የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዛሬ 80 ዓመት (መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም) በአነስተኛ አውሮኘላን ከአዲስአበባ በአስመራ በኩል ወደካይሮ የመጀመሪያውን በረራ አደረገ። ዛሬ ከ80 ዓመት በኋላ 150 እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመያዝ ወደ 145 መዳረሻዎች በረራዎችን በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር ከሆኑ አየር መንገዶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።
አቶ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩኘ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለተቋሙ ሠራተኞች (የቀድሞዎቹን ጨምሮ) እንዲሁም አጋሮች እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ አየር መንገዱ ባለፉት 80 ዓመታት ከአንድ አውሮኘላን በረራ ተነስቶ በአሁን ጊዜ በበረራ ብቻ ሳይሆን በአውሮፕላን ጥገና፣ በስልጠና፣ በተቋም ግንባታ፣ በአውሮኘላን ማረፊያዎች ጥገናና ግንባታ እንዲሁም በሆቴል… ተደጋጋፊ በሆኑ ዘርፎች መሰማራት ችሏል። ይኸም አየር መንገዱ የአቪየሽን ግሩኘ ወደመሆን ማሳደግ ችሏል ብለዋል።
አየር መንገዱ በአሁን ሰዓት 150 ዘመናዊ አውሮፕላኖች በመያዝ፣ ከ28 ሺ በላይ ሰራተኞቹ እየታገዘ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን መቻሉን በአሁን ሰዓት ተጨማሪ 117 አውሮኘላኖች ማዘዙን ጠቅሰዋል።
አየር መንገዱ ከገጠሙት ተግዳሮቶች አንዱ የኮቪድ ሕመምን ተከትሎ የተከሰተው ችግር መሆኑን በማስታወስ በወቅቱ በርካታ አለምአቀፍ አየር መንገዶች ለኪሳራ ሲዳረጉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሩን በጥበብ ማለፉን አቶ መስፍን ተናግረዋል።
በአሁን ሰዓት የኢራንን ጦርነት ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ወደእጥፍ የሚጠጋ ጭማሪ ማስከተሉ ፈተና መሆኑን በመጥቀስ ይህንን ወጪዎችን በመቀነስና በቲኬት ላይ መጠነኛ ጭማሪ በማድረግ ለማለፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአየር መንገዱ 80ኛ ዓመት በተለያዩ መርሐግብሮች ለቀጣይ 6 ሳምንታት እንደሚከበር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ 10 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ወጪ በቢሾፍቱ ከተማ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከ3 ወራት በፊት ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ80ኛ ዓመት ምስረታውን ዛሬ ማክበር ጀመረ
Source#ድሬቲዩብ

