የኢራን የበላይ መሪ አሊ ካሚኒ ባልተለመደ ሁኔታ በኢራን አብዮት በዓል ላይ አለመገኘታቸው መነጋገሪያ ሆነ፡፡
በየዓመቱ የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ የሚከበረው የኢራን አብዮት መታሰቢያ ዝግጅት ላይ ባልተለመደ ሁኔታ የኢራን የበላይ መሪ አሊ ካሚኒ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡
በእርሳቸው ምትክ የኢራን ጦር የበላይ አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጀነራል አብዶክራሂም ሚሳቪ ክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በኢራኑ የበላይ መሪ ምትክ በበዓሉ ላይ የታደሙትን የተለያዩ ወታደራዊ አዛዦችን ያገኙት ሚሳቪ በንግግራቸው ላይ ከአሜሪካ ጋር ሊኖር ስለሚችል ግጭት በማንሳት ቀጠናዊ ጦርነት ለመጀመር ምንም ፍላጎቱ የለንም ብለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ቀናት ሳምንታት ተቃዋሚዎች አያቶላህ አሊ ካሚኒ ከስልጣን እንዲወርዱ እና በህዝባዊ አብዮት የመጣውን የእስላማዊውን ሪፐብሊክ አገዛዝ እንዲያበቃ ሲጠይቁ ነበር፡፡
በኢራን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለሳምንታት በተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ በርካቶች ሲታሰሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መገደላቸው አይዘነጋም፡፡//

