የአድዋ ድል ትሩፋት ምንድነው? /ነጭ ነጯን/

 የዐድዋ ድል ሀገራችንን ማንም ሊያወርዳት ከማይችልበት ከፍታ ላይ የሰቀላት እንደሆነ ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች እየተለገፀ ነው።
 የአድዋ ድል የዛሬ 125 ዓመት ያስገኙት ጀግኖች አባቶቻችን በእርግጥም አንገታቸው ቀና አድርገው ሲሄዱ ነበረ፤ ይህ ግን የቀጠለው እስከ 1966 ግብታዊው አብዩት ድረስ ይመስለኛል፤ ኢትዮጵያ ምናልባትም በዓለም አደባባይ መዋረድ የጀመረችው 40 ዓመት የመሯትንና የአፍሪካ አባት የሚል የክብር ካባ የደረቡትን አፄ ኃይለስላሴን ገድላ ሽንት ቤት ስር ከቀበረችበት ጊዜ ጀምሮ ይመስለኛል፡፡
– አድዋ በዓለም አደባባይ አንገታችን ቀና አድርግ እንድንሄድ ያደረገን ድል ነው ብንልም ኢትዪጵያውያን እንደ አሁኑ በዓለም አደባባይ አንገታችን የደፋን ህዝቦች መሆናችንን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ዛሬ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው በዓለም አደባባይ በአድዋ ሳቢያ በማናቸውም ቦታዎች ቅድሚያ አገልግሎት የሚያገኘው?
– ወደ ውጭ ሀገር የተጓዛችሁ ሰዎች መስከሩ የኢትዮጵያ ፖስፖርት በመያዛችሁ ሳቢያ ‹ይህማ ለመላው የጥቁር ህዝቦች ፋና ወጊ የሆነውን የአድዋ ድል ያመጡ ኩሩ ህዝቦች ዜጋ ነው› ተብሎ የተለየ መስተንግዶ ያገኘ ኢትዮጵያዊ?
– ዛሬ ወደ ውጭ ገር ለመሄድ በየውጭ ሀገር ኤምባሲ ደጃፍ ላይ ቪዛ ለማግኘት ያለው ሰልፍና ወረፋ ከእኛ ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች አንገት ቀና የሚያስደርግ ነው ወይስ የሚያስደፋ?
– በዲቪ ስም ወደ አሜሪካ ለማግባት በሀይማኖት ህጋችን ሆነ በሞራል ደንባችን ከተፃፈው በተቃራኒ ቪዛ ለማግኘት ሲባል ወንድም ከእህቱ ጋር እህትም ከወንድሟ ጋር አልተጋባንም፤ ይሄ አንገት የቀና አድርጎ በኩራት መሄድን ወይስ አንገት መድፋታችን ያሳያል?
– በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚሰማው ዜና የቱን ይነግረናል?
– ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በባህር ላይ አቋርጠው አውሮፖ ለመግባት ሲጓዙ ባህር ላይ ስለመቅረታቸው ፤ አስከሬናቸውንም የሻርክ ሲሳይ የመሆኑ ዜና ኢትዮጵያን ከማይወርድ ማማ ላይ ያስቀምጣታል ወይስ አንገት ያስደፋል?
– በሊቢያ በረሃ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አንገታቸው የመቀላቱ ዜና፤ በህይውት እያሉ ኩላሊታቸው ከሰውነታቸው ውስጥ መወሰዱ አንገት ቀና ያስደርጋል ወይስ ያስደፋል?
– በ2009 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በኮንቴነር አሳፍሮ በማላዊ በረሃ አቋርጦ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዝ በነበረው መኪና ውስጥ የነበሩ 37 ወጣቶች በሙቀት ሳቢያ ታፍነው ሲሞቱ ገላቸው እርስ በእርሱ በመጣበቁ ሳቢያ ማን ማን እንደሆነ የማላዊ ፖሊሶች መለየት አቅቷቸው ነበር፤ ይህ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ የእነዚያ የአድዋ ድል ጀግኖች ልጆች ናቸው ተብሎ ገመናችን ማን ሸፈነልን?
ደረቴ ላይ ያለው የሀገሬ ባንዲራ
ያምራል ተባለ እንጂ ክብሩም አልተፈራ› እንዲሉ አብየ መንግስቱ ፤
– የቢቢሲ ዜና ፡- በ2017 ብቻ በዚህ መልኩ 1 ሺ 700 ኢትዮጵያውየን በኬኒያ፤በዲሞክራቲክ ኮንጎ፤በዛምቢያና በማላዊ ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ዜጎች አስከሬናቸው በአውሬ ተበልቷል፤ እህስ አንገት ቀና ያደርጋል ወይስ ያስደፋል?
ሰው እያለ አጠገባችን እሱነቱን ማየት ሲያመን
ከእኛ አብሮ በህይወት ቆሞ መልካም ስሙን መጥራት ሲያቅተን
ሰው ካልሞተ ወይ ካልሄደ አይነሳም እንላለን
እንዲህ እያልን
ስንቱን ጠቢብ ሸኘነው አበባውን ቀጥፈን ጥለን
አበባ ብቻ እናስቀምጣለን /ነብይ መኮንን/
– ሩቅ ሳንሄድ ባለፉት ሶስት ዓመታት ራሳችን በራሳችን ወገኖች ላይ የፈፀምነው ግፍ የኩሩዎች የአድዋ ጀግኖች ልጆች ስለመሆናችን ያሳያል ወይስ ያሸማቅቃል?
ሀይሌ ገ/ስላሴ በዓለም አደባባይ በሩጫ ድል ሲያደርግ ድሉ የሀይሌ ብቻ ነው ወይስ የሁላችንም የኢትዮጵያውያን?
– የሁላችንም ከሆነ
በሻሸመኔ ተዘቅዝቆ የተሰቀለውና በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው ወጣትን የገደሉት የተወሰኑ ሰዎች ናቸው ወይስ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን?
በመተከል፤በነቀምት፤በበደኖ፤በአረካ፤ወዘተ ከጥይት አልፈን በቀስትና በካራ የፈጀናቸው ሰዎች ጣሊያናውያን ናቸው ወይስ ኢትዮጵያውያን?
ቀይ ሽበርና ነጭ ሽብር ብለን ወጣቶችን በየመንገዱ ላይ እየገደልን ቤተሰቦቻቸውን የጥይት ሂሳብ መጠየቃችን ምን የሚሉት ጀግንነት ነው?
ይህ ዜና በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ሲዘገብ እኛ የአድዋ ጀግኖች ልጆች ነን ብለን አንገታችንን ቀና እንደርጋለን ወይስ እንደ ህዝብ አንገታችን እንደፋለን?
በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ የሄዱ ኢትዮጵያውያን በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የመኪና ጎማ ራሳቸው ላይ ተደርጎ በእሳት አልጋዩም? ይሄ ለአፍሪካ ለመላው ጥቁር ህዝብ ፋና ወጊዎች ነን ብለን የምንኩራራበት አድዋ ከእሳቱ ነበልባል ለመከላከል ከቶ እንዴት አላስቻለንም?
– ዜኖፎቢያ በሚባለው ዘመቻ ያለቁ ኢትዮጵያወያን እነማናቸው? ስንት ናቸው? ይታወቃሉ?
ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት በስንዴ ልመና የምንታወቅ ዜጎች ከመሆናችን ጋር ተያይዞ በመዝገበ ቃላት መፍቻ ላይ ሳይቀር ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ለፋሚን ወይም ለረሃብ መፍቻነት መዋሉ የአባቶቻንን ገድል ዘወትር እንደንተርክ ያደርገናል ወይስ?
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለውን ችግር በተመለከተ ከኬኒያው ፕሬዚዳንት ጋር በስልክ መወያየታቸው ተዘግቧል፤ በማን ጉዳይ ነው አሜሪካ ማንን የምታናግረው?
አንገትህን የደፋህ ህዝብ ስለሆንክ አሜሪካ እኛን አልፋ በእኛ ጉዳይ የሌላ ሀገር መሪ ብታናግር አይግረምህ
የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ፤ በተለይም የአማራ ልዩ ኃይልን በሚመለከት ያወጣው መግለጫ ተገቢነት የሌለው ነው ብሏል። ለማለት ያህል ብቻ
– አይግረምህ፤ ገና የየካ ክፍለ ከተማ ሊቀ መንበር አቶ አበበን እንጂ አቶ ከበደን ለምን አደረጋችሁ ትለናለች፤ለምን አንገትህን የደፋህ ህዝብ ነሃ! ጥላሁን ገሠሠ እንዳለው ‹ከሌለህ የለህም›
– በነገራችን ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባልን ያለው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ነው ፤ሳሊኒን እኛ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ ስላለን ቀጠርነው ወይስ ከ125 ዓመት በኋላም ባለንበት ቆመን ስለጠበቅነው እንደገና ሊያቀናን መጣ?
– ከዚህ አንገት መድፋ እንደ ህዝብና እንደ ሀገር ለመውጣት ምን ማድረግ አለብን?
– የዐድዋ ድል ሀገራችንን ማንም ሊያወርዳት ከማይችልበት ከፍታ ላይ ሰቅሏታል፤ ከሚለው ግብዝነት ወጥተን አንገታችንን ከመድፋት ለመውጣት ምን እናድርግ?
– ፖለቲካን ለፖለቲከኞች እንተው
– ወጣቶች ስራ ሳትመርጡ ስሩ፤
– ገበሬው ያምርት
– ግንበኛው ገንቡን ብቻ ይስራ
– አንፂው እንጨቱን ይጥረብ
– መምህሩ ያስተምር
– ነጋዴው ይነግድ
– ተማሪ ስራው መማር ብቻ ይሁን፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ይቅሰም፤
– የሀይማኖት አባቶች ግብረ ገብ ያስተምሩ፤
– አርቲስቶች ፍቅርን ይዘምሩ
– ሐኪሞች ህሙማንን ይርዱ ፤ሰው መሆንን ያስቀድሙ፤ ወዘተርፈ
– ከ5 ዓመት በኋላ 130ኛውን ዓመት የአድዋ ድል በዓል ስናከብር እንደዘንድሮው አንገታችን እንዳንደፋ ዛሬ መሠረት እንጣል፤ በቁጭት እንነሳ፤
– ያን ግዜ እኛም እንደ አፄ ምንሊክ ትውልድ ታሪክ ሰሪ እንሆንና በቀጣዩ ትውልድ እንዘከራለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe