የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሳሳተና ተቀባይነት የሌለው የአፍሪካን ካርታ በድረ ገፁ ላይ በመጠቀሙ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሶማሊያ የሌለችበት የአፍሪካ ካርታ መጠቀሙንና በምትኩ ሶማሌ ላንድ ራሷን የቻለች አገር አድርጎ አቅርቧል ሲል ሚሞ የተባለው የሶማሊያ ሚዲያ ድርጊቱን ኮንኖታል።
መሥሪያ ቤቱ ካርታውን የተጠቀመው ባለፈው ቅዳሜ የተከበረውን የአፍሪካ ቀንን አስመልክቶ በፃፈው ጽሁፍ ላይ ነበር።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኦፊሴላዊ ድረ ገፁ የተጠቀመው የአፍሪካ ካርታ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ግዛት እንደሆነች ተደርጎ ቀርቦበታል።
በካርታው ላይ በሶማሌ ላንድ የምትገኘው ሃርጌሳ አስተዳዳር ራሷን የቻለች አገር እንደሆነች አሳይቷል።
ካርታው በማህበራዊ ሚዲያዎች ከተዘዋወረ ከሰዓታት በኋላ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ካርታውን ከገፁ ላይ ያጠፋው ሲሆን በኢፌዴሪ አርማ ተክቶታል።
ስህተቱ በፈጠረው ውዥንብር መፀፀቱን የገለፀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ቡድኑ የድረ ገፁን ደህንነት ለማረጋጋጥ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ምንጭ፡ BBC Amharic