠራር ነው፡፡ እስዎም ቢሆኑ፣ የጤና ቢሮው ሰዎች በርዎን ድንግት ቢየንኳኩ እንዳይገርምዎት፣ ማለቴ ድንገት ተጋልጠዋል ከተባለ ነው፡፡ ታዲይ ጀርመኖቹ ይህንን ክትትል ሲያደርጉ፣ ያ ቀለል ጉንፋን የያዘውና ያገገመው ሰው፣ አክታ ምርመራ ያሳየው ይኸው አዲሱ ቫይረስ መኖሩን ነው፡፡ ተጨማሪ ባደረጉት ምርመራ አራት ሰዎች መጋለጣቸው ይረጋገጣል፡፡ ይህ ዜና በታወቂው የኒው ኢንግላንድ መፅሄት ሲቀርብ፣ ባለሙያተኞቹ በፍራቻ ነው ያነበበብነው፡፡ የምንሠራውን ሥረ አቀራረብም ያከብድብናል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ አንድ ሰው አመመውም አላመመውም ቫይረሱ አለበት ከሚባል ቦታ ከመጣ ተገልሎ እንዲቆይ የሚደረገው፡፡
መሸጋገሪያው ዋናው መንገድ፣ ቫይረሱ ካለበት ሰው ስድስት ጫማዎች ጠጋ ብሎ በትንፋሽ የሚወጣውን ቫይረስ መቋደስ ነው፡፡ በተለይም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሲያስለው ወይም ሲያስነጥሰው ለአይን የማይታዩ ቫይረሱን የያዙ ጠብታዎች አጠገብ ባለው ሰው አፍና አፍንጫ በሚዘልቁበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ፣ ቫይረሱ ያረፈባቸውን ዕቃዎች በመነካካት ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደሚችል ነው፡፡ ይህ በርግጥ ባይረጋገጥም፡፡ አያድርስ፡፡ በህክምናው አለም፣ በዚህ ምክንያት፣ ቫይረሱ አለበት ለተባለ ሰው አፍና አፍንጫ ላይ የሚደረግ ማስክ ተሠጥቶ ለብቻው በተለየ ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ይደረጋል፡፡ የሕክምና ባለሙያው ወደ በሽተኛው ክፍል ሲገባ ግን፣ ከራስ ፀጉር እሰከ ጫማ ድረስ ተሸፍኖ፣ ጓንት አድርጎ፣ ለዚህ ጉዳይ ለህክምና ባለሙያተኞች የሚሠት የትንፋሽ ማስክና አይን የሚሸፍን መከለያ አድርጎ ነው የሚገባው፡፡ ያው ኢቦላ ላይ እንዳያችሁት ማለት ነው፡፡
መከላከልና ህክምና
አስከሁን ድረስ፣ አማራጭ የሆነው መንገድ ለቫይረሱ አለመጋለጥ ነው፡፡ አዲስ እንደመሆኑም፣ ከትባትም የለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን፣ እንደ ባህል አድርግን ልንይዘው የሚገባ፣ በተለይም ከላይ የጠቀስኩት የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስንም ታሳቢ በማድረግ የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
እጅዎን በሳሙና ለ20 ሰከንዶች መታጠብ፡፡ ይህንን የሚያደርጉትም፣ ከሳሉ፣ ካስነጠሱ፣ አፍንጫዎን ከጠረጉ በኃላም ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን መፀዳጃ ቤት ደርሰው ሲመለሱ፣ ምግብ ከመብላትዎ በፊትም ማድረግ የሚገባዎት ነገር ነው፡፡ አጋጥሟችሁ ከሆነ፣ መፀዳጃ ቤት ገብተው ከተገለገሉ በኋላ እጃቸውን ሳይታጠቡ የሚወጡ ብዙ ሰዎች እይተው ይሆናል፡፡ ይህንን ሳይ፣ በበኩሌ፣ አንዳገሬ የአንገት ሰላምታ ብቻ ሠጥቼ የእጅ ጨበጣውን መተውን እመኛለሁ፡፡ በተለይ በኢንፍሉዌንዛ ወራቶች፡፡
ውሃ ከሌለ ደግሞ፣ እጅ ላይ የሚወለወሉ አልኮሎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ይህ ለንፅህና የሚጠቀሙት አልኮል 60% አልኮል ያለው መሆኑን ያረጋግጡ፡፡
ካልታጠቡ ግን፣ አይንዎን፣ አፍንጫዎንና አፍዎን ከመነካካት ይቆጠቡ ከታመሙ ሰዎች ጋር አለመገናኘት ይምረጡ፡፡ ያመመዎት ከሆነም፣ ለሌሎች ሲሉ ከቤት አይውጡ፣ ቤትም ውስጥ ቢሆን፣ ከተቻለ የተወሰነ ክፍል ውስጥ ብቻ ይቆዩ፡፡ ልብ ማለት የሚገባዎት፣ እነዚህ የቫይረስ በሽታዎች የሚጠናባቸው ሰዎች በዚህ ምክንያትም ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል መገንዘብ ጥሩ ነው፡፡
የሚያስልዎትና የሚያስነጥስዎት ከሆነ፣ ቲሺው ካለ በዛ ሸፈን ያድርጉ፣ የተጠቀሙበትን ወዲያው ወደ ቆሻሻ መጣያ ያስገቡ፡፡ ከሌለ ደግሞ በእጅጌዎ ሸፈን አድርገው ይሳሉ ወይም ያስነጥሱ፡፡ ልብ ማለት ያለብዎት ስድስት ጫማ ርቀት አጠገብዎ ያለ ሰው ለቫይረሱ እንደሚጋለጥ ነው፡፡
በቤት ውስጥ ወይም ድንገት ቢሮ ከሄዱም፣ በእጅ የነኳቸውን ነገሮች በማፅጃ ማፅዳት ይኖርብዎታል፡፡ ብዙ ጊዜ የሚረሳው፣ የበሮች መክፈቻና መዝጊያ ነው፡፡ ተደጋግሞ የሚነካውም ነገር አሱ ሰለሆነ፣ እጀታዎቹን ማፅዳት ተገቢ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እንግዲህ፣ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የሚመክረው ወደ ቻይና እንዳይጓዙ ነው፡፡ ይህ ባሁነ ሰአት ሲሆን ወደፊት የትኞቹን አገሮች እንደሚጨምር አይታወቅም፣ በተለይም በሽታው በስፋት ከተዛመተ፡፡

ሕክምናን በሚመለከት፡፡ ለዚህ ቫይረስ ተብሎ የተዘጋጀ ምንም አይነት መድሐኒት የለም፡፡ በአብዛኛው ድጋፍ ሰጭ ህክምና ነው የሚደረገው፣ ሌላ ተጓዳኝ በሽታ ካለ ለሱም ህክምና ይደረጋል፡፡ ብዙ ጊዜ የበሽታው ምልክት ከታየ ከሁለት ሳምንት በኋላ ከበድ ያለ የሳንባ ምች በሽታ የሚታይባቸውና እየከፋ ሲሄድም ሌሎች የስውነት ክፍሎች መድከም ይታያሉ፡፡

በቅርብ ጊዜ በወጣ ሪፖርት፣ ለኢቦላ ቫይረሰ የሚሠጠው መድሃኒትን መጠቀም የቻሉ ሀኪሞች ጠቆም ያደርጋሉ፡፡ አሱም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ አማራጭ ከማጣት የተነሳ የሚደረግ ነው፡፡

እንግዲህ ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ከመታመምዎ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ቻይና ተጉዘው ከሆነ፣ ወይም በዚህ ቫይረስ ተለከፈ ከሚባል ሰው ጋር ተገናኝተው ከሆነና፣ አሁን የህመም ስሜት የሚሰማዎት ከሆነ፣ ወደ ሆስፒታል ከመሄድዎ በፊት ደውለው እንዲያስታውቁ ይመከራሉ፡፡ ባለሙያተኞቹ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁዎት ነው፡፡ መገንዘብ ያለብን ሁሉም ታማሚ የግድ ሆስፒታል መሄድም አያስፈልገውም፡፡ በቤት ሆነው ክትትል ሊደረግሎትም ይችላል፡፡

አስከ ፌብሩዋሪ 02፣ 2020 ድረስ 2019 አዲሱን ኮረና ቫይረስ በሚመለከት

አለም አቀፍ የጤና ድርጅት፣ Public Health Emergency of International concern ብሎ አውጇል
የአሜሪካው የጤና ሚኒስትርም ቢሆን፣ በጃንዋሪ 31፣ 2020 ሁኔታውን በአሚሪካ Public Health Emergency ነው ብለው አስታውቀዋል
ፕሪዚዳንቱም ቢሆን፣ ከቻይና የሚመጡ ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ጊዜያዊ እገዳ ጥለዋል፡፡ እነዚህ ሰዎችም አሜሪካ ከመግባታቸው ከአስራ አራት ቀናት በፊት በቻይና ቆይታ ከነበራቸው ነው፡፡ ዕገዳው ሆንክ ኮንግና ማካዎን አይጨምርም፡፡
በአሚሪካም ቢሆን ከመንገደኞች ወይም ከመንገደኞች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚበሉ ሰዎች፣ ባሁኑ ጊዜ 11 ሰዎች በላብራቶሪ የተረጋገጠ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ በአሜሪካ በህብረተሰቡ ውስት እይተዘዋወረ አይደለም፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ፣ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች አገሮች ቁጥር 27 ደርሷል (አስካሁን የአፍሪካ አገር ስም አልታየም) አስከ ፌብሩዋሪ 03 ድረስ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ 17391 ሰዎች፣ ከዚህ ውስጥ 2838 አዲስ ግኝት
ከነዚሀ መሀል በቻይና 361 ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ ከቻይና ውጭ ደግሞ የአንድ ሰው ህይወት አልፏል
ነገሩ ለጊዜው እየቀጠለ የሚሄድ ነው የሚመስለው፡፡ የቻይናው ሥርጭት በጣም ከፍተኛ ደረጃ ተብሎ ነው የተሰየመው፡፡

መልካም ንባብ

ስለ ኮሮና ቫይረሶች ማወቅ የሚገባዎት

በጤና በኩል፣ አለምን ውጥረትና ጭንቀት ውስጥ እያስገባ ስለሚገኘው ኮሮና ቫየረስ ማወቅ የሚገባንን ያህል ለማስገንዘብ ይህን ጽሀፍ አቅርቤያለሁ፡፡ መጀመሪያ ስሙን ካስተዋልን፣ አዲስ ኮሮና ቫይረስ ነው የሚለው (Novel Corona virus of 2019)፡፡ አዲስ ነው ከተባለ የድሮዎቹ እነማናቸው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ ስመጥር ቫየረሶች ስለሆኑ መታወቅም ይገባቸዋል፡፡ ክፉ አውሪ አትበሉኝ እንጂ፣ ከሙያና ከታሪክ አንፃርም፣ የሰውን ልጅ ላልታሰበ ዕልቂት ከሚዳርጉት ነገሮች ቫይረሶች ትልቅ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

ኮሮና ቫይረሶች በብዛት በቁጥራቸው በርከት ያሉ የቫይረስ ቤተሰቦች ሆነው ከቀላል ጉንፋን እሰክ ለሕይወት አስጊ የሆኑ በሽታዎች ያስከትላሉ፡፡ እነዚህ ቫይረሶች በአይነት ሰባት ሲሆኑ፣ አራቱ በብዛት የሚገኙ ቀላል ጉንፋን የሚያስይዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ከ1960 ጀምሮ በህክምናው አለም የሚታወቁ ናቸው፡፡ በየጊዜው ቀላል ጉንፋን ህመም የሚያሰከትሉትን ትተን ከዘህ ቀደም በጣም በአሳሳቢ ደረጃ ተከስተው የነበሩትን ስናስተውል፡፡

እኤአ በ2002 ተከስቶ የነበረው ሳርስ ( SARS: Severe Acute Respiratory Syndrome) የሚባለው SARS-CoV
በህብረተሰቡ ዘንድ ብዙም ያልታወቀው፣ ነገር ግን በመካከለኛው ምሥራቅ ችግር ያስከተለው ሜርስ-ኮቫይረስ (Mers-co: Middle Easte Corona virus )ተብሎ የሚጠራው
አሁን በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት፣ አለማቀፋዊ አደጋ ያስከትላል ተብሎ የታወጀለት የ2019-nCoV አዲሰ ኮሮና ቫይረስ ይገኙበታል፡፡

ሥርጭትን በተመለከተ

ኮሮና ቫይረሶች ከአንስሳት ወደሰዎች የሚተላለፉ ቫይረሶች ሲሆን ከዛም ከሰው ወደ ሰው በሚያደርጉት ሥርጭት ነው ጭንቀት የሚያስከትሉት፡፡ የሳርስ ቫይረስን ብንመለከት፣ ከድመት ዝርያዎች አንዱ ከሆነው ሲቬክ ድመት ወደ ሰው የተላለፈ ሲሆን የመካካለኛው ምሥራቁ ቫይረስ ደግሞ ከግመል ወደ ሰው ነው የተሸጋገረው፡፡ እንግዲህ ከእንስሳት ወደ ሰው መተላለፍ በእንግሊዘኛው አጠራር ዞኖቲክ zoonotic የሚባል ሲሆን፡፡ ገና ወደ ሰው ያልተሻገሩ በእንስሳቱ ላይ የሚዘዋወሩ ብዙ ቫይረሶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአብዛኘው ወደ ሰው ሲዘሉ ቸግር የሚያስከትሉ ቢሆንም ከአንስሳቱ ጋር ተላምደው የሚኖሩ ይመስላሉ፡፡ ይህ አዲሱ ኮሮናቫይረስ፣ በቻይና ተከሰተ ሲባል፣ ዉሃን በሚባል ክፍለ ሀገር በአሳ መሸጫ ገበያ አካባቢ ነው የተነሳው ነው የሚባለው፡፡ አሁን ግን፣ እንደምንመለከተው ከዚያ ሰፋ ብሎ ወጥቷል፡፡

የሚያስከትሉት የበሽታ አይነትና ለህይወት ማለፍ ደረጃ

አዲሱን የ2019 ኮረኖቫይረስ በመጠኑም ቢሆን ከከፍተኛ ስጋት ወረድ ያለ እንዲሆን ያደረገው፣ በቫይረሱ ከተለከፉ ሰዎች ምን ያህሉ ህይወታቸው ያልፋል የሚለው ጥያቄ መልስ ነው፡፡ ይህንን ለመገንዘብ በሶስቱ ቫይረሶች መሀል ያለውን ልየኑት እናነፃፅር

የሳርስ ቫይረስ፡ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ከመቶ አሥሩ ሕይወታቸው ያልፋል (9.6)፣ በ2002 በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ በዘጠኝ ወራት ውሥጥ 8096 ሰዎች በቫይረሱ የተለከፉ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ሞተዋል ተብሎ የተዘገበው የሰዎች ቁጥር 774 ነበር፡ በዚያን ጊዜ ከፍተኛ የሆነ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ነገር እንደነበር፣ ከሙያ አንፃር የማይረሳ ትዝታ ነበር፡፡ ይህ ከቻይና ተነስቷል የተባለው ቫይረስ ከ2004 ወዲህ ድምፁ አልተሰማም፡፡
ቀጥሎ የተከሰተው ደግሞ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የታየው ሜርስ-ኮቫይረስ ነው፡፡ ይህ ቫይረስ አሁንም ድረስ ችግር የሚያሰከትል ነው፡ ይህ ከሳውድ አረቢያ ተነስቶ ወደሌሎች አገሮች የተዛመተው ቫይረስ በስፋት ባይሠራጭም በአይነ ቁራኛ የሚጠበቅ ቫይረስ ነው፡፡ በአረብ የባህር ሠላጤ አካባቢ ሰለሚታይ ነው የመካከለኛው ምሥራቅ ኮሮናቫይረስ የሚባለው፡፡ ይህ ቫይረስ ከግመል ጋር በሚደረግ ንክኪ የሚመጣ ሲሆን፣ ከሳውዲና ሌሎች የአረብ አገሮቸ ተነስተው በሚጓዙ መንገደኞች ወደሌላው አለም ይዛመታል፡፡ ከመጠነኛ ሳል አዘል በሽታ አስከ ከባድ የሕይወት ህልፈት ምክንያትም ነው፡፡ አስከ ጃንዋሪ 2019 በቀረበው ሪፖርት በቫይረሱ በላቦራቶሪ የተረጋገጠ 2298 ሰዎች በ27 አገሮች ውስጥ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስት 811 ህይወታቸው አልፏል፡፡ በሂሳብ ሲሰላ፣ ከተለከፉት መሀል 35 ፐርስነቱ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ከአንድ ሶሰተኛ በላይ ማለት ነው፡፡ ለዚህ በሽታ ሠርጭት ምክሩ፣ ከግመሎች መራቅ፣ የግመል ጥሬ ወተት አለመጠጣት፣ ከግምል ሽንትም ጋር ንክኪ አለማድረግ ነው፡፡ አሁንም በአይነ ቁረኛ ሰለሚጠበቅ ነው ሰፋ አድርጌ ያቀረብኩት፡፡ የባሰ አለ ለማለትም ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ቫይረሶች የመጀመሪያ ምንጫቸው ናቸው የሚባሉት የሌሊት ወፎች ናቸው፡፡
ይህ አዲስ ኮሮና ቫይረስ ደግሞ አስካሁን ድረስ በተደረገው ዘገባ ከተያዙ ሰዎች መሀከል አስከ 2.9 በመቶ የሚሆኑት ህይወታቸው ያልፋል፡፡ ቸግሩ ግን ይህ የህይወት ማለፍ ደረጃ እንደተያዘው ሰው የጤንንት ደረጃ ነው፡፡ የሚበረታባቸው ሰዎች እንዳሉ መገንዘብ ያሻል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ውጭ ግን፣ ሰልተለመደ እንጂ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ነው፡፡ በሰሜን አሜሪካ በየአመቱ በቀዝቃዛው ወራት መታወቂያውን እየቀየረ ብቅ የሚለው ይህ የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ በ2019 አስከ 600ሺ ሰዎች ድረስ የለከፈ መሆኑ ሲታወቅ፣ ለምርመራ ከተላከው ናሙና ወደ 107ሺ የሚሆነው የኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ተግኝቶበታል፡፡ በነገራችን ላይ በከፍተኛ ደረጃ ህመም ከሚያስከትሉ ቫይረሶች፣ ኢንፍሉዌንዛ A ና ኢንፍሉዌንዛ B ይገኙበታል፡፡ የዚህ በሽታ መክፋት መለኪያዎች፣ በቫይረሱ መለከፍ ምክንያት ምን ያህል ሰዎች ሆስፒታል ገብተው የታከሙ መሆናቸውና ከዚህ ጋር በተያያዘም የምን ያህል ሰዎች ህይወት እንዳለፈ ማወቅ ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ ዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ሰዎች በብዛት ሆሰፒታል ውስጥ ተኝተው የሚታከሙ ሲሆን ባጠቃላይ ከ100ሺ ሰው 29.7 የሚሆኑት ሆስፒታል እንዲገቡ ምክንያት ነው፡፡ ዕደሜያቸው ከ65 አመት በላይ ከሆነ፣ ይህ ቁጥር ወደ 71.3 ያድጋል፡፡ ከኢንፍሉዌንዛና የሳንባ ምች ጋር በተያያዘ፣ በአሜሪካ፣ 6.7 ከመቶ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይሕ ቁጥር፣ ከ7.2 በመቶ በታች በመሆን በከፍተኛ ደረጃ ተዛምቷል አልተባለም፡፡ ካስተዋልን ግን፣ ኢንፍሉዌንዛ፣ ከአዲሱ ኮሮና ቫይረስ በላይ ገዳይ ነው፡፡ ደግነቱ፣ ለኢንፍሉዌንዛ ክትባትም አለ፣ መድሀኒተም አለ (ወዲያውኑ መወሰደት አለበት)፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe