የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት መግለጫ ምን ይላል?

በጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ የሚመራው የአዲስ አበባ የባለአደራ ምክርቤት ባሳለፍነው ቅዳሜ መጋቢት 21/2011 ዓ.ም ለጋዜጠኞች ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከሉ ይታወሳል። ይህንኑ ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት ክልከላው የተደረገው የፀጥታ ስጋት በመኖሩ ለደህንነት ሲባል እንደሆነ አስታውቋል።

በመሆኑም ከእስክንድር ነጋ ጋር በመነጋጋር በሚፈልገው ቦታና ጊዜ መስጠት እንደሚችል በገለፀው መሰረት ዛሬ መጋቢት 25/2011 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል በሚል አራት ኪሎ በሚገኘው የእስክንድር ነጋ ቢሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የምክርቤቱ አመራር አባላትም ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት ‘የከፋፍለህ ግዛ’ ዓላማ ባነገቡ አምባገነኖች መዳፍ ወድቃ ብዙ ፈተናዎችን እንዳለፈች የሚያነሳው መግለጫው ለዚህ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ የሚያፋጁ የልዩ ጥቅም ፈሊጥ አንደኛው ወጥመድ እንደሆነም ተጠቅሷል።

በዚህም የገዥ ፓርቲው አካል የሆነው ኦዴፓ አንዱ መሆኑ በእጅጉ እንደሚያሳስበው የገለፀው ምክር ቤቱ “ማንኛውም ሂደት ፍፁም ሊሆን ስለማይችል በሂሳዊ ድጋፍ እየሞረዱና እያስተካከሉ መሄዱ የግድ ነው” ሲል ያክላል።

ምንም እንኳን የሀገሪቷ አበይት የትኩረት አቅጣጫ የምርጫ ጉዳይ ቢሆንም የአዲስ አበባን ጉዳይ በጎንዮሽ ለማንሳት መገደዳቸውን ገልፀዋል።

በዲሞክራሲ መንገድ የተመረጠ አስተዳደር አለመኖር ዋናው ጥያቄ መሆኑን የሚያነሳው ምክርቤቱ ይህም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ክስተት ነው ብለዋል። “በሌሎች የሃገሪቷ ክልሎችና ከተሞች ባልታየ መልኩ የነዋሪዎቿ ጥቅምም እየተገፋ ይገኛል” ሲል መግለጫው አትቷል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ የታደሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ህገ ወጥ መታወቂያዎች፣ ከተማዋ ወኪሎች ባልመረጠችበት ሁኔታ ከኦሮሚያ ጋር ያለው የአስተዳደር ወሰን ድርድር እንዲደረግ መወሰኑ፣ የከተማዋን የብሔር ስብጥር ለመቀየር ዒላማ ያደረገው መንግስታዊ ሰፈራ እቅድ እና ኦዴፓ ስለ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ ያወጣቸው መግለጫዎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው በሰላማዊ መሆኑን እንደተገነዘበ የሚገልፀው ምክር ቤቱ “ከመሰረታዊ መርህ ፍንክች እንደማይል በአደባባይ ቃል ገብቷል፤ ይህንን ቃልኪዳን ሰምቶና አይቶ እንዳልሰማና እንዳላየ በመሆን በህዝብ በተወከለው ምክርቤታችን ሰላማዊ አካሄድና ህጋዊነት ላይ ከባለስልጣን የሚነሱ ጥያቄዎች ፈፅሞ አግባብነት የላቸውም” ሲልም አስታውቋል።

እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችም መልስ ላለመስጠት ሰበብ ፍለጋ ነው የሚል ጥርጣሬ እንዳሳደረባቸውም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በአንድ መድረክ ላይ ግልጽ ጦርነት ውስጥ እንገባለን ብለው ስለሰጡት አስተያየት የተጠየቀው እስክንድር መልስ ሲሰጥ “እንቅስቃሴያችን ሰላማዊና ሕጋዊ እንዲሆን ውክልና የሰጠን ሕዝብ ቃልኪዳን አስገብቶናል። ጦርነት ቢከፈትብን እንኳን ምላሻችን ሰላማዊ ነው። የሃሳብ ጦርነት ግን ልንፋለም እንችላለን” ብሏል።

“ባልደራስ የተሰባሰበው በአስር ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ውክልና ስላለን ሞራላዊና ፖለቲካዊ ሕጋዊነት አለን፤ የከተማው ምክር ቤት ከንቲባውን ጨምሮ ይህ የለውም” ሲልም ጨምሮ ተናግሯል።

በመጨረሻም በአዲስ አበባባና በኦሮሚያ መካከል ሊደረግ የታሰበ የአስተዳደር ወሰን ድርድር በሁለቱም ክልል በህዝብ የተመረጡ መስተዳድሮች እስኪሰየሙ ድረስ እንዲቆይ፣ የከተሞች የብሔር ስብጥር ለመለወጥ ሲባል የተጀመረው የሰፈራ መርሃ ግብር በህዝብ የተመረጡ መስተዳድሮች እስከሚሰየሙ እንዲቆም የሚሉ ሁለት ጥያቄዎችን ለመንግስት አቅርበዋል።

እነዚህን ጥያቄዎችም ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፣ ለኦሮሚያ ክልል መስተዳድር ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ማድረሳቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል።

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክርቤት መጋቢት 1/2011 ዓ.ም ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ እኩልነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ሰላማዊነትን የእንቅስቃሴው መሰረት አድርጎ በባልደራስ አዳራሽ በተስብሳቢው ድምፅ እንደተቋቋመ ምክርቤቱ አስታውሷል።

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe