የኢቢኤስ ቴሌቪዥን መስራች አቶ አማን ፍስሐጽዮን ማነው ?

አቶ አማን ፍስሐጽዮን በተወለደ በ54 ዓመቱ የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ.ም በሚወዷቸው ቤተሰቦቹ ተከቦ  በዋሽንግተን ዲሲ ከዚህ አለም ድካም በሰላም አርፋል።

የባለራዕዩ፣ ስራ ፈጣሪው፣ ታማኝ ባለትዳር፣ መልካም አባት እና የኢትዮጵያ ኩሩ ልጅ የሆነው አቶ አማን ህይወት እና ማንነቱ በእምነት፣ በቁርጠኝነት፣ በተስፋና በጽናት የተሞላ ነበር። በፈጣሪ ላይ በነበረው ጽኑ እምነትና ለወገኖቹ እና ለሀገሩ በነበረው የማይናወጥ ፍቅር ተመርቶ የሌሎችን እንባ ለማበስ፣ የተቸገሩትን ለመርዳት፣ በብዙሃን ፊት ላይ የፈገግታን ጸዳል ለማብራትና ሌሎችን ለማገልገል በፍጹም ቅንነት፣ በእውነተኛ ስብዕና እና በጽኑ አላማ እራሱን የሰጠ ታላቅ ሰው ነበር።

አቶ አማን ሐምሌ 3 ቀን 1964 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ከተማ ከአባቱ ከአቶ ፍስሐጽዮን ገብረሕይወትና ከእናቱ ከወይዘሮ ሕይወት ተኬ ተወለደ። ለቤተሰቡ ስድስተኛና የመጨረሻ ልጅ የነበረው አቶ አማን፣ እምነትን ማዕከል ባደረገ፣ የቤተሰብ እሴቶች በከበረበት ቤት ውስጥ  በወላጆቹ እንዲሁም በአያቱ በወይዘሮ ይመስገን ገብረሥላሴ የማይነጥፍ ፍቅርና ምክር ታንጾ አድጓል። የሕይወት ጉዞው መሠረትና መገለጫ የሆኑት በጎነት፣ ብሩህ ተስፋ፣ ቆራጥነትና የመሪነት ስብዕና  ገና በለጋ እድሜው የሚታዩ ባህሪያት ነበሩ።

አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ሳንፎርድ የእንግሊዝ ትምህርት ቤት  ከተከታተለ በኋላ፣ ወደ አሜሪካ በመጓዝ በዮርክ ፔንሲልቬንያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቋል። በመቀጠልም ከፔንሲልቬንያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በኦፕሬሽን ማኔጅመንት እና ማርኬቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪዉን ተቀብሏል። በውጭ ሀገር የነበረው ቆይታ የአስተሳሰብ አድማሱን ቢያሰፋውም፣ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረዉን ቁርኝት ግን ምንጊዜም የማንነቱ ማዕከል ነበር። ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ፣ ሀገሩን ለማገልገል በታላቅ ተነሳሽነትና በጠራ ዓላማ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል።

1989 ዓ/ም አማን እና የሕይወት አጋሩ ወይዘሮ ማክዳ አሰፋ የተገናኙበት፣ የህይወት መስመራቸው አንድ ሊሆን መንገድ የጀመረበት አመት ነበር። እናም አቶ አማን እና ግማሽ አካሉ ማክዳ  ሚያዝያ 1 ቀን 1991 ዓ.ም  በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል። ትዳራቸው በጥልቅ ፍቅር፣ በማይናወጥ መደጋገፍ፣ ሁኔታዎችና ፈተና በማይበግረው ጽኑ ታማኝነት ላይ የተገነባ የሕይወት ጥምረት ነበር። ሁለት ሆነው እንደ አንድ የኖሩበትን የትዳር ህይወት በመከባበር፣ በፈሪሃ እግዚአብሄር እና በጋራ ህብረት በተገነባ ጥንካሬ መርተውታል። አማኑኤል፣ መቅደላዊትና ሰላም ፍስሐጽዮን የተባሉ ሦስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ ኖቫ የተባለች የልጅ ልጅ ለማየትም በቅተዋል። አቶ አማን በህይወቱ እጅግ መጠነ ሰፊ የሆኑ ስኬቶች ባለቤት ቢሆንም፣ ከሁሉም በላይ ትልቁ ኩራቱና የልብ ደስታው ቤተሰቡ ነበር።

በ2000 ዓ/ም አማን ከአጋሮቹ ከአቶ ሙሴ ፍስሐጽዮን፣ አቶ ኖኅ ፍስሐጽዮንና አቶ ነቢዩ ያሬድ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስን (EBS TV) በሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ መሰረቱ። በታላቅ ራዕይ የተጀመረው ይህ ተቋም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን የሚደርስና በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዋነኛ የመገናኛ ድልድይ የሆነ ዓለም አቀፍ የሚዲያ መድረክ ለመሆን በቅቷል። ኢቢኤስ የአማንን የፈጠራ ስራ መሪነትና አርቆ አሳቢነት የሚያንጸባርቅ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ታማኝና ተደማጭነት ያለው ነጻ ድምፅ ለመሆን በቅቷል።

በ2003 ዓ/ም አማን ለብዙ ዘመናት ሲመኘው የነበረውን ወደ ሀገር የመመለስ ውሳኔ ተግባራዊ አድርጓል። ይህ ውሳኔ በሕይወቱና በሙያው ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነበር። በእሱ መሪነት ኢቢኤስ በኢትዮጵያ የሚዲያ እድገት ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቷል። በራዕዩና እረፍት የለሽ ትጋቱ በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥና ሽግግር እንዲመጣ አድርጓል። ነፃ የመገናኛ ብዙሃን እንዲስፋፋ እና በቴሌቪዥንና በመዝናኛው ዘርፍ ለአዳዲስ ፈጠራዎችና ለበርካታ ባለክህሎቶች እድልና መድረኮች እንዲፈጠሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በጣም በርካታ ውጤቶችን ባስመዘገበበት እና መሰረታዊ የሚባል አሻራን ባተመበት ጉልህ የሥራ ዘመኑ ፣ አማን በአሜሪካና በኢትዮጵያ ውስጥ በበርካታ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የአመራርነትና በቦርድ አባልነትም አገልግሏል። የቲ.ኤ ብሮድካስቲንግ (TA Broadcasting Inc.) ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የክሊር ኮሙኒኬሽንስ (Clear Communications Inc.) የማርኬቲንግ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በአዲስ አበባ የአብዶሽ ኢንተርናሽናል ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን ሰርቷል። በተጨማሪም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ በአዲስ አበባ የዲያስፖራ ማህበር፣ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትና ብሮድካስተሮች ዘርፍ ማኅበር ውስጥም በአመራርነትና በባለሙያነት የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ለነበረው ስኬቶችም በርካታ እውቅናዎችንና አክብሮቶችን  አግኝቷል። ከኢትዮ-አሜሪካ የንግድ ምክር ቤት የላቀ የንግድ ስራ ሽልማትን የተቀበለ ሲሆን፣ የዓመቱ ፈር ቀዳጅ የዲያስፖራ ባለሀብት በመባልም ተሸልሟል።

አማንን በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ በሙያዊ ስኬቶቹ ብቻ ሳይሆን በስብዕናው ጥንካሬ፣ በደግነቱ፣ በለጋስነቱና ሌሎች ትልልቅ ህልሞችን አልሞ ለተግባራዊነቱ እንዲተጉ ሰዎችን በማነሳሳት ልዩ ችሎታው ያከብሩታል፣ ይወዱታል። አቶ አማን  ለብዙዎች ተስፋንና ብርታትን የሰጠ፣ የወደቁትን ያነሳ፣ የደከሙትን ያበረታ መልካም እና ታላቅ ሰው ነበር።  አማን ጋ ተስፋ መቁረጥ፣ መሸነፍ፣ መረታት፣ ቦታ አልነበረውም። የትኛውንም መሰናክል በማስተዋል፣ በጥበብ እና በብልሃት የሚያልፍ፣ በጊዚያዊ ጫጫታና ሁከት የማይረበሽ፣ ከፍርሃትና ከጥርጣሬ ጭለማ ይልቅ የተስፋን ብርሃን የመረጠ መልካም ሰው ነበር። የአመራር መርሁም ሆነ ከሰው ጋር ያነበረው መስተጋብር የረጋ መንፈስን እና ቅን ልቦናውን መሰረት ያረጉ ነበሩ።  በጣም ፈታኝ በሆኑ ጊዜያት ውስጥ እያለፈ እንኳን፣ ነገ የተሻለ እንደሚሆን የማይናወጥ እምነት ነበረው። ያንን የተሻለ ነገ እውን ለማድረግም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሰርቷል። ለሌሎች በር መክፈት፣ መድረክ መስጠት፣ ማገዝ፣ ማበረታታትና ከፍ ማድረግ የሁልጊዜም መገለጫው ነበር።

አቶ አማን በሕይወት የተለያት የሚወዳት ባለቤቱን ወይዘሮ ማክዳ ፍስሐጽዮን፣ ልጆቻቸውን አማኑኤል፣ መቅደላዊትና ሰላም ፍስሐጽዮን፣ የልጅ ልጁን ኖቫ ፍስሐጽዮን፣ እናቱን ወይዘሮ ሕይወት ተኬን፣ ወንድምና እህቶቹን ሜሮንን፣ ሙሴን፣ ኖኅን፣ ነጻንና ሜሪ ፍስሐጽዮንን እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የቤተሰብ አባላትንና ወዳጆቹን ነው።

አቶ አማን አሁን በፈጣሪ ፊት በዘላለማዊ ሰላም እና እረፍት እንዳለ እናምናለን። ያም ሆኖ ታሪኩ ወደፊት በነጻነት እንዲራመድ ባገዘው ፣ ባቋቋማቸው እና በገነባቸው ተቋማትና ከምንም በላይ በሚወደው  ቤተሰብ ውስጥ ህያው ሆኖ ይኖራል። አቶ አማን በጸና እምነት ተመርቶ፣ በታማኝነት፣  በማገልገል እና እራስን አሳልፎ በመስጠት የተሞላ ሕይወትን ኖሯል።

የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙሃን  በራዕዩ የለወጠ፣ ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ የሆነ፣ ፈር ቀዳጅ፣ ሀገር ወዳድና የእምነት ሰው ሆኖ ምንጊዜም ሲታወስ ይኖራል። የአማን ራዕይ፣  የስራው ውጤት፣ በጎ ተጽዕኖውና በሁላችንም ላይ የጣለው አሻራ ዘወትር ማብራቱን ይቀጥላል።

******************

የአቶ አማን ፍስሃጽዮን ስርዓተ ቀብር የካቲት 12 ቀን 2018  ቤተሰቦቻቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸው የሙያ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናትና የተለያዩ ተቋማት መሪዎች በተገኙበት በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈፅሟል። ከስርዓተ ቀብር ስነስርዓቱ ቀደም ብሎ የስንብት መርሃ ግብር በአድዋ ሙዚየም  ተካሂዷል።

አቶ አማን ፍስሃጽዮን የኢትዮጵያን የሚዲያ ኢንዱስትሪ በማዘመንና ጥበብን ወደ ቤታችን በማድረስ ረገድ የማይረሳ አሻራ ጥለው አልፈዋል። ላበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ሁሌም ሲታወሱ ይኖራሉ።

በድጋሚ ለአቶ አማን ፍስሃፅዮን ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦች፣ ወዳጅ ዘመዶቹና ለመላው የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ቤተሰቦች ሁሉ መፅናናትን እንመኛለን።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe