የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው እንደገለጹት አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ፖሊሲ በማስፈለጉ ነው ክለሳ የሚደረግበት፡፡
መልካም ግንኙነት የተፈጠረበት አዲስ ጎረቤት ሃገር መኖሩም ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ከ18 ኣመት በፊት ፖሊሲው ሲወጣ ደቡብ ሱዳን የሚባል ሃገር አልነበረም፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነትም ከመቃቃር ወደ መተባበር መጥቷል፤ እነዚህም ለማሻሻያው ከምክንያቶች ውሥጥ ይጠቀሳሉ ነው ያሉት፡፡
በሌላ በኩል የአውሮፓ ህብረት የውጭ የጸጥታ ጉዳይ ኃላፊ እንዲሁም የጊኒ እና የኢስቶኒያ መሪዎች ከቀጣዩ የካቲት ወር ጀምሮ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የንግድ የየብስ መንገድ በጅቡቲ መንግስት እድሳት እንደሚደረግለት በ15ኛው የኢትዮ_ጅቡቲ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ስምምነት መደረሱንም አቶ ነቢያት ገልጸዋል፡፡ ለተፈጻሚነቱም ጉባኤው የሁለቱን ሃገራት ጉዳይ የሚከታተል ቋሚ የቴክኒክ ኮሚቴ ማቋቋሙን ነው የገለጹት፡፡

