የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብድር ገደብ ሙሉ በሙሉ አነሳ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዳዲስ የፖሊሲ ማሻሻያ አደረገ፤ የብድር ገደብ ሙሉ በሙሉ አነሳ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ 7ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ በሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ፣ የዋጋ ግሽበት፣ የባንክ ዘርፍ አፈጻጸምና በበጀት ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ግምገማ ካደረገ በኋላ አምስት ዋና ዋና የፖሊሲ ውሳኔዎችን ለቦርዱ አቅርቦ ማጽደቁን በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል።
የባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ያሳለፋቸውና በብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የጸደቁት አምስቱ ቁልፍ የፖሊሲ ማሻሻያዎች የሚከተሉት ናቸው፦
የመጀመሪያውና ዋናው ውሳኔ ብሔራዊ ባንክ በጊዜያዊነት ሲጠቀምበት የቆየውን ዓመታዊ የብድር ዕድገት ገደብ (credit cap) ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ማድረጉ ነው። ይህ የብድር ገደብ የተነሳው የታቀዱትን ዓላማዎች በማሳካቱና የወለድ ተመንን መሠረት ያደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ ወደ ላቀ ሽግግር በመድረሱ እንጂ የባንኩ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ተቀይሮ እንዳልሆነ ተብራርቷል።
ሁለተኛው ውሳኔ የብድር ገደብ መነሳትን ተከትሎ ተመጣጣኝ የጥብቅ ፖሊሲ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ በመሆኑ፣ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ በ1.0 መቶኛ ነጥብ እንዲያድግ ተደርጓል። በዚህም መሠረት የፖሊሲ ወለድ ምጣኔው ከ15 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል የተወሰነ ሲሆን የ ± 3 መቶኛ ነጥብ ክልል (band) ሳይለወጥ እንዲቆይ ተደርጓል።
ሦስተኛው ውሳኔ የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ፣ በእያንዳንዱ ባንክ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ ምጣኔ ታርጌት (loan-to-deposit ratio) ላይ በመመስረት የተለየ የመጠባበቂያ ተቀማጭ (targeted reserve requirement) እንዲተገበር መወሰኑ ነው።
አራተኛው ማሻሻያ ከሸቀጦች ገቢ ንግድ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመቀነስና የውጭ ምንዛሬ ገበያን ለማሳደግ ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ኮሚሽን ምጣኔ ከ2.5 በመቶ ወደ 1.5 በመቶ (በ1 በመቶኛ ነጥብ) እንዲቀንስ ተወስኗል።
አምስተኛው ውሳኔ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻልና የገበያ ላይ መተማመንን ለመገንባት የታለመ ሲሆን፣ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ለባንኮች እንዲያስረክቡ ቀደም ሲል ይጠየቁ የነበረው 50 በመቶ (FX surrender requirement) ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
የበጀት ሁኔታን በተመለከተ፣ መንግሥት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወስድ መደረጉ የመሠረታዊ ገንዘብ ዕድገትን ለመገደብ ማገዙ የተገለጸ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ምጥጥን 0.9 በመቶ መድረሱ ታውቋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው በመስከረም 2019 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ እንደገና ለመሰብሰብ ቀጠሮ ይዟል።
(መናኸሪያ ራዲዮ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe