የኢትዮጵያው ‹ቦኮ ሀራም› ማነው?

ሸገር ሬዲዮ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ስለታገቱት የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሰራው ዜና ላይ የተነሱትን ነጥቦች ልብ ብሎ ለተመለከተ ሰው እየሆነ ባለው ነገር ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡ መንግስትን እና በስሩ ያሉ ተቋማትን በእጅጉ ይታዘባቸዋል፡፡ ‹እውን እዚህች ሃገር ላይ ለውጥ መጥቷል ወይ?› ብሎ መጠየቁ የሚጠበቅ ነው፡፡
ዜናው እንደወረደ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲሄዱ የታገቱ ተማሪዎችን የተመለከተ አዲስ መረጃ እንደሌለ የፌደራል ፖሊስ ተናገረ፡፡
የፌደራል ፖሊስ የተማሪዎችን ጉዳይ እየተከታተለው መሆኑን የነገሩን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ አዲስ ነገር ሲኖር ለህዝብ እናሳውቃለን ብለዋል፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ ከእገታ የተለቀቁትንና ያልተለቀቁትን ተማሪዎች ማንነት ከዩኒቨርስቲው ለማጣራት ጥረት ባደርግም ስልክ አልሰራ ስላለኝ ጥረቴ አልተሳካም ሲል ተናግሯል፡፡ነገር ግን ተማሪዎቹን የተመለከተ አዲስ መረጃ በሚያገኝበት ወቅት ለህዝብ የሚያሳውቅ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ቢሮ ሰምተናል፡፡
በዶንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ሁከት መቀስቀሱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ስለመታገታቸው መነገሩ ይታወሳል፡፡የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሀላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከታጋቾቹ ውስጥ 21ዱ ማለትም 13 ሴቶችና 8 ወንዶች መለቀቃቸውን ለኢቲቪ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ሌሎች ያልተለቀቁ 6 ታጋቾች መኖራቸውንም መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ሸገር ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካለትም፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮን ለማናገር ያደረግነው ጥረትም አልተሳካልንም፡፡ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ምን እንደሚል ለመስማት ስልክ ብንደውል፣ ስልካቸው አይሰራም፡፡ሸገር በአካባቢው የኔትዎርክ ብልሽት ያለ እንደሆነ እንዲነገረው ኢትዮ ቴሌኮምን ቢጠይቅም መልስ አላገኘም››
ከዚህ የሸገር ዜና እንደምንረዳው ስለታገቱት የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ከየትኛው የመንግስት አካል መረጃ ማግኘት አይቻልም፡፡ የፌዴራል ፖሊስ መረጃ የለኝም ብሏል፤ 21 ተማሪዎችን አስለቅቄያለሁ ሲል ይፋ ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ማስረጃ አልሰጠንም፤ ልጆቹን ከማን እንዳስለቀቀና አሁን የት እንዳሉ አልነገረንም፡፡ ከቤተሰቦቻቸውም አላገናኛቸውም፡፡ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮና የክልሉ መንግስትም መረጃ ሊሰጥ አልቻለም፡፡ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ጉዳዩ ድራማ ነው እንዴ? ብለን እንድንጠይቅ ይጋብዙናል፡፡
የአቶ ንጉሡ መግለጫ
በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ በታጣቂዎች የታገቱ 21 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በአቶ ንጉሡ አማካኝነት ካስታወቀ ከሳምንት በላይ ተቆጥሯል፡፡
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ታግተው መቆየታቸውን ነው የፅ/ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የተናገሩት።
ታግተው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 13 ሴትና 8 ወንድ በድምሩ 21 ተማሪዎች የተለቀቁ ሲሆን አሁንም ቀሪ 5 ተማሪዎችና አንድ የአካባቢው ተወላጅ ታግተው እንደሚገኙና በአካባቢው የፀጥታ ኃይል መሰማራቱን ኃላፊው አክለዋል።
ኃላፊው ይህንን ይበሉ እንጅ ቤተሰቦች ግን ምንም አይነት መረጃ የለንም፤ ከልጆቻችን ጋር አልተገናኘንም ይላሉ፡፡ እህቱ እንደታገተችበት የገለጸ አንድ ግለሰብ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በስልክ ባደረገው ቃለ ምልልስ እህቱም ሆነች ሌሎቹ ተማሪዎች በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃው እንደሌለው ተናግሯል፡፡
”እህቴ እስካሁን አልደወለችልኝም፤ ማንም የደወለልኝም ሰው የለም። ተማሪዎች ተለቅቀዋል የሚለውን ዜና ከሰማሁ በኋላም ሌሎች ልጆቻቸው የታገቱባቸው ቤተሰቦች ጋር በስልክ ተገናንኝተን ነበር፤ እነሱም እስካሁን ምንም መረጃ የላቸውም” ብሏል።
አክሎም ”እኔም ደወልኩላቸው፤ እነሱም ደወሉልኝ። ነገር ግን ማንኛችንም ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ ከመንግሥትም ሆነ ከተማሪዎቹ ራሳቸው የተነገረን ነገር የለም” ብሏል።
”ተማሪዎች ተለቅቀዋል የሚለውን ዜና ስንሰማ በጣም ደስ ብሎናል። ነገር ግን የተለቀቁ ተማሪዎች ዝርዝር ስላልታወቀ ግራ ገብቶናል። በጣም ደስ ቢለንም ማን ይለቀቅ ማን ይቅር ስላላወቅን አስቸጋሪ ሆኖብናል።”
ለሁለት ሳምንታት ከእህቱ ጋር በስልክ ሲገናኙ ስለአወሩት ነገር ተጠይቆም ”በደወሉ ቁጥር ቦታው ምን ይመስላል? ንገሩን ወይ እራሳችን ወይ ፖሊስ እንዲመጣ ስንላቸው ማውራት አንችልም፤ አጠገባችን አሉ ይሉን ነበር። በተጨማሪ ደግሞ ማታ ላይ ለሁለት ወይም ለሶስት ሰዓታት ያክል በጫካ ውስጥ እንድንጓዝ ያደርጉናል ብላኝ ነበር” ብሏል።
”ከዋልንበት አናድርም፤ ካደርንበት አንውልም። ሁሌም ማታ ማታ እንጓዛለን” የሚል ምላሽ ትሰጠው እንደነበር ያስታውሳል።
ወንድሟ ከታጋች ተማሪዎች መካካል አንዱ እንደሆነ የተናገረች ወጣትም እስካሁን ተለቀቁ የተባሉት ተማሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የሰማችው ነገር እንደሌለ ትናገራለች።
”ዜናውን ከሰማንበት ሰዓት ጀምሮ በጉጉት እየተጠባበቅን ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ወንድሜም አልደወለም፤ ሌላ የደወለልኝም አካል የለም” ብላለች።
”ሌሎች የቤተሰብ አባሎቻቸው ከታገቱባቸው ጋር እንገናኛለን፤ እነሱም ቢሆኑ እስካሁን የሰሙት ነገር እንደሌለ ነግረውኛል። ማን እንደተለቀቀና ማን እንዳልተለቀቀ ይነግሩናል ብለን ብንጠብቅም እስካሁን ምንም ነገር የለም” የታጋች እህት የሰጠችው ምላሽ ነው።
ታጋቾቹ ተማሪዎች
ከቤተሰብ በተገኙ መረጃዎች መሠረት ታግተው ያሉ ተማሪዎች ስምና ይማሩበት የነበረው ትምህርት ክፍል ዝርዝር የሚከተለው ነው፦
 በላይነሽ መኮንን ደምለው – ኢኮኖሚስት 1ኛ ዓመት
 ሳምራዊት ቀሬ አስረስ – ጋዜጠኝነት 2ኛ ዓመት
 ዘውዴ ግርማው ፈጠነ – ኢኮኖሚክስ 3ኛ ዓመት
 ሙሉ ዘውዴ አዳነ – ሳይኮሎጅ 2ኛ ዓመት
 ግርማቸው የኔነህ አዱኛ – ባዮሎጅ 3ኛ ዓመት
 ስርጉት ጌትነት ጥበቡ- ተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዓመት
 ትዕግስት መሳይ መዝገቡ – 12ኛ ክፍል ተማሪ (የአካባቢው ተማሪ)
 መሠረት ከፍያለው ሞላ- ተፈጥሮ ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 ዘመድ ብርሃን ደሴ- ተፈጥሮ ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 ሞለሞን በላይ አበበ- ጋዜጠኝነት 3ኛ ዓመት
 ጤናዓለም ሙላቴ ከበደ- አግሪ ሳይንስ 2ኛ ዓመት
 እስካለሁ ቸኮል ተገኘ- ኬሚስትሪ 3ኛ ዓመት
 አሳቤ አየለ አለም- ቬተርናሪ ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 ቢተውልኝ አጥናፍ አለሙ – ኮምፒዩተር ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 ግርማው ሐብቴ እማኘው- መካኒካል ኢንጅነሪንግ 3ኛ ዓመት
 አታለለኝ ጌትነት ደረሰ- ተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዓመት
 ክንዳየሁ ሞላ ገበየሁ- ተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዓመት
ከታጋቾች አንዷ
ተማሪ አስምራ ሹሜ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነበረች። የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ታስረዳለች።
“በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነበርኩ። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በመዘጋቱ ወደ ትውልድ አካባቢዬ ተመልሼ አዲስ ዘመን ከተማ ነው ያለሁት።
ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነኝ። መጀመሪያ በአጋቾቹ የተያዝነው 18 ተማሪዎች ነበርን። እኔ ማምለጥ ስለቻልኩ አሁን ታግተው ያሉት ተማሪዎች ቁጥር 17 ነው። ከእነዚህ መካከል 4ቱ ወንዶች ሲሆኑ 13ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። አሁን ታግተው ያሉት ተመራቂ ተማሪዎች እና የኢንጅነሪንግ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች ናቸው።
በወቅቱ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ስለነበር ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተው ነበር። እኛም መውጣት አሰብን ወደ አዲስ አበባ በቀጥታ የሚያስመጣው ዋና መንገድ በመዘጋቱ ከደምቢ ዶሎ በጋምቤላ በኩል አድርገን አዲስ አበባ ለመግባት ወሰንን።
ሁላችንም ከአማራ ክልል አካባቢዎች የመጣን ተማሪዎች ነን።
ከደምቢ ዶሎ ጋምቤላ የ30 ብር ትራንስፖርት ሲሆን እቅዳችን ጋምቤላ አድረን ወደ አዲስ አበባ ነበር። ነገር ግን ያሰብነው ቦታ ሳንደርስ ደምቢ ዶሎ እና ጋምቤላ መካከል ‘ሱድ’ የምትባል ቦታ ላይ ስንደርስ መኪናውን አስቁመው፤ ወጠምሻ ወጣቶች መጥተው አፈኑን። የአፋኞቹ ቁጥር ከእኛ ቁጥር በላይ ነበር።
አካባቢው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ በእርሱ ውስጥ ይዘውን ገቡ። ይዘውን ሲሄዱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ከማየት ውጭ ለማስጣል የሞከረ አልነበረም።
እየጮህን ነው ይዘውን የሄዱት። የጫካውን ግማሽ እንደተራመድን የተወሰኑት ሴቶች መራመድ አቃታቸውና ወደቁ። ታዲያ እነርሱን ‘ተነሱ፤ አትነሱ’ እያሉ ለማንሳት ሲሞክሩ ነበር እኔ ከአይናቸው የተሰወርኩት።
በጫካው ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ካደርኩ በኋላ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው የመኪና መስመር መውጣት ቻልኩ። ግራ ተጋባሁ፤ ስልኬን ስለወሰዱት ስልክ መደወል አልቻልኩም፤ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር።
እንደምንም ብዬ ወደ መስመር ስወጣ አንድ አማርኛ በትንሹም ቢሆን መናገር የሚችሉ አባት አገኘሁ። እርሳቸው እንዳዩኝ ‘የእኔስ ልጆች እንዲህ አይደል የሚሆኑት’ ብለው በማዘን ኮታቸውን አለበሱኝ።
‘ከታየሁ እኔም እገደላለሁ’ ብለው ደብቀው አስቀመጡኝ። ‘የት ነው መሄድ የምትፈልጊው’ አሉኝ። ‘ደምቢ ዶሎ ለፌደራል ፖሊሶች ስጡኝ’ አልኳቸው። ከዚያም መኪና ለምነው አሳፍረው ላኩኝ። መረጃውንም ለፌደራል ፖሊሶቹ ተናግሬያለሁ። ፌደራል ፖሊሶቹ ‘ቦታው እንኳን ለተማሪ ለወታደርም አስጊ ነው፤ እንከታተላለን’ አሉኝ።
ከታገቱት መካከል አንዷ ጓደኛዬ መጀመሪያ አካባቢ ስልክ እየሰጧት ትደውልልኝ ነበር። ለማውራት ብዙም ነፃነት ባይኖራትም ‘በጣም እያሰቃዩን ነው፤ ምግብም ሲያሻቸው ይሰጡናል፤ ሲፈልጉ ደግሞ ይከለክሉናል’ ስትል ነግራኛለች። የምትደውልበትን ስልክ ‘የእነርሱ ነው ያዥው’ ብላኝ ነበር። ከዛን ቀን በኋላ ግን አይሰራም፤ እነርሱም ደውለው አያውቁም፤ እኛም አግኝተናቸው አናውቅም።
ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት፤ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፀጥታ እና ደህንነት መረጃውን ሰጥቻለሁ፤ ጠይቄያለሁ። ‘እንከታተላለን’ ነው ያሉኝ።
ከዚያ መምጣቴን የሚያውቁ የተማሪዎቹ ወላጆችም ያለሁበት ድረስ እየመጡ ያለቅሳሉ፤ እኔ ግን ‘መንግሥት ይዟቸዋል፤ አሁን ይመጣሉ’ እያልኩ ከማረጋጋት ውጭ የማደርገው ጠፍቶኛል።”
የቤተሰቦች ጭንቀት
ተማሪዎቹ ተለቀዋል የሚለው ዜና ከመሰማቱ በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸውን ለልጆቹ ደህንነት ስንል ያልጠቀስናቸው የታገቱት ተማሪ ቤተሰቦች፤ ተማሪዎቹ ከታገቱ አንድ ወር እንዳለፋቸው ይናገራሉ። “በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ስልክ ይደውሉ ነበር፤ አሁን ግን ድምፃቸውን ከሰማን ሦስት ሳምንታት አልፈዋል” ይላሉ።
እህቱ እንደታገተችበት የነገረን አንድ ግለሰብ፤ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ሲወጡ፤ እርሱም እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ቢነግራቸውም እነርሱ ግን ከአሁን አሁን ይረጋጋል እያሉ መቆየታቸውን ያስረዳል።
ይህ ግለሰብ እንደሚለው ስልክ ተደውሎለት እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ስለመታፈናቸው የሰሙት ሕዳር 24፣ 2012 ዓ.ም ነው።
ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ በነበሩት ሁለት ሳምንታት በተማሪዎቹ ስልክ ከዚያ በኋላ ‘የአጋቾቹ ነው’ ባሏቸው ስልክ ይደውሉላቸው ነበር። ቦታውን ሲጠይቋቸው ግን እንደማያውቁት ነበር ሲነግሯቸው የቆዩት።
“የሆነ ሰዓት ላይ ስልክ ተሰጥቷት የፅሁፍ መልዕክት ላከችልኝ፤ ”አሻና አፋን ገደራ’ የሚባል ቦታ ነው ያለነው፤ ለመከላከያ ደውሉና እዚህ አካባቢ ይፈልጉን’ ብላ ፃፈችልኝ” ይላል።
በመጨረሻው የስልክ ልውውጣቸው፤ “አሁንም እዚያው ቦታ ነሽ ወይ?” ብሎ ሲጠይቃት “በፊት ቢሆን ጥሩ ነበር፤ አሁን ቦታ ቀይረናል፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የሁለት የሦስት ሰዓት መንገድ በጫካ እንጓዛለን፤ አታገኙንም፤ አሁንም ልትንቀሳቀሱ ነው ተብለናል፤ እስካሁን ባለው ደህና ነን” ስትል ስልኩን ከዘጋች ወዲህ እህቱን በስልክ ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራል።
ከታጋች ተማሪዎች ወላጆች መካከል ሁለት ሰዎች፤ ስለ ልጆቻቸው መረጃ ፍለጋ ወደ ደምቢ ዶሎ ተጉዘው እንደነበረ ይሄው እህቱ የታገተችበት ወንድም ይናገራል።
እሱ እንደሚለው ወደ ሥፍራው የሄዱት ሰዎች ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።
የኢትዮጵያው ‹ቦኮ ሀራም› ማነው?
እስካሁን አጋቾቹ እነማን እንደሆኑ በግልጽ አልታወቀም፡፡ አጋቾቹ ሀላፊነቱን ወስደው የሚፈልጉትን ነገር አልጠየቁም፡፡ መንግስትም ቢሆን በአቶ ንጉሡ በኩል ስለልጆቹ መለቀቅ ሲገልጽ ከማን እንደተለቀቁ ግን አልተናገረም፡፡
ወንድሟ የታገተባት እህት ከወንድሟ ባገኘችው መረጃ መሠረት አጋቾቹ ገንዘብ አይፈልጉም። ከአጋቾቹ እጅ ያመለጠችው አስምራ እንደምትናገረው ደግሞ፤ አጋቾቹ በተደጋጋሚ “ከእናንተ ጋር ጸብ የለንም። ጸባችን ከመንግሥት ጋር ነው” እንደሚሉ ትናገራለች።
አጋቾቹ “የአማራ ሕዝብ ልጆቻችን ታግተዋል ብሎ ሰልፍ ሲወጣ፤ መንግሥት እኛን ያነጋግራል። የዛኔ እኛ ጥያቄያችንን ለመንግሥት እናቀርባለን፤ ጥያቄያችንም ይመለሳል” እንዳሉ አስምራ ለቢቢሲ ገልፃለች።
ተማሪዎቹን ያገታቸው የትኛው አካል እንደሆነ በይፋ ባይነገርም፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው እና በድሪባ ኩምሳ የሚመራው ኃይል ስለመሆኑ ግምቶች ይሰጣሉ ሲል ቢቢሲ ጽፏል፡፡
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የቀድሞ የኦነግ ጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ በትግል ስሙ ጃል መሮ ግን በቢቢሲ ተጠይቆ “ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ እየሰማሁ ያለሁት ከእናንተ ነው። የትግል ዓላማችን ከተማሪዎች ጋር አይገናኝም። በተማሪዎቹ ላይም ይህን የተባለውን አይነት ተግባር አልፈጸምንም። እንደተለመደው የእኛን ስም ለማጉደፍ የተወራ ነው እንጂ በፍጽም እንዲህ አይነት ተግባር አሁንም ወደፊትም እንፈጽምም።”
መሮ ተማሪዎቹ ታግተውበታል በሚባለው ሥፍራ በኮንትሮባንድ ንግድ ሥራ ላይ ታጥቀው የተሰማሩ አካላት መኖራቸውን ተናግሮ፤ የእሱ ጦር ግን በአካባቢው እንደሌለ ይናገራል።
ትዝብት ውስጥ የወደቀው መንግሥት
የአማራ ሴቶች ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት እና የአማራ ሴቶች ማህበር በቅርቡ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ በመግለጫው ላይ ‹‹የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ መንግሥት የተሰጠው የተምታታ መግለጫ ለጉዳዩ ትኩረት አለመሥጠቱን ማሳያ ነው›› ሲል ትዝብቱን አንስቷል፡፡ ይህ የሌችም ትዝብት ነው፡፡
ምንም እንኳ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ ታግተው ከነበሩ አብዛኞቹ ተለቀዋል ቢሉም፤ ተማሪዎቹ ስለመለቀቃቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ እስካሁን አልተሰጠም።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት፤ ተማሪዎቹን ያገታቸው ማነው? ከተለቀቁ የት ነው የሚገኙት? ከወላጆቻቸው ጋር ለምን እንዲገናኙ አልተደረገም? ለሚሉ እና ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ስላልሰጠ፤ የጉዳዩ አወዛጋቢነት እንደቀጠለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ታግተዋል ያሉት የተማሪዎች ቁጥር እና የፌደራል መንግሥት ከእገታው አስልቅቄያለሁ የሚለው ቁጥር ልዩነት፤ በመንግሥት መካከል በራሱ የመረጃ መጣረስ መኖሩን ያሳያል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe