የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው ያልተያዙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሳይውሉ አይቀሩም ተባለ

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እስካሁን ድረስ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ግለሰቦች ቢዘገይም ነፃ እንደማይሆኑ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔነራል እንደሻው ጣሰው ሐሙስ የካቲት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በኮሚሽኑ መሥሪያ ቤት በሰጡት መግለጫ፣ የእስር ትዕዛዝ ለወጣባቸው ግለሰቦች ትዕዛዙን ለማድረስ ሲኬድ ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ በመግለጽ፣ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት መታኮስ አስፈላጊ ስላልነበር የተለያዩ አማራጮች ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹አንዳንድ ጉዳዮች በመደበኛ የፖሊስ ሥራዎች ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ የተለያዩ ቦታዎች ሔደው የተደበቁ ሰዎች አሉ፡፡ የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው በኋላም የእስር ማዘዣውን ቦታው ድረስ ሄዶ ለመስጠት ሲሞከር ያጋጠሙ እንቅፋቶች አሉ፡፡ በዚህ ወቅት አትታኮስም፡፡ ሁኔታው አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ በጥሞና እንዲታይ ይደረጋል፡፡ ይኼ ለሰላም ሲባል ነው፡፡ ይኼ የሚደረገው አጠቃላይ ነገር እንዳይበላሽና እንዳይደፈርስ ሲባል ነው፡፡ ይኼ ማለት ግን ሄዶ ሄዶ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ሰዎች ነፃ ይወጣሉ ማለት አይደለም፡፡ እንኳን በአገር ውስጥ ያለ ይቅርና በውጭ አገር በወንጀል የተጠረጠረ ካለ ይዘን እናቀርባለን፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ይኼንንም ለማስፈጸም ከተለያዩ ክልሎች ጋር አስተዳደራዊ ውይይቶች እንደተደረጉ በማስታወቅ፣ ‹‹ጉዳዮቹ ጊዜ ተሰጥቷቸው የክልል መንግሥታትም የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና በወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ይዘው የሚያስረክቡ ክልሎች እንዳሉም ያወሱት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፣ በተቃራኒው የሚደብቅ፣ የሚሸሽግና አካባቢዬ ላይ ተጠርጣሪው የለም ብሎ የሚያብር ሰው መልካም ተሞክሮ እንዳልሆነ፣ ብሎም የተጀመረውን ለውጥ የሚያናጋና የሚያበላሽ እንዲሁም የወንጀል መከላከል ሥራ ላይም ጥላ የሚያጠላ ጉዳይ ስለሆነ በሚታረምበት መንገድ ይታረማል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe