የአድዋ ድል ትሩፋት ምንድነው? የፈረንጅ ቅኝ ገዢን በሐበሻ መቀየር ነውን?

ከ127 ዓመታት በፊት በዓድዋ ተራሮች አውሮፓዊ ቅኝ ገዥ በነበረው የጣሊያን ሠራዊት ላይ የተገኘው አንፀባራቂ ድል፣ ዘንድሮ በመላ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ተከብሯል፡፡ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሪነት በ1888 ዓ.ም. በተካሄደው ፍልሚያ የተገኘው ታላቅ ድል፣ የኢትዮጵያዊያንን የአይበገሬነት ከፍታ ከመጨመሩም በላይ ኢትዮጵያንም የአፍሪካውያንና የመላው ጥቁር ሕዝቦች አብሪ ኮከብ ማድረጉን በየመገናኛ ብዙሃኑ ላይ የተጋበዙ ባለስልጣናትና የታሪክ ሰዎች በማውሳት፣የዓድዋ ጀግኖችን ዘክረዋል፡፡

እርግጥ ነው፤

ዓድዋ ከፍታ ላይ ከሰቀላቸው የኢትዮጵያ ዕሴቶች አንዱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ነው፡፡ ከምዕራብና ከምሥራቅ፣ ከሰሜንና ከደቡብ የዘመቱ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በመልክና በሙያ ኅብር የሆኑ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት የማዳን የአንድነት ዓላማ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ያስገኙት ድል ነው፡፡ በዓድዋ ዘመቻ ከ10 ዓመት ሕፃን እስከ 90 ዓመት አዛውንት ተካፍለዋል። ማየት የቻሉት ብቻ ሳይሆኑ ዓይነ ሥውራንም ዘምተዋል፤

እርግጥ ነው፤ ይህ ሁሉ ኅብረ ብሔራዊ ሠራዊት የተለያየ ቋንቋ እየተናገረ፣ የተለያየ እምነት እያመነ፣ የተለያየ ዓይነት ምግብ እየተመገበ፣ የተለያየ ዓይነት ልብስ ለብሶ፣ የተለያየ ዓይነት ባህል ይዞ፣ በምን እየተግባባ ዘመተ የሚለውን ቢጠየቅ መልሱ ግልፅ ነው፤ የተግባባው በኢትዮጵያዊነቱ ነበር። ኢትዮጵያዊ ኅብረ ብሔራዊነታችን መግባቢያ ቋንቋ ነውና፡፡ አንድነታችን የሚሠራበት ሰበዝ፣ ጥንካሬያችንን የሚገነባው ቅመም፣ ውበታችን የሚኳልበት ቀለም የሚቀዳው ከሌላ ሳይሆን ከኅብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነታችን ነውና፤

እርግጥ ነው ፤የዓድዋ ዘመቻ ኢትዮጵያውያንን ከጥንቱ በተሻለ ያስተሳሰረ ዘመቻ እንደነበረ፣ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን፣ ከሁሉም ብሔሮች፣ ከሁሉም እምነቶች፣ ከሁሉም ዓይነቶች ለአንድ ዓላማ፣ በአንድ ቦታ  ወረኢሉ ላይ ተገናኝተዋል። ዓድዋ ዘምተዋል።

‹እርግጥ ነው፤ በውጊያው ጊዜ ከቅድመ አያቶቻችን መካከል አንዳቸው ጎድለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ዓድዋም፣ የዓድዋ ልጅነትም ከእነ አካቴው ባልኖሩ ነበር። የአገርን ጥሪ እኩል ሰምተው በጋራ ባይዘምቱና ዓድዋ ላይ የድል ሰንደቅ ባይተከሉ ኖሮ፣ ዛሬ የምናከብረው የድል ቀን መሆኑ ቀርቶ እንደ ሌሎች አፍሪካውያን የነፃነት ቀን በሆነ ነበር።

እርግጥ ነው፤በድል ቀንና በነፃነት ቀን መካከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለ። ዓድዋ ከእኛ የድል ሰንደቅነት አልፎ ተርፎ ለብዙ የነፃነት ቀናት እንደ ምንጭ ሆኖ ያገለገለ፣ ለፀረ ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴዎች ፋና የለኮሰ፣ በሁለት ዘሮች በጥቁሮችና በነጮች መካከል የተገነባውን የበታችነትና የበላይነት ግንብ የፈረካከሰ፣ ባለ ብዙ መልክ ትዕምርት ነው፡፡

እርግጥ ነው፤በተለያዩ አካባቢዎች አኩርፈው የሸፈቱ ሳይቀሩ ዕርቅና ሰላም እያወረዱ ከዓድዋው ዘማች ጋር መቀላቀላቸውን፣ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የአመራር ጥበብ የታየበት ድል መሆኑን፣ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በአራት መንገድ ሠራዊቱን ማደራጀታቸውን፣ የኋላ ኋላ ዕውን የሆነው ድል በአንድ ጀንበር የመጣ እንዳልነበረ፣ ብርቱ የአገር ልጆች በተለያዩ መንገዶች መሣሪያ በማሰባሰብ፣ ስንቅ በማዘጋጀት፣ ጥቂት ጊዜ መግዛት የሚያስችል የዲፕሎማሲና በመረጃዎች የመራቀቅ ሥራዎችን በማከናወንና ሠራዊቱን አደራጅተው በመዝመት ያንን ድል ማሳካታቸው እሙን ነው።

እርግጥ ነው ፤ የተገኘው ድል ይህ የመሪዎችን የአመራር ብልኃትና የሠራዊቱን መርህ ጠባቂነት ያሳየ ነበር። የአመራር ብልኃት፣ የመሣሪያ አጠቃቀም፣ የሠራዊት ብቃትና የመልክዓ ምድር አያያዝ ተባብረው ያስገኙት ድል ነው፡፡ በአጠቃላይ የዓድዋ ድል የማይቻል የሚመስለው የተቻለበት፣ የማይቀየረው የተቀየረበት ታሪካዊ ድል ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ ያልዘመነ ጦር የታጠቀ አፍሪካዊ ኃይል ልዩ ልዩ የዘመኑ የጦር መሣሪያዎችን እስከ አፍንጫው የታጠቀ አውሮፓዊ ኃይል ድባቅ መትቶ የጣለበት ውብ አጋጣሚ እንደነበር፣ የማይቀየር የሚመስለው የነጮች የበላይነት ታሪከ በጥቋቁር አናብስት የተሸነፈበት፣ ኢትዮጵያም በዓለም አደባባይ ጥቁር ፈርጥ ሆና ብቅ ያለችበት ድንቅ ጊዜ ነበር፡፡

እርግጥ ነው፤ ‹‹ዓድዋ ድል ብቻ አይደለም። ዓድዋ የኢትዮጵያ መለያ ‹ብራንድ› ነው። የኢትዮጵያውያን ከፍታ እንዴት ሊመጣ እንደሚችል የሚያሳይ ፍልስፍና ነው። ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከመተንተን ይልቅ ዓድዋን ማሳየት በሚገባ ለመረዳት ያስችላል። መሪና ተመሪ ተናቦና ተገናዝቦ ከሠራ ውጤቱ እንዴት ዓለምን እንደሚቀይር ዓድዋ  ማሳያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት በተከበረው የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ   ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፍ ሐሳብ እንዳለን ዓድዋ ትልቁ ምስክራችን ነው›› ማለታቸው ይታወሳል፤

ግን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት  እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዘመን ለአፍሪካና ለዓለም የሚተርፍ ሀሳብ ባለቤቶች ነን ወይ የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ነው፤ እውነታቸውን መጋፈጥ ለለውጥ ያግዛልና የታሪካችንን ሌላኛውን ገፅታ ብንገልጥስ

 • የዐድዋ ድል ሀገራችንን ማንም ሊያወርዳት ከማይችልበት ከፍታ ላይ የሰቀላት እንደሆነ ይነገራል፤ ሰሞኑንም በተለያዩ ሚዲያዎች እየተለገፀ ነው።
 • የአድዋ ድል የዛሬ 127 ዓመት ያስገኙት ጀግኖች አባቶቻችን በእርግጥም አንገታቸው ቀና አድርገው ሲሄዱ ነበረ፤ ይህ ግን የቀጠለው እስከ 1966 ግብታዊው አብዮት ድረስ ይመስላል፤ እስካዛ ድረስ መሪዎቻቸን ወደ አውሮፓም ሆነ አሜሪካ ሲሄዱ መንገድ ተዘግቶ አቀባበል ይደረግላቸው ነበር፤ ዜጎቻችን ለትምህርት በየሀተዱባቸው ሀገራት ተምረው ይመለሱ ነበር፤ መቅረት አይታሰብማ! ኢትዮጵያ ምናልባትም በዓለም አደባባይ መዋረድ የጀመረችው 40 ዓመት የመሯትንና የአፍሪካ አባት የሚል የክብር ካባ የደረቡትን አፄ ኃይለስላሴን ገድላ ሽንት ቤት ስር ከቀበረችበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን አይቀርም፡፡
 • አድዋ በዓለም አደባባይ አንገታችን ቀና አድርግ እንድንሄድ ያደረገን ድል ነው ብንልም ኢትዪጵያውያን እንደ አሁኑ በዓለም አደባባይ አንገታችን የደፋን ህዝቦች መሆናችንን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ዛሬ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው በዓለም አደባባይ በአድዋ ሳቢያ በማናቸውም ቦታዎች ቅድሚያ አገልግሎት የሚያገኘው?
 • ወደ ውጭ ሀገር የተጓዛችሁ ሰዎች መስከሩ የኢትዮጵያ ፖስፖርት በመያዛችሁ ሳቢያ ‹ይህማ ለመላው የጥቁር ህዝቦች ፋና ወጊ የሆነውን የአድዋ ድል ያመጡ ኩሩ ህዝቦች ዜጋ ነው› ተብሎ የተለየ መስተንግዶ ያገኘ ኢትዮጵያዊ?
 • ዛሬ ወደ ውጭ ሀገር ለመሄድ በየውጭ ሀገር ኤምባሲ ደጃፍ ላይ ቪዛ ለማግኘት ያለው ሰልፍና ወረፋ ሌሎች ጥቁር ህዝቦችን አንገት ቀና የሚያስደርግ ነው ወይስ የሚያስደፋ?
 • በዲቪ ስም ወደ አሜሪካ ለማግባት በሀይማኖት ህጋችን ሆነ በሞራል ደንባችን ከተፃፈው በተቃራኒ ቪዛ ለማግኘት ሲባል ወንድም ከእህቱ ጋር እህትም ከወንድሟ ጋር አልተጋባንም፤ ይሄ አንገት የቀና አድርጎ በኩራት መሄድን ወይስ አንገት መድፋታችን ያሳያል?
 • በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚሰማው ዜና ምን ይነግረናል?
 • ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በባህር ላይ አቋርጠው አውሮፖ ለመግባት ሲጓዙ ባህር ላይ ስለመቅረታቸው ፤ አስከሬናቸውንም የሻርክ ሲሳይ የመሆኑ ዜና የአሁኒቷን ኢትዮጵያን ከማይወርድ ማማ ላይ ያስቀምጣታል ወይስ አንገት ያስደፋል?
 • በሊቢያ በረሃ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አንገታቸው የመቀላቱ ዜና፤ በህይወት እያሉ ኩላሊታቸው ከሰውነታቸው ውስጥ መወሰዱ አንገት ቀና ያስደርጋል ወይስ ያስደፋል?
 • በ2009 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በኮንቴነር አሳፍሮ በማላዊ በረሃ አቋርጦ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዝ በነበረው መኪና ውስጥ የነበሩ 37 ወጣቶች በሙቀት ሳቢያ ታፍነው ሲሞቱ ገላቸው እርስ በእርሱ በመጣበቁ ሳቢያ ማን ማን እንደሆነ የማላዊ ፖሊሶች መለየት አቃተን ብለው ለሚዲያ ተናግረው ነበር፤ ይህ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲተላለፍ የእነዚያ የአድዋ ድል ጀግኖች ልጆች ናቸው ተብሎ ገመናችን ማን ሸፈነልን?

ደረቴ ላይ ያለው የሀገሬ ባንዲራ

ያምራል ተባለ እንጂ ክብሩም አልተፈራ› እንዲሉ አብየ መንግስቱ ፤

 • የቢቢሲ ዜና ፡- በ2017 ብቻ በዚህ መልኩ 1 ሺ 700 ኢትዮጵያውየን በኬኒያ፤በዲሞክራቲክ ኮንጎ፤በዛምቢያና በማላዊ ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ዜጎች አስከሬናቸው በአውሬ ተበልቷል ይላል፤ እህስ ይሄ ዜና አንገት ቀና ያስደርጋል ወይስ ያስደፋል?

ሰው እያለ አጠገባችን እሱነቱን ማየት ሲያመን

ከእኛ አብሮ በህይወት ቆሞ መልካም ስሙን መጥራት ሲያቅተን

ሰው ካልሞተ ወይ ካልሄደ አይነሳም እንላለን

እንዲህ እያልን

ስንቱን ጠቢብ ሸኘነው አበባውን ቀጥፈን ጥለን

አበባ ብቻ እናስቀምጣለን /ነብይ መኮንን/

 • ሩቅ ሳንሄድ ባለፉት ሶስት ዓመታት ራሳችን በራሳችን ወገኖች ላይ የፈፀምነው ግፍ የኩሩዎች የአድዋ ጀግኖች ልጆች ስለመሆናችን ያሳያል ወይስ ያሸማቅቃል?

ሀይሌ ገ/ስላሴ በዓለም አደባባይ በሩጫ ድል ሲያደርግ ድሉ የሀይሌ ብቻ ነው  ወይስ የሁላችንም የኢትዮጵያውያን? እርግጥ ነው ድሉ የሁላችንም ነው፤

 • የሁላችንም ከሆነ

በሻሸመኔ ተዘቅዝቆ የተሰቀለውና በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው ወጣትን የሰቀሉት እነማናቸው ? በወለጋ ነፍሰ ጡር ሴት የገደሉትስ? የተወሰኑ ሰዎች ናቸው ወይስ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን?

በመተከል፤በነቀምት፤በበደኖ፤በአረካ፤በሽሬ፤ በአክሱም፤ በዶምቢዶሎ፤ወዘተ ከጥይት አልፈን በቀስትና በካራ የፈጀናቸው ሰዎች ጣሊያናውያን ናቸው ወይስ ኢትዮጵያውያን?

 • 40 አመታት ወደ ኋላ ስንደረደር ቀይ ሽበርና ነጭ ሽብር ብለን ወጣቶችን በየመንገዱ ላይ እየገደልን ቤተሰቦቻቸውን የጥይት ሂሳብ የጠየቅነው እኛ አይደለንም? ምን የሚሉት ጀግንነት ነው?

ይህ ዜና በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ሲዘገብ እኛ የአድዋ ጀግኖች ልጆች ነን ብለን አንገታችንን ቀና እንደርጋለን ወይስ እንደ ህዝብ አንገታችን እንደፋለን?

 • በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ የሄዱ ኢትዮጵያውያን በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የመኪና ጎማ ራሳቸው ላይ ተደርጎ በእሳት አልጋዩም? ይሄ ለአፍሪካ ለመላው ጥቁር ህዝብ ፋና ወጊዎች ነን ብለን የምንኩራራበት አድዋ ከእሳቱ ነበልባል ለመከላከል ከቶ እንዴት አላስቻለንም?
 • ዜኖፎቢያ በሚባለው ዘመቻ ያለቁ ኢትዮጵያወያን እነማናቸው? ስንት ናቸው? ብሔራቸው? ሀይማኖታቸው? ቋንቋቸው ይታወቃል?
 • ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት በስንዴ ልመና የምንታወቅ ዜጎች ከመሆናችን ጋር ተያይዞ በመዝገበ ቃላት መፍቻ ላይ ሳይቀር ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ለፋሚን ወይም ለረሃብ መፍቻነት መዋሉ የአባቶቻንን ገድል ዘወትር እንደንተርክ ያደርገናል ወይስ?

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው አመት መጀመሪያ ላይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያለውን ጦርነት በተመለከተ ከኬኒያው ፕሬዚዳንት ጋር በስልክ መወያየታቸው በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት  ተዘግቧል፤ በማን ጉዳይ ነው አሜሪካ ማንን  የምታናግረው አላችሁ? አይግረምህ፤

አንገትህን የደፋህ ህዝብ ስለሆንክ አሜሪካ እኛን አልፋ በእኛ ጉዳይ የሌላ ሀገር መሪ  ብታናግር አይግረምህ፤ ነጭ ነጯን እንነጋገር ያለው ማን ነበር? /ነጭ ነጯን/

 • በወቅቱ የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ፤ የሌላ ሀገር መሪን ልታናግር አይገባም፤ ሉዋላዊነታችን መድፈር ነው እኛ የአድዋ ልጆች ነን! የሚል መግለጫ ያወጣል ብለህ ጠብቀህ ነበር? አትጃጃል፤ ቀለብ ሰፋሪን መናገር ጡር አለው!
 • አይግረምህ፤ ገና የየካ ክፍለ ከተማ ሊቀ መንበር አቶ አበበን እንጂ አቶ ከበደን ለምን አደረጋችሁ ትለናለች፤ለምን ተመፅዋችና አንገትህን የደፋህ ህዝብ ነሃ! ጥላሁን ገሠሠ እንዳለው ‹ከሌለህ የለህም›
 • በነገራችን ላይ ታላቁን የህዳሴ ግድብ እየገነባልን ያለው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ነው ፤ሳሊኒን እኛ ኢትዮጵያውያን መስራት ያቃተንን ግድብ እንዲሰራልን ቀጠርነው ወይስ ከ120 ዓመት በኋላም ባለንበት ቆመን ስለጠበቅነው እንደገና ሊያቀናን መጣ?
 • አድዋ ከእኛ አልፎ ለአፍሪካውያን የነፃነት ቀንዲል ያበራ ነው ብንልም ዛሬ ማንም ኢትዮጵያዊ ዘመዶቹን ጥየቃ ወደ ገጠር እግሩን ሊያነሳ የማይችልባት የነፃነት ቀንዲል ሀገር ላይ ነው ያለነው፤
 • ከጎንደር እስከ ሐረር፤ ከወልቂጤ እስከ ነቀምቴ፤ከመቀሌ እስከ ባሌ፤ከባህር ዳር እስከ ቀብሪዳሃር፤ከበሻሻ እስከ ሸገር ማምሻ ኖ ፍሪደም!
 • በጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕትነት ድል የተመታው ጣሊያን ቢሳካለት ኖሮ በግድ ቋንቋዬን ተማሩ ለማለት ነበር የመጣው፤ አሁን ነፃ ነን በምልበት ዘመን የአድዋ ድል ወራሽ የሆኑት  ልጆቻችን የግዴታ ቋንቋ እንዲማሩ ተፈርዶባቸዋል፤
 • በፖለቲካ አልበቃ ያለው ብሔርተኝነት መለኮታዊ የሆነውን ሀይማኖታዊ ቀኖናን በመሸንሸን በዘር መከፋፈል አልሳካ ሲል ምዕንምኑን በፆምና ፀሎት ሳይሆን ሊያስተራርደው ካራ የሚስሉ ምዕንመናንን የያዘች የነፃነት ቀንዲል መሆኗ ለማን አቤት ይባላል
 • በቅኝ ብንገዛ ኖሮ በራሳችን ቋንቋና ፊደል እንዳንማር እንደረግ ነበር፤ አሁንስ ነፃነት አለን ብለን በራሳችን  ቋንቋና ፊደል ነው ወይ  የምንማረው/ ከተሞቻችን ላይ የተሰቀሉ ማስታወቂያዎችን የንግድ  ስያሜዎችን ተመልከት፤ መንግስት  ራሱ መስሪያ ቤቶችን የሚሰይመው ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፤ሆርቲካልቸር ኢንስቲትዩት እያለ ነው፤ እንደ ሀገር የራሳችን ቋንቋና ፊደል አለን ብንልም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቀመው የላቲን ፊደልንእ ነው፤ እናስ ወዴት ነው ነፃነትህ?
 • እናስ? የአድዋው ትሩፋት የጣሊያን ቅኝ ገዢን በሀበሻ ቅኝ ገዢ መቀየር ነውን?
 • ከዚህ አንገት መድፋት ለመውጣት እንደ ህዝብና እንደ ሀገር ምን ማድረግ አለብን?
 • በመጀመሪያ ደረጃ ‹የዐድዋ ድል ሀገራችንን ማንም ሊያወርዳት ከማይችልበት ከፍታ ላይ ሰቅሏታል፤› ከሚለው ግብዝነት እንውጣ! አንገታችንን ከመድፋት ለመውጣት ምን እናድርግ?
 • ፖለቲካን ለፖለቲከኞች እንተው
 • ወጣቶች ስራ ሳትመርጡ ስሩ፤
 • ገበሬው እርሻውን ይረስ፤ ያምርት
 • ግንበኛው ገንቡን ብቻ ይስራ
 • አንፂው እንጨቱን ይጥረብ
 • መምህሩ ያስተምር
 • ነጋዴው ይነግድ
 • ተማሪ ስራው መማር ብቻ ይሁን፤ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ይቅሰም፤
 • የእጅ ሙያተኛው ብረት ይቆልምምና ማረሻ ይስራ
 • የሀይማኖት አባቶች ግብረ ገብ ያስተምሩ፤ ለሀገር ይፀልዩ
 • ሐኪሞች ህሙማንን ይርዱ
 • አርቲስቶች ፍቅርን ይዘምሩ ፤ሰው መሆንን ያስቀድሙ፤ ወዘተርፈ
 • ከ10 ዓመት በኋላ 137ኛውን ዓመት የአድዋ ድል በዓል ስናከብር እንደዘንድሮው አንገታችን እንዳንደፋ ዛሬ መሠረት እንጣል፤ በቁጭት እንነሳ፤
 • ያን ግዜ እኛም እንደ አፄ ምንሊክ ትውልድ ታሪክ ሰሪ እንሆንና በቀጣዩ ትውልድ እንዘከራለን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe