የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ወጪ 54 ሚሊዮን ዶላር አለመክፈሉ ተነገረ

ኢትዮጵያን ጨምሮ አሥር የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መንግሥታት በየአገሮቻቸው የበረሩ አየር መንገዶች ላቀረቧቸው አገልግሎቶች በውጭ ምንዛሪ ሊከፈላቸው የሚገባቸውን አጠቃላይ 1.08 ቢሊዮን ዶላር አለመክፈላቸውን፣ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (IATA) አስታወቀ።
ዓለም አቀፉ ማኅበር በተያዘው ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ ባደረገው አጭር ሪፖርት እንደገለጸው፣ እ.ኤ.አ. እስከ ጥቅምት ወር 2025 መጨረሻ ድረስ እስካለው ጊዜ በየአገሮቻቸው ለተንቀሳቀሱ አየር መንገዶች መክፈል ከነበረባቸው የውጭ ምንዛሪ ካልከፈሉት መንግሥታት፣ 93 በመቶ የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ናቸው።
በአጠቃላይ መከፈል ከነበረበት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 89 በመቶ ወይም 1.08 ቢሊዮን ዶላር ያህሉ፣ በአሥር አገሮች መንግሥታት ወጪ ያልተደረገ ፈንድ (Blocked Fund) መሆኑን፣ የአየር ትራንስፖርት ማኅበሩ አስታውቋል።
በሪፖርቱ ከተጠቀሱት በየአገሮቻቸው አገልግሎት ላቀረቡ አየር መንገዶች መከፈል የነበረበትን ገንዘብ ካልከፈሉ መንግሥታት ውስጥ፣ አልጄሪያ በ307 ሚሊዮን ዶላር ተቀዳሚውን ሥፍራ ስትይዝ፣ በተመሳሳይ የገንዘብ ኖት የሚገለገሉት ስድስቱ የአፍሪካ አገሮች ዞን (ZAF Zone) 179 ሚሊዮን ዶላር፣ ሊባኖስ 138 ሚሊዮን ዶላር፣ ሞዛምቢክ 91 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም አንጎላ 81 ሚሊዮን ዶላር አለመከፈላቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ኤርትራ 78 ሚሊዮን ዶላር፣ ዚምባቡዌ 67 ሚሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያና ፓኪስታን እያንዳንዳቸው 54 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም ባንግላዴሽ 32 ሚሊዮን ዶላር ለአየር መንገዶቹ ባለመክፈላቸው የስም ዝርዝራቸው ተካቷል፡፡
መንግሥታቱ ለአየር መንገዶቹ በውጭ ምንዛሪ መክፈል ይገባቸዋል የተባሉት ገንዘብ፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹ በአገሮቹ ውስጥ ለሸጡት የአውሮፕላን ጉዞ ቲኬት ሽያጭ፣ ካርጎ የማጓጓዝ አገልግሎት፣ እንዲሁም በአገሮቹ ውስጥ ላቀረቡት ተያያዥ የአቪዬሽን አገልግሎቶች መሆኑን ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ጠቁሟል፡፡
በተለመደው አሠራር መሠረትም መንግሥታቱ የአገልግሎት ክፍያዎቹን በዶላር ለውጠው ለአየር መንገዶቹ ዋና መሥሪያ ቤት መፈጸም እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ ማኅበር ማብራሪያ አብዛኛውን ጊዜ መንግሥታት የዶላር ክፍያውን ሳይፈጽሙ የሚቆዩት፣ በአገሮቹ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ክምችት በቂ አለመሆን፣ መንግሥታት ወይም ማዕከላዊ ባንኮች ተፈጻሚ የሚያደርጓቸው ገደቦች (Restrictions)፣ እንዲሁም እጅግ የተጓተቱና ከፍተኛ ቁጥጥርና ገደብ ያለባቸው የከፍያ ማፅደቅ ሒደቶች ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ ለምን 54 ሚሊዮን ዶላሩን መክፈል እንዳልቻለች ሪፖርተር ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ ክስተቱ እንግዳና የሚያሠጋ አለመሆኑንና ኢትዮጵያም በተመሳሳይ በሌሎች አገሮች ያላትን የውጭ ምንዛሪ እስካሁን ያልከፈሏት መንግሥታት መኖራቸውን የአየር መንገዱ እንድ የሪፖርተር የመረጃ ምንጭ ጠቅሰው፣ ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከተው ብሔራዊ ባንክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. የወቅቱን በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች ያልተሰበሰበ ገንዘብን አስመልክቶ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ይህ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ትልቅ ችግር ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በየአገሩ ተይዞብን ነበር፡፡ መጠኑ ቢቀንስም ነገር ግን አሁንም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፤›› ማለታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe