የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ ፦ ‹‹እውነቱን ለመናገር ኢቢሲን መምራት ተግዳሮቱ ቀላል አይደለም››

 ‹‹ችግር የለም ብዬ መደፋፈን አልፈልግም››

ከተመሰረተ 58 ዓመታትን ያስቆጠረውን የገሀሪቱን ብሔራዊ የሚዲያ ተቋም የሚመራው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በተለያዩ ዘመናት በተለያ ስያሜዎች ሲጠራ ኖሯል፡፡ ከ50 ዓመታት በኋላ የራሱን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ህንፃ አስገንብቶ ስርጭቱን የጀመረው ጣቢያው ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ የወጣበትን ስቱዲዮዎች አስገንብቶ ለስራ ዝግጁ በማድረግ በኩል የአንበሳውን ድርሻ የተወጣው የ36 አመቱ  የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ እንደ ህንፃው ሁሉ በጣቢያው ላይ የይዘት በለውጥ ለማምጣት‹ እንጥራለን› ይላል፡፡ ካለፉት 14 ዓመታት የስራ ልምዱ 13 ዓመቱን በትምህርትና በስራ ማሳለፉን የሚገልፀው አቶ ፍስሃ ‹‹ሚዲያን መምራት ከባድ ስራ ነው፤ ኢቢሲ ደግሞ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉበት አይቻለሁ፡፡ ግን ደግሞ ያንን ተግዳሮት አልፎ ትንሽ ለውጥ ማምጣት ከተቻለ ትልቅ ነገር መሆኑን ተመልክቻለሁ›› ይላል፡፡ ሰሞኑን ከተመረቀው የኢቢሲ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጋር በተያያዘ ስለ ገንዘብ አሰባሰቡ ግልፅነት፤ ስለሚያው ነፃነትና ተግዳሮቶች፤ በሎጎው ላይ ስለነበረው የኢትዮጰያ ባንዲራ ፤ ሰለ ኢትዮጵያ አይዶል ዳኛ መባረር፤ የአየር ሰአት ወስደው ስለሚሰሩ የመንግስት ተቀማት፤ ስለ ለተዘነጋው የኢትዮጵያ ራዲዮ ጣቢያና ስለ በጀት ምንጩ ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡

ቁም ነገር ፦ ኢቢሲ የዚህ ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ባለቤት እንዲሆን ያደረገው ሰው አቶ ፍስሃ ማነው ?

አቶ ፍስሃ፦ ተወልጄ ያደኩት አርሲ ነገሌ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ 230 ኪሎ ሜትር ከሻሽመኔ አጠገብ ማለት ነወ፡፡ የአንደኛ ደረጃም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩትም እዚያ ነው፡፡12ኛ ከፍልን ብቻ የተማርኩት ደብረብርሃን መጥቼ ነው፤

ቁም ነገር ፦ እንዴት መጣህ ደብረብርሃን?

አቶ ፍስሃ፦ ቤተሰቦቼ የሰሜን ሸዋ መራቤቴ ሰዎች ናቸው፡፡ ደብረብርሃን የመጣሁት አጎቴ ጋር ነው፡፡ 12ኛን ሃይለማርያም ማሞ ተምሬ እንደጨረስኩ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገብቼ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በሳይኮሎጂ አግኝቻለሁ፡፡

ቁም ነገር ፦ስራስ?

አቶ ፍስሃ፦ የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንደያዝኩ ቀጥታ የገባሁት ኢንሳ ነው፡፡ ኢንሳ አራት አመት ሰርቻለሁ፡፡ ማስተርሴን የያዝኩት ኢንሳ እየሰራሁ ነው፡፡

ቁም ነገር ፦ በምን ሙያ ኢንሳ ገባህ፤ አንተ ሳይኮሎጂ ነው የተማርከው?

አቶ ፍስሃ፦ኢንሳ እንደተቋቋመ የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎችን ነው ያሰባሰበው፡፡ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰሩ፤ዳታ አናሊስስ የሚሰሩ፤ የሶሻል ሳይንስ፤ ፖለቲካል ሳይንስ፤ ሶሺዮሎጂ ወዘተ በጣም የተለያየ ሙያ ያላቸው ልጆች ነበሩ፤ እኔም የገባሁት ከእነዚ ውስጥ አንዱ ሆኜ ነው፡፡አሁን በተለያየ የመንግስት የስራ ሀላፊነት ላይ የምታያቸው ሰዎች ያኔ እዛ የነበርን ነን፤

ቁም ነገር ፦ መቼ ማለት ነው?

አቶ ፍስሃ፦ እንደተቋቋመ ከ1999 እስከ 2002/03 በጣም የተደራጀበት ወቅት ነው፡፤ ያን ግዜ ዶክተር አብይ አመራር የነበሩበት ወቅት ነው፡፡እና ኢንሳ እየሰራሁ ነው ከዚያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በሶሻል ሳይኮሎጂ የማስተርስ ዲግሪ ያገኘሁት፡፡ በነገርህ ላይ ላለፉት 14 ዓመታት በስራ ላይ ነኝ፤ ከዚህ ውስጥ ለ13 ዓመታት ያህል በትምህርት ላይም ነበርኩ፤

ቁም ነገር ፦እንዴት?

አቶ ፍስሃ፦ስራ እየሰራሁ እማራለሁ፡ ፡ አሁንም ትምህርት ላይ ነኝ ለ3ኛ ዲግሪዬ፡፡ ከሳይኮሎጂው ሌላ በኢኮኖሚክስ ሌላ ዲግሪ አለኝ፡፡ ከሶሻል ሳይኮሎጂው ማስተርስ ሌላ በገቨርመንት ኢኮኖሚክስም ሌላ ማስተርስ ሰርቻለሁ፡፡ላለፉት አራት ዓመታት ደግሞ የዶክትሬትዲግሪዬን እንግሊዝ ሀገር ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ አሁን የቀረኝ የጥናት ስራዬን ማስገባት ብቻ ነው፤መስከረም ላይ እሱም ይጠናቀቃል ብዬ አስባለሁ፡፡

ቁም ነገር ፦ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ነው ይሄ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ተሰርቶ የተጠናቀቀው፤ ያ ደግሞ ያንተን የዕለት ተዕለት ክትትል የሚፈልግ ነበር፤ እንዴት ነው በዚህ ውስጥ ሆነህ የዶክትሬት ዲግሪ ለመማር

የቻልከው?

አቶ ፍስሃ፦ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡የዶክትሬት ዲግሪው ትምህርት እንደእኛ ሀገር አይደለም፡፡ የተወሰነ 15 ቀን ያህል እዛ ሄጄ ከተከታተልኩ በኋላ በአብዛኛውን የምርምር ፅሑፎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ትምህርቱን የጀመርኩት የዛሬ አራት ዓመት ወደዚህ ስራ ሳልመጣ ነው፡፡ በምርምር ስራዬ ዋና ዋና የሚባሉ የዳታ ስብስብ ስራዎችን የሰታሁት ኢቢሲ ከመምጣቴ በፊት ነው የጨረስኩት፡፡እዚህም ከመጣሁ በኋላ እየሰራሁ ነበር፤ ባለፈው አንድ ዓመት ከጠዋት እስከ 10 ሰዓት ድረስ የድሮው ቢሮአችን ነበር የምውለው፤ ኤዲቶሪያል ስብበባ ከጨረስኩ በኋለ ወደእዚህ ነበር የምመጣው ግንባታውን ለመከታተል፡፡የትምህርቱን ጉዳይ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ ነው የምሰራው፡፡ የሰው ልጅ ለትምህርቱም ለስራውም ሰዓቱን በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን እስካዘጋጀ ድረስ የማይቻል ነገር የለም ፡፡ባይሆን የመዝናኛ ሰኣትን መቀነስ ብቻ ነው የሚጠበቀው፡፡/ሳቅ/

ቁም ነገር ፦የዶክትሬት ዲግሪህ የምትሰራው በምን ዘርፍ ነው?

አቶ ፍስሃ፦ዲፊንስ ሴኩሪቲ ላይ ነው ፋካሊቲው፡፡ የመመረቂያ የጥናት ስራዬ ደግሞ እንደእኛ ባለ በልማት ታዳጊ ሀገራት ላይ የልማታዊ መንግስት የእድገት መንገድ ዘላቂ ነው ወይ? የሚለውን የሚፈትሽ ነው፡በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ ብዝሃ ብሔርና ቋንቋ ባለበት እንደእኛ ሀገር የልማታዊ መንግስት ስትራቴጂ ያስኬዳል ወይ?የሚለው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

ቁም ነገር ፦በየትኛው ‹‹ልማታዊ›› መንግስት ላይ የሚያተኩር ነው?

አቶ ፍስሃ፦ ከኢህአዴግ ጀምሮ እስከ ምርጫው ድረስ ያለውን የብልፅግና መንግስት የልማት አቅጣጫዎች ነው የምፈትሸው፡፡

ቁም ነገር ፦የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነህ እንድትሰራ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረህ ማነው?

አቶ ፍስሃ፦ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡

ቁም ነገር ፦መቼ?

አቶ ፍስሃ፦ከምርጫው በኋላ የተደረገው የመንግስት ምስረታ ዕለት ከሰዓት በኋላ ነው ነገሩኝ፡፡ በማግስቱ

ቢሮ ሄጄ ከዶ/ር ንጉሴ ጋር ስራ ተረካክበን በማግስቱ ስራ ጀመርኩ፡፡

ቁም ነገር ፦በአንድ ቀን አቶ ፍስሃ፦በአንድ ቀን፡፡ ባይገርምህ የእዚኑ ዕለት ኤዲቶሪያል ስብሰባ መርቻለሁ፡፡

ቁም ነገር ፦የምትጠብቀው ሹመት ነበር?

አቶ ፍስሃ፦ኢንሳ የነበርኩ ጊዜ የመረጃ ትንተና ላይ ነበር የምሰራው፡፡ከእዛ በኋላ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የመረጃ ማዕከል እንደ ዳይሬክተር ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ አሁን ወደ እዚህ ሀላፊነት ከመምጣቴ በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የወቅታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሆኜ ነበር የምሰራው፡፡ከዚህ አንጻር ሚዲያ ውስጥ ባልሰራም ከሚዲያና ከኮሚኒኬሽን ጋር ቅርበት ነበረኝ ለማለት እችላለሁ፡፡ወቅቱ መስከረም ላይ የመንግስት ምስረታ የሚካሄድበት ወቅት ስለነበር የተለያዩ መስሪያ ቤት ሀላፊዎች የሚቀያሩበት ወቅት ስለነበር የሆነ አዳዲስ ቦታዎች ብዙ ነበሩ፡፡ በመሆኑም በዚህ ምደባ መሠረት ማን የት ቦታ ቢሆን የተሻለ አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል ተብሎ የተሰጠኝን ቦታ ተቀብያለሁ፡፡

ቁም ነገር ፦ ግን ልመራው እችላለሁ ወይ ብለህ ራስህን አልጠየቅህም?

አቶ ፍስሃ፦ያስፈራል፤ ትልቅ ሚዲያ ነው ኢቢሲ፡፡ በእዛ ላይ ብሔራዊ የሚዲያ ተቋም ነው፡፡ ስለተቋሙም ብዙ ነገሮች ይባላሉ፡፡አንዳንድ ሰዎች እንደውም ወደእዚህ መስሪያ ቤት እንደተመደብኩ ሲያውቁ ‹እንኳን ደስ ያለህ ሳይሆን ያሉኝ እግዚአብሔር ይሁንህ› ነው፡፡ አንድ ወዳጄ ምን አለኝ መሰለህ? ሚዲያን መምራት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሚዲያን መምራት ማለት እንደ እግር ኳስ አሰልጣኝ ወይም እንደ ፈንጂ አምካኝ ሙያ ነው አለኝ፡፡ እግር ኳስ አስልጣኝ ብዙ ጨዋታ አሸንፎ ዋንጫ ወስዶ አንድ ቀን ቢሸነፍ የሚደርስበትን ትችት ታውቀዋለህ፡ ፡ ፈንጂ አምካኝም መሳሳት የማይችል ሰው ነው፡፡ ከተሳሳተ ስህተቱን ለማረም አይችልም፡፡ ልክ እንደ እዛ ሁሉ ሚዲያ ላይም ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ሰርተህ ያንን ሁሉ በአንድ ቀን ስህተት ልትደመስሰው ትችላለህ፡፡ እና ሚዲያ መምራት በጣም ከባድ ስራ ነው፡፡ ብዙ አማራሮች ከሀላፊነት የተነሱት በእንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየሰሩ ነው፡፡ጋዜጠኞቹ ለሚሰሩት ስህተት ሃላፊነቱን የሚወስዱት አመራሮቹ ናቸው፡፡ እና ኢቢሲ ስመጣ ተግዳሮቶች እንዳሉ አይቻለሁ፡፡ ግን ደግሞ ያንን ተግዳሮት አልፎ ትንሽ ለውጥ ማምጣት ከተቻ ትልቅ ነገር መሆኑን ተመልክቻለሁ፡፡

ቁም ነገር ፦ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህንፃው ምረቃ እለት ‹ኢቢሲ ስፒከር አይደለም› ብለው ነበር፤ የህንጻውና መሳሪያዎቹ መሟላት አንድ ነገር ሆኖ ሚዲያ የሚለካው በይዘቱ ነው፤ ከዚህ አንፃር ኢቢሲ ስፒከር ሆኖ ላለመቀጠሉ ምን እቅድ አለው?

ምረቃ

አቶ ፍስሃ፦በእኔ እምነት ሚዲያ በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ በሆነ መልኩ እየተቀየረ ነው፡፡ ይህ ለውጥ ለኢቢሲ ብቻ ተብሎ የመጣ ሳይሆን አጠቃላይ ቴክኖሎጂው ይዞት የመጣው እውነታ ነው፡፡ ከዚህ ለውጥ ጋር ራስን አስማምቶ መጓዝ አማራጭ የለውም፡፡በዚህ ውስጥ ኢቢሲ ውድድሩን ለማለፍ እንደተባለው ይዘት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የተመልካችንና የአድማጭን ቀልብ ለሚይዝ ይዘት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከህንጻውና ከመሳሪያዎቹ ውጭ የተለያዩ የይዘት ለውጦችንና አቀራረቦችን በመዝናኛው፤ በዜናው፤ በስፖርቱና በሌሎቹ ይዘቶቻችን ላይ ለውጥ እያመጣን ነው፡፡ ድራማዎቻችንና የታለንት ሾዎቻችን በርካታ ተመልካቾን እየሳቡ ነው፤ ይህንን በሚገባ ማስቀጠል ከቻልን ኢቢሲ ስፍራውን ያገኛል፤ ተመልካችም አድማጭንም መያዝ እንችላለን ብዬ አምናለሁ፡፡ለዚህ ቀን ከሌሊት እንሰራለን፤ ፈራጁ ህዝብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖማለት ነው፡፡

ቁም ነገር ፦ለውጦች እየታየ ነው፡፡ ከኢቢሲ የሚጠበቀው ግን ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዩች ላይ ምን ለውጦች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኢቢሲ ተመርቆ ስራ በአዲሱ ስቱዲዮ ስራ ከጀመረ አንድ ወር ሆኖታል፤ በዚህ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የህዝብ ድምፅ መሆኑን ሊያሳይ የሚችል ምን ስራ ተሰርቷል?

አቶ ፍስሃ፦እውነቱን ለመናገር ተግዳሮቱ ቀላል አይደለም፡፡ቀላል ነው፤ ችግር የለም ብዬ መደፋፈን አልፈልግም፡፡ አንዳንድ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የእነርሱ ህዝብ ግንኙነት እንድትሆን ነው የሚፈልጉት እንጂ የራስህ ነፃነት ያለህ ተቋም አድርገው አይመለከቱትም፡፡በተለይ የምርምራ ስራ ለመስራት ገና ስልክ መደወል ስትጀምር ሊያስቆሙህ ይፈልጋሉ፡፡ጫና አለው፡፡ፈተናው የመንግስት ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆን የሚመጣው ከግል ድርጅቶችም ነው፡፡ እኛ በአሁኑ ወቅት ገቢያችንን የምንችለው ከማስታወቂያና ከስፖንሰር ሽፕ ነው፡፡አንድ ነገር ዘገባ ስንሰራ ማስታወቂያውና ስፖንሰሩን የሰጡ ድርጅቶች ይደውላሉ፡፡

ቁም ነገር ፦ በራሳችን ገቢነው የምንተዳደረው ስትል ከመንግስትምንም በጀት አታገኙም?

አቶ ፍስሃ፦ 90 ከመቶ በራሳችን ወጪ ነው የምንተዳደረው፤ ደሞዛችንን ጨምሮ፡፡ መንግስት የበጀት ጉድለት እንዳለብን ስለሚያውቅ ለካፒታል በጀት የተወሰነ በጀት ይሰጠናል፡፡ ከእዛ ውጭ የ4ራ ማስኬጃና ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን የዓመት የሠራተኞች የደሞዝ ወጪያችንን ራሳችንን ነን የምንችለው፡፡ ከዚህ አንፃር ፈተናው ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከግሉም ዘርፍ ይማጣል፡፡በተለይ ግጭት ሀገሪቱ ላይ ሲኖር ሁሉም ጣቱን የሚጠቁመው እኛ ላይ ነው፤ ያም ሆኖ ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁመን የምሰራቸው ብዙ ስራዎች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ እኔ እንኳን ከመጣሁ በርካታ የመንግስት አመራሮችን ከስራ ያስነሱ የምርመራ ዘገባዎች ሰርተናል፡፡ያንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ያ ማለት ግን እኛ የህዘብ ሚዲያ ነን፡፡ እንደ ትግል ሚዲያዎች ወይም እንደ ማህበራዊ ሚዲያው አንድ ነገር ሲፈጠር ለማራገብ አንችልም፡፡ ሀላፊነት አለብን፡፡ ተልእኮአችን ግልፅ ነው፡፡

ቁም ነገር ፦ ሚዲያው የህዝብ ነው ይባል እንጂ በህግ እውቅና አግኝትው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች መድረክ አይሰጥም፤ ለምሳሌ ባለፈው አንድ ወር እንኳ ወደ ስደስት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫዎችን አውጥተዋል፤ አንዱም ግን በእናንተ ሚዲያ አልተዘገበም፤ ለምንድነው?

አቶ ፍስሃ፦ በዚህ አንድ ወር ውስጥ ጣቢያው ስራ የጀመረው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፖርቲዎችን በማነጋገርና ራሳችንን በማስተቸት ነው፡፡ እንዲተቹን በራችንን ከፍተን ለህዝብ ያሉትን አስተላልፈናል፡፡ መግለጫን በተመለከተ እኛ ሽፋን ለመስጠት እንፈልጋለን፡፡ ግን አይነግሩንም መቹና የት መግለጫ እንደሚሰጡ፡፡ለምን እንደሆነ አላውቅም፤ ለምሳሌ ኢዜማ በፖሊሲ ጉዳዩች ላይ ውይይቶችን ያካሂዳሉ፡፡ ግን አይነግሩንም፡፡ ቢነግሩን ውይይቱን ቀርጸን ለህዝብ እናቀርባልን፡፡እኔ ራሴ ደውዬ ለምንድነው እንደዚህ አይነት ነገር ስታዘጋጁ የማትነግሩን ብዬ እስከመጠየቅ ደርሻለሁ፡፡

ቁም ነገር ፦ ግን ምን ጥሪ ያስፈልጋል፤ በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቲውተር ገፅ መልዕክቶች ዜና እየሆኑ ነው፡፡ ታዲያ የፖለቲካ ፖርቲዎቹ በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ዜና አይሆኑም? አቶ ፍስሃ፦ሊሆን ይችላል፤ እንዳገኘን ሽፋን ልንሰጥ እንሞክራለን፡፡ ግን ደግሞ ማንም የፖለቲካ ፖርቲ መግለጫ ስላወጣ ዝም ብለን ዜና እናደርገዋለን ወይ ብለን እንጠይቃለን፡፤ የዜናው ክብደት ዎርዚ ነው ወይ? ብለኝ እንጠይቃለን፡፡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ መግለጫ ስላወጣ እሱን ዝም ብለን ለመዘገብ ያስቸግራል፡፡

ቁም ነገር ፦የብልፅግናን መግለጫና ስብሰባ ትዘግቡ የለ?

አቶ ፍስሃ፦ብልጽግና እኮ የመንግስት ስልጣን የያዘ ፖርቲ ነው፡፡ የፖርቲው ማንኛውም ውሳኔ በህዝቡ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ አለው፡፡ ምንም የምክር ቤት መቀመጫ የሌለው ፖርቲን አኩል አድርገን መግለጫውን ልናቀርብ አንችልም ፡ እናድርግ ብንልም ስንት የፖለቲካ ፖርቲ ነው እዚህ ሀገር ያለው? ቀኑን ሙሉ መግለጫ ስናነብ ልንውል ነው፡፡

ቁም ነገር ፦ወቅታዊ በሆኑ የህዝብ ጉዳዩች ለምሳሌ የሸገር ከተማ ነዋሪዎች መፈናቀል፤ ሰሞኑን ደግሞ በጉራጌ ዞን ያገጠመውን ግጭት ወዘተ እንዳላየ ነው የምታልፉት፤ ለምንድነው?

አቶ ፍስሃ፦ እኛ ተልዕኮ ያለን ሚዲያ ነን ብያለው፡፡ አንድ ነገር ሲከሰት እንደሌሎች ማራገብ ላይ አናተኩርም፤ ለምሳሌ የሸገር ከተማ መፈናቀልን በተመለከተ ጥናት አድገን ከንቲባውን ስቱዲዮ ጠርተን ሞግተናል፤

ቁም ነገር ፦ተፈናቃዮቹን ግን አላናገራችሁም?

ሎጎ

አቶ ፍስሃ፦ ከንቲባውን ያነጋገርነው እኮ ቦታው ድረስ ሄደን ምንድነው የሆነው? የሚለውን አይተን የሚመለከታቸውን ተፈናቃዮች አነጋግረን ነው የሞገትነው፡፡መፍትሄ ለማምጣት ከሆነ መረጃ መሰብሰብ ያስፈልገናል፡፡ ጋዜጠኞች አሰማርተን ያንን ይዘን ነው ስራውን የሰራነው፡፡ በከተማችን ውስጥ ያለውን የወንጀል ጉዳይ፤የኮንዶሚኒየም፤ የመሬት ዘረፋ፤ የትራንስፖርት እጥረት፤ የማዳበሪያ የትራክተር ችግር በዚህ መልኩ ነው የሰራነው፡፡ በቂ ነው ወይ? ካልከኝ በቂ አይደለም፤ ግን ጥሩ ጅማሬዎች አሉ፡፡ እንደውም በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ካሉ ሚዲያዎች መሀከል መንግስትን የሚተች የስራ ሃላፊዎችን የሚያጋልጥ የምርምራ ዘገባ በመስራት የኢቲቪን ያህል ማንም የለም ልል እችላለሁ፡፡

ቁም ነገር ፦የህንፃ ግንባታው ጋር በተያያዘ የነበረው የገንዘብ ማሰባሰብ ምን ያህል ግልፅነት አለው? ማን ምን ሰጠ የሚለውን ህዝብ የማወቅ መብት አለው?

አቶ ፍስሃ፦ኢቢሲ ይህንን ህንጻ ለመስራት ከተለያዩ ተቀቋማት ገንዘብ ሰብስቧል፡፡ ግን ተቋማቱ ስጦታ አይደለም የሰጡን፡፡የቢዝነስ ስምምነት ነው ያለን፡፡ምሳሌ አራቱ ተቋማት ስቱዲዮ አሰርተውልናል፡፡ ትልቁን ገንዘብ የሰጠን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው 200 ሚሊዮን ብር፤ የዜና ስቱዲዮውን ገንብተንበታል፡፡ለዚህ እኛ ደግሞ በውል የታሰረ በሚወቀጥለው አንድ ዓመት የማስታወቂያና የዶክመንተሪ ስራዎችን እንሰራላቸዋለን፡፡የሰጡትን 200 ሚሊዮን በዚህ መልኩ ይጠቀሙበታል፡፡ በፊት ማስታወቂያ አስነግረው ነበር የሚከፍሉት፤ አሁን በቅድሚያ ለግንባታ መስሪያ ሰጡን ማለት ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌ ኮም የቋንቋዎች ስቱዲዮን ማሰሪያ ሰጥተውናል፡፡

ቁም ነገር ፦ስንት ከፍለው?

አቶ ፍስሃ፦ 150 ሚሊዮን ነው የከፈሉት፡፡ እነርሱም በተመሳሳይ የ150 ሚሊዮን ብር ማስታወቂያና የዶክመንተሪ ስራ ይሰራላቸዋል፡፡ መድን ድርጅትም 150 ሚሊዮን ብር በመስጠት የመዝናኛ ስቱዲዮውን ሰርተንበታል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድርም በ40 ሚሊዮን ብር የህፃናት ቻናል ስቱዲዮ መስሪያ ሰጥተውናል፡፡ሁሉም በነጻ አይደለም የሰጡን ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህንን ሰፊ 11 ሄክታር ላይ ያረፈ ግቢ ስንረከብ መንግስት ሲሰጠን ለግንባታው ተብሎ የታያዘ በጀት የለንም፡፡ በጀቱን በራሳችን መንገድ መፈለግና መስራት ነበረብን፡፡ ያንን ነው ያደረግነው፡፡

ቁም ነገር ፦ገንዘብ የሰጡ ተቋማት ተፅኖአቸውንስ እንዴት ልትቋቋሙ ነው?

አቶ ፍስሃ፦ትክክልኛ ጥያቄ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህን ያህል ገንዘብ አፈላልገን ባንሰራ ይሄ ጥያቄ አይመጣም ነበር፡፡ያም ሆኖ ግን ቀደም ሲል እንደገለፅኩልህ ተቋማቱ በነጻ የሰጡን ገንዘብ የለም፤ ስለዚህ ነፃነታችንን ጠብቀን በሀላፊነት ስሜት መስራት ያለብንን ነገር ነው የምንሰራው፡ ፡ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ላይ በርካታ የምርመራ ዘገባዎች እንደሰራለን፡፡ በመሬት በኮንዶሚኒየም ጉዳይ በሙስና ላይ እንሰራለን፡፡ ለምን ብለው ጠይቀውን አያውቁም፡፡ ሌሎቹ ላይም መስራት ያለብንን ነገር እንሰራለን፡፡

ቁም ነገር ፦የቢዝነስ ስምምነት ላይ የተመሰረተ ከሆነ ሌሎች የግል ተቋማት ተጠይቀዋል ተመሳሳ እድል እንዳለና እንደሚሰጣቸው?

አቶ ፍስሃ፦ ግንባታው በሚካሄድበት ወቅት በርካታ የግልና የመንግስት ተቋማት የስራ ሃላፊዎችን እየጠራን እኔ ራሴ ምሳ እየጋበዝኩ ጥያቄ አቀርቤያለሁ፡፡ ሁኔታውን ተረድተው ሀሳቡ ገብቷቸው የተሻለ ኦፈር የሰጡን እነዚህ ተቋማት ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ሌሎች የምሰራቸው ስቱዲዮዎች አሉን፡፡ ከመጡ እንቀበላቸዋለን ፍላጎቱ ያላቸው ካሉ፡፡

ቁም ነገር ፦ ግን የግል ድርጅቶች ምንም ተሳትፎ የላቸውም ማለት ነው?

አቶ ፍስሃ፦እንደሌሎቹ ስቱዲዮ ማሰሪያ አልሰጡም እንጂ ስምምነት ያደረጉ የግል ድርጅቶችም የመንግስት ተቋማትም አሉ፡፡

ቁም ነገር ፦ለምሳሌ?

አቶ ፍስሃ፦ለምሳሌ በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ፤የቤቶች ኮርፖሬሽን፤በርካታ የግል ባንኮች፤ ግብርና ሚኒስቴር፤ ገቢዎች ሚኒስቴር፤ ብዙዎቹ በማስታወቂያ ታሳቢ የሚደረግ ገንዘብ ሰጥተውናል፡፡

ቁም ነገር ፦በድምሩ ምን ያህል በጀት እንደተሰራ ይታወቃል?

አቶ ፍስሃ፦አሁን የነገርኩህን እንደምረው?/ሳቅ/ ስቱዲዮ ካሰሩልን ተቋማት ብቻ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስበናል፡፡ይሄ ለግንባታ የዋለ ነው፡፡ ሌላ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚሆነው ደግሞ ለቴክኖሎጂው ግንባታ የዋለ ነው፡፡ በአጠቃላይ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ወጥቶበታል ፡፡

ቁም ነገር ፦ የተለመደ የቢዝነስ ስምምነት ከሆነ ለተወሰኑ ተቋማት ሎጎ በየስቱዲዮዎቹ መግቢያ ላይ መስቀል ለምን አስፈለገ? ከሚዲያ ስነ ምግባር አንፃር ግቢ ውስጥም ጭምር ሎጓቸው መስቀል ለምን ተደረገ?

አቶ ፍስሃ፦እንግዲህ ሎጓቸው የት ላይ ነው የተሰቀለው የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ በዋናው የቴሌቪዥን መስኮት ላይ ሰቅለን ለህዝብ አላሳየንም፡ ፡ በስቱዲዮው በር ላይ ነው የ ተ ሰ ቀ ለ ው ፤ በዋናው ስርጭት ላይ ምርትና አገልግሎታቸውን ብቻ ሳይሆን ሎ ጓ ው ን ም ጭ ም ር እ ያ ስ ተ ላ ለ ፍ ን ግቢ ውስጥ ለምን ሎጓቸውን ሰ ቀ ላ ች ሁ የ ሚ ለ ው ችግር ያለው አይመስለኝም፡፡

ቁ ምነ ገ ር፦ በ ቴ ሌ ቪ ዥ ን እኮ ከፍለው ነው ለህዝብ የሚተዋወቅላቸው?

አቶ ፍስሃ፦ እዚህም እኮ ግቢ ውስጥ ላለው ከፍለዋል፡፡ ከእዛ የሚለየው የግቢውና የስቱዲዮው የሚታየው እዚህ በመጣ ሰው ብቻ ነው፡፡

ቁም ነገር ፦የኢትዮጵያ ራዲዮ አንጋፋ ጣቢያ ነው፤ ኤፍኤም አዲስ 97.1ም አንጋፋ ጣቢያ ነው፤ ይህ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ግን ትኩረቱ ቴሌቪዥን ላይ ብቻ ይመስላል፤ኢትዮጵያ ራዲዮ ለምሳሌ በደንብ አይሰማም፤በእዛ ላይ ይቆራረጣል፤ አዲስ አበባ ላይ በኤፍኤም ስርጭት ካልሆነ አይሰማም፤ ራዲዮ አልተረሳም ወይ?

አቶ ፍስሃ፦ ይሄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው ኢትዮጵያ ራዲዮ ያለው ማሰራጫ የቆየ ነው፡፡አንቴናዎቹም ቢሆን ረዥም እድሜ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ አጠቃላይ መሠረተ ልማቱ መቀየር አለበት፡፡ለራዲዮኖቹ በጣም ጥሩ ጥሩ ስቱዲዮዎች ሰርተናል በአዲሱ ሚዲያ ኮምፕሌክስ፡፡ ቴክኖሎጂዎችም እያስመጣን ነው፡፡ ግን እንደ ቴሌቪዥኑ ትኩረት ሰጥታችሁታል ወይ ካልከኝ አልሰጠነውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በኢቢሲ ውስጥ አምስት የቲቪ ጣቢያና ሶስት የራዲዮ ጣቢያ አለን፡፡ በዚህ ውስጥ ሁሉ ለሚሰሩ ሰራተኞች ደሞዝ መክፈል የቻልነው በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ገቢ ነው፡፡ ያም ሆኖ ለራዲዮ አሁን አዲስ ፕሮጀክት ቀርፀን ወደ ስራ እየገባን ነው፡፡ ራዲዮ ዲጂታላይዝ እየሆነ ነው፡፡ በአንድ ትራንስሚተር እስከ ስምንት ራዲዮ ጣቢያዎችን ለማስተላለፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ያንን በመጠቀም በቀላሉ በየቋንቋው ተደራሽ መሆን እንችላለን፡፡ ከዚህ በኋላ ዘመኑ የራዲዮ ይሆናል፡፡

ቁም ነገር ፦በመዝናኛው ቻናል ላይ ድራማዎችን በጋራ ፕሮውዲሰውስ እያድጋችሁ ጥሩ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ በዜና ቻናልስ ለባለሙያ ከፍላችሁ ቃለ መጠይቅ የምታደርጉት መቼ ነው?

አቶ ፍስሃ፦ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ስትጠይቅ ደስ ይለኛል፡፡ከዚህ በፊት እንዳከው ዝም ብለን ባለሙያዎችን ጋብዘን አነጋግረን ብቻ ነበር የምንሸኛቸው፡፡ አሁን ግን የተወሰኑ የተመረጡባለሙያዎችን በሆነ ሙያ ላይ እውቀቱ ያላቸው ሰዎችን ከፍለን ልናነጋግር ትንታኔ ልናሰጥ አቅደናል፤ በሌሎች ጣቢያዎች ላይም በአልጀዚራ በሲኤንኤን ላይ ይደረጋል፤እኛም ወደእዛ መሄዳችን የማይቀር ነው፤ግን ደግሞ ይሄም ቢሆን ገንዘብ እንደሚፈልግ መረሳት የለበትም፡፡

ቁም ነገር ፦ ኢቢሲ የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ጣቢያ እየሆነ ነው፤ለምሳሌ ንግድ ባንክ የአየር ሰዓት ወስዶ የራሱን ስኬቶች ያቀርባል፤ ውጭ ጉዳይ የአየር ሰኣት አለው፤ልማት ባንክ ተመሳሳይ ነው፤ ፌደራል ፖሊስ ፕሮግራም አለው፤ጤና ሚኒስቴር ወዘተ የት ላይ ነው ማቆሚያው?

አቶ ፍስሃ፦ትክክል ነው፤ ጣቢያችን ያንን ሲያፈደርግ ገንዘብ ያገኛል፤ ከእዛም በላይ ግን በጋራ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ዲፕሎማሲያችን

የሚል ፕሮግራም አለን፤ በጋራ ነው የምናቀርበው፡፡ በእነርሱ በኩል ሌላ ጊዜ የማናገናቸውን ዲፕሎማቶችና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን የተመለከተ መረጃዎች እናገኛለን፡ ፕሮግራሙን የምናዘጋጀው እኛ ነን፡፡ አቀራረቡ ላይ የህዝብ ግንኙነት ከመሰለ ግን ድክመቱ የእኛ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በጋራ የምንሰራቸው ስራዎች ላይ በይዘቱ ላይ ማንም ጣልቃ አይገባብንም፡፡

ቁም ነገር ፦በቅርቡ በጉማ የፊልም ሽልማት ላይ የተቃውሞ ድምፅ ያሰማችው ኢትዮጵያ አይዶል ላይ በዳኝነት እንደምትሰራ ያስተዋወቃችኋት ልጅ/ፍላጎት አብርሃም/ ፕሮግራሙ ሲጀምር የለችም፤ምነው?

አቶ ፍስሃ፦ለኢትዮጵያ አይዶል ላይ እንዲሰሩ ካናገርናቸው ዳኞች መሀከል አንዷ ልጅ ነበረች፡፡ብዙ ዳኞች አሉን፡፡ ፕሮግራሙን ልንክፍት ስንል ልጅቷ ምን እንደተፈጠረ በማናውቀው ምክንያት ስልኳን ዘግታ ጠፋች፡፡ ስልኳ ስላልሰራ ብለን የፕሮግራሙን መክፈቻ ቀን ልንቀይረው አንችልም፡፡ ስለዚህ ባሉት ዳኞች አስጀምረነዋል፡፡ ግን በዚህ አጋጣሚ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ከፖለቲካ ከሀይማኖትና ሌሎች መሰል ነገሮች ነፃ እንዲሆኑ እንፈልጋልን፡፡በተለይ ዳኛ ሆነው የሚሰሩ ሰዎች ነፃ ቢሆኑ ጥሩ ነው ብለን እናምናለን፡፡ የኢትዮጵያ አይዶል የሚዳኘው በዳኞች ብቻ ሳይሆን በህዝብም ነው፡፡ ስለሆነም ፖለቲካ ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ቅሬታ ያለው ሰው ጉዳዩን ከሌላ አጀንዳ ጋር እንዲያይዘው ስለማያስፈልግ በተቻለ መጠን ዳኞቻችንን ከፖለቲካ ወገንተኝት የፀዱ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡

ቁም ነገር ፦ግን እኮ ከዳኞቻችሁ መሀል አንዱ የምክር ቤት የአባልና የብልፅግና አባል ነው፤

አቶ ፍስሃ፦ማን?

ቁም ነገር ፦ ነብዩ ባዬ፤

አቶ ፍስሃ፦ነብዩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል መሆኑን አውቃለሁ፡፡ የብልፅግና አባል

ግን አይደለም፡፡ ምክር ቤት ከገቡ የብልፅግና ተመራጮች መሀከል የብልፅግና አባል ያልሆኑ ብዙ ተመራጮች አሉ፡፡

ቁም ነገር ፦ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሎጎ የድሮው ጎጆ ቤት ሆኗል፤ቀደም ሲል የነበረው የኢቢሲ ሎጎ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያለበት ነበር፤ ባንዲራውን ማጥፋት ለምን አስፈለገ?

አቶ ፍስሃ፦ አሁን ያለው ሎጎ አዲስ አይደለም፤ ላለፉት 50 ዓመታት ቴሌቪዥን በሚያይ ሰው አእምሮ ውስጥ ያለ ሎጎ ነው፡፡ሎጎው ደግሞ በደንብ ታስቦበት ትርጉም እንዲሰጥ ተብሎ የተሰራ ሎጎ ነው፡፡ በዚያ ዘመን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጎጆ ውስጥ እናስገባለን የሚል መልዕክት ነው ያለው፡፡ ይህንን በጣም ፈጠራ የታከለበትና ብዙ ሰው የሚያውቀው ሎጎ የተቀየረበት መንገድ በደንብ ውይይት የተደረበት አልነበረም፡፡ ስለዚህ ወደ ነበርንበት ነው የተመለስነው፡፡ ህዝቡም አዲስ ሎጎ እንደመጣበት ሳያስብ ነው የተቀበለው፡፡ ምክንያቱ የሚያውቀው ሎጎ ስለሆነ ነው እንጂ ከባንዲራው ቀለም መቀየር ጋር ምንም ግንኙነት የለም፡፡ ባንዲራን በተመለከተ በግቢያችን ውስጥ ከኢትዮጵያ ባንዲራ አልፈን የአፍሪካ ህብረትን ባንዲራ ሰቅለናል፡፡

ቁም ነገር ፦አመሰግናለሁ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe