የአንድ ሙዚቃ ቡድን አባላት የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በአንድ ዝግጅት ላይ ያደረጉትን ንግግር በመተቸታቸው ለእስር ተዳረጉ።

ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ቅዳሜ ዕለት በተካሄደ የአንድ የቀድሞ ባለሥልጣን ባዘጋጁት ሥነ ሥርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር ረጅም እንደሆነ የተናገሩ ስምንት የሙዚቃ ቡድን አባላት ናቸው የታሰሩት።

ሙዚቀኞቹ ፕሬዝዳንቱን በሚተቹበት ጊዜ አጠገባቸው የነበረው ማይክሮፎን ክፍት ስለነበረ ንግግራቸው በሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች ተሰምቷል።

ይህንንም ተከትሎ የፕሬዝዳንቱ የደኅንነት አባላት የሙዚቃ ቡድኑ አባላትን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርገዋቸዋል።

ሙሴቬኒ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አማማ ምባባዚ የጋብቻ በዓላቸውን 50ኛ ዓመት ባከበሩበት ጊዜ ያደረጉትን ንግግር ረጅም ነው በማለታቸው በፕሬዝዳንቱ ላይ እንደ ተሰነዘረ ስድብ ተቆጥሮ ለእስር መብቃታቸውን የኡጋንዳ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።‘ክሬንስ ፐርፎርመርስ’ የተባለው የሙዚቃ ባንድ አባላት የፕሬዝዳንቱ ንግግርን ረጅምነት በማንሳት ሲያብጠለጥሏቸው እንደነበር የአገሪቱን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ምንጮችን ጠቅሰው የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የባንዱ አባላት “የተንዛዛ ንግግር፣ ደከመን እኮ፣ መናገሪያውን ለምን አይለቁም” በማለት ፕሬዝዳንቱን ተችተዋል ተብለው ነው የታሰሩት።

ሙዚቀኞቹ በዋና ከተማዋ ካምፓላ ውስጥ በሚገኝ ማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱን በመስደብ ክስ እንደተመሠረተባቸው የፍርድ ቤት መዝገብን ጠቅሰው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ነገር ግን የሙዚቃ ቡድኑም ሆነ ፖሊስ ስለጉዳዩ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

የኡጋንዳ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ንግግር እያደረጉ የባንዱ አባላት ትችት መሰማቱ በተሰብሳቢው ሕዝብ መካከል ድንጋጤን ፈጥሯል።

ለፕሬዝዳንቱ ጥበቃ የሚያደርገው የኡጋንዳ ልዩ ኃይል አባል የሆኑት ሌተናል ቶኒ ኮማኬች የባንዱ አባላት ተገቢ ያልሆነ ንግግር ሲያደርጉ መመልከቱን ገልጿል።

“ወዲያው የደኅንነት አባላት ፕሬዝዳንቱን የሰደቡትን የባንዱን አባላት ከበቡ። የባንዱ ኃላፊ ጎርደን ካዮቩ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ ነው” በማለት የደኅንነት ምንጮች ተናግረዋል።

በሙዚቀኞቹ ላይ ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒን በመስደብ በሚል እሁድ ዕለት የክስ መዝገብ የተከፈተ ሲሆን፣ ፖሊስ የተከሳሾች እና የምስክሮችን ቃል መቀበሉን አስታውቋል።