‹የእኔ የምርጫ አካሄድ የሚያተኩረው  የተሻለ ሀሳብ እንዳለኝ ማቅረብ ላይ ነው እንጂ ሌላውን በማጣጣል ላይ አይደለም ›

በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰባኪነቱ ይታወቃል፤በሚፅፋቸው ወጎቹ ብዙዎችን ያስደምማል፤ ከ25 በላይ መፅሐፍትን አሳትሟል፤ የመፅሐፍት ወዳጅ ነኝ የሚል ሰው የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን መፅሐፍት ያውቃቸዋል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሀገራችን የአመራር ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ዲያቆን ዳንኤል የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆኖ ቤተመንግስት ገብቷል፤ በቅርቡ በሚካሄደው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ደግሞ ራሱን ወክሎ በግሉ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ለመወዳደር እጩ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በብዕሩ ብዙ አድናቂዎች ያሉት ዲያቆን ዳንኤል የምርጫ ዘመቻውን በቅርቡ በካፒታል ሆቴል ጀምሯል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሆኖ በግሉ ስለሚወዳደርበት ምክንያት፤ ሰሞኑን ከኤርትራ ጦር መግባት/ መወጣት ጋር ተያይዞ ስለሰጠው አስተያየት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ስላሉ አማካሪዎች ብቃት፤ስለ ብሔር ፖለቲካ፤ ስለቋንቋ ፌደራሊዝም፤ ስለህገመንግስት መሻሻልና ስለሚከተለው ‹አወንታዊ የምርጫ ዘመቻ ምንነት› የቁም ነገር መፅሔት አዘጋጅ ታምራት ኃይሉ አነጋግሮታል፤

ቁም ነገር፡- ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በዚህ ዓመት ይካሄዳልና፤ ዘንድሮ እንዴት ለመወዳደር አሰብክ? አምና ቢደረግ ኖሮ ትወዳደር ነበር ወይስ ዘንድሮ የመጣ ሀሳብ ነው?

ዲያቆን ዳንኤል ፡- አምናም ቢካሄድ ኖሮ ሀሳቡ ነበረኝ፤ እሳተፍ ነበር፤ ምርጫው ወደ ዘንድሮ በመሸጋገሩ ምክንያት የመጣ ሀሳብ አይደለም፡፡ አምና 2012 ነው ሙሉ ቁጥር ነው፤ ዘንድሮ 2013 ጎዶሎ ነው በሚል ነገር የማምን  ሰው አይደለሁም፡፡

ቁም ነገር፡- ከምርጫው ምን ተስፋ ታደርጋለህ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እንግዲህ የሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለኢትዮጵያ የማዕዶት ጊዜ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ማለትም ትልቅ የሽግግር ጊዜ ነው፤ ምርጫው ምናልባት ለብዙ ጊዜያት የተከማቹ ችግሮቻችንንና ሸክሞቻችንን የምናወርድበት ጊዜ ይሆናል፡፡ በሀገሪቱ የተከማቹ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት የምንደረደርበት ጊዜ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡እናም ወደ እንደዚህ አይነት ጉዳይ ውስጥ የገባሁት የተቻለኝን ያህል አስተዋፅኦ አድርጌ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ ነገር ትቶ ለማለፍ በሚል ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ሀሳቡ ቀድሞውኑ  የነበረህ በግልህ ለመወዳደር ነው ወይስ በፖለቲካ ፖርቲ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡- እኔ የፖለቲካ ፖርቲ አባል የመሆን ፍላጎት ድሮም ጀምሮ የለኝም፤ በፖርቲ ዲስፕሊን መታሰር አልወድም፤ ለዚህም ነው በግሌ የምወዳደረው፡፡ የፖለቲካ ሀሳቦች አሉኝ፤ ግን  በፖለቲካ ፖርቲ ውስጥ ገብቼ አይደለም ያንን ሀሳቤን ማራመድ የምፈልገው፡፡

<የአውሮፓ ህብረት“ሉዓላዊነት የሚዳፈር” ስራ እንዲሰራ ስላልተፈቀደለት የመታዘብ እቅዱን ሰርዟል-ኢትዮጵያ>

ቁም ነገር፡-የፓርቲ ዲስፕሊኑን ፍራቻ ነው?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ፍራቻ አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ የሆነ የፖለቲካ ፖርቲ አባል ሆነህ ሀሳብ አቅርበህ ተከራክረህ አሳምነህ ተችተህ ወደ ተሻለ ነገር ለመሄድ የፖለቲካ ፖርቲዎቻችን አፈጣጠር አይፈቅድላቸውም፤ የተሻለ የምትለው ሀሳብ እዚያኛው ፖርቲ ውስጥ ካለ ያንን ጥሩ ነው ለማለት አትችልም፡፡ እንዴት ? ትባላለህ፤የአንድ ፖርቲ አባል ሆነህ ከሌሎች ፖርቲ ሰዎች ጋር መታየት አትችልም፤ አሁን አንዳንድ ሰዎች የሚገመገሙበትን ነገር አያለሁ፡፡ ዲያቆን ሆነህ እንዴት ቤተ መንግስት ገባህ ትባላለህ፤ አንድ ቦታ ከታየህ ሌላ ቦታ መታየት የለብህም ትባላለህ፤ ሳሎን ከገባህ መኝታ ቤት ምን ታደርጋለህ እንደማለት ነው፤ይህ ትክክል አይደለም፤ከዚህ አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ገና አልወጣንም፤ ለምሳሌ አንተ የብልጽግና አባል ሆነህ በኢዜማ ውስጥ ጥሩ ነገር አይተህ  ብናትገር ምን ችግር አለው?

ቁም ነገር፡-ምንጩ ምንድነው ትላለህ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እንግዲህ ብዙዎቹ የሀገራችን  የፖለቲካ ፖርቲዎችን የኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለምን መሠረት አድርገው የተመሰረቱና የሚንቀሳቀሱ ናቸው፤ ማዕከላዊ ኮሜቴ፤ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምናምን እያሉ የሚሰሩ ናቸው፤ጠቅላላ መዋቅራቸውና አሰራራቸው ሶሻሊስታዊ ናቸው፡፡ምናልባትም ምርጫው ከእንደዚህ አይነት ነገሮች ሁሉ ሊያላቅቀን ይችላል በቀጣዮቹ ዓመታት ብዬ ነው የማስበው፡፡እና አንተ በእነዚህ ፖርቲዎች ውስጥ ከገባህ ስራ አትሰራም ማለት ነው፤ስለ ስራ ው ሳይሆን ስለአሰራሩ ስትከራከር ቀኑ ያልቃል አባል ብትሆን ማለት ነው፡፡እና ለዚህ ነው የፖርቲ አባል ያልሆንኩት፤ እነርሱንም አስቸግራለሁ እኔም እቸገራለሁ፤

ቁም ነገር፡-ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲ ሳለህ ዘመቻ ሄደህ ነበር፤ ያን ግዜም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ አልገባህም?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የፖለቲካ ፖርቲ ውስጥ ምንም ተሳትፎ አልነበረኝም ያኔም ቢሆን፡፡የፖለቲካ ፖርቲ የሆነ ሰው የሆነ የሚተለው ርዕዮተ ዓለም አለ፤ያንን ለማሳካት ነው የምትሞክረው፡፡ እኛ ሀገር እንደውም ሲቪክ ድርጅቶች ሊሰሩት የሚገባውን ስራ ነው የፖለቲካ ፖርቲዎች ሲሰሩት የምትመለከተው፡፡ የፖለቲካ ፖርቲዎች ሊሰሩ የሚገባቸውን ደግሞ ሲቪክ ድርጅቶች ሲገቡበት ታያለህ፡፡ ሁሉም የየራሱን መስመር ይዞ ቢሄድ የሚታሰበው ግብ ላይ ለመድረስ ይቻላል፡፡ የአንዳንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ሲቪክ ድርጅት እንቅስቃሴ ወስጥ ታገኛቸዋለህ፡፡ለምሳሌ በቋንቋ መጠቀም መብት አንድ ጊዜ በህገ መንግስት ውስጥ ካስገባኸው በኋላ የፖለቲካ ስራ መሆን የለበትም፤ የሲቪክ ድርጅቶች ስራ ነው ያንን ማሳደግና ጥቅም ላይ  እንዲውል፤ የፅሑፍ ቋንቋ እንዲሆን ማስደረግ፡፡መንግስት ሲቪክ ድርጅቶች ያንን ስራ በተጠናከረ መልኩ እንዲሰሩ በበጀት በሰው ሃይል መደገፍ ነው ያለበት፡፡አነስተኛ ተናጋሪ ያላቸውን ቋንቋዎች ያሉዋቸው እንዲያድጉ ከፍ ያለ በጀት ስትመድብ ብዙ ባለሙያዎች  ያንን ወደ ማጥናትና የማሳደግ ስራ ይሰራሉ፤ ለምሳሌ በአሜሪካ ከተለያየ የዓለም ክፍል መጥተው የሚኖሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ማህበረሰቦች ራዲዮ ጣቢያ ቢያቋቁሙ ኮሚኒቲ ሲመሰርቱ ድጋፍ ይደረግላቸዋል በመንግስት፤ ምክንቱም ያ ቋንቋ እንዳይጠፋ ለማድረግ ነው፡፡በአውስትራሊያ ደግሞ ቤተክርስቲያን እንኳ እነዚህ አነስተኛ ማህበረሰቦች ሲያቋቁሙ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ከሌሎቹ ጋር  መወዳደር አይችሉም በሚል ማለት ነው፡፡ እኔም የሲቪክ መብቶች ላይ እና  ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ነው በስፋት የምንቀሳቀስው፡፡በነዚህ የተነሳ የሆነ የፖለቲካ ፖርቲ ደግፌ የሆነ የፖለቲካ ደርጅት ተቃውሜ መቆም አልችልም፤

ቁም ነገር፡- አሁን የመጣኸው የግል ተወዳዳሪ ሆነህ ነው፤ የኢትዮጵያ ችግር በግል ተወዳዳሪ እጩዎች ይፈታል ብለህ ታስባለህ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የኢትዮጵያ ችግር በፖለቲካ ፖርቲዎች ብቻም አይፈታም፤ ችግሯ ከፖርቲዎቹም በላይ ነው፡፡በፖርቲዎች ካልተፈታ በግለሰቦችም አይፈታም ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ፖርቲዎች ታሪክ በኢትዮጵያ የ50 ዓመት ታሪክ አለው፤ ከአፄ ሀይለስላሴ መንግስት መውደቅ በኋላ የመጣ ነው፡፡ በዚህ 50 ዓመት ችግራችንን ሊፈቱት አልቻሉም፡፡ ችግራችን በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት የሚፈታ ነው፤ የሆነ ጊዜ የመሬት ጥያቄ በመሬት ላራሹ ተፈታ፤ የሆነ ጊዜ የብሔር ጥያቄ ለመፍታት ተሞከረ፤ የሆነ ጊዜ  የሆነ ችግር ይፈታል እያለ ነው የሚሄደው እንጂ በአንድ ጊዜ አይፈታም፤ የኢትዮጵያ ችግር በሂደት የሚፈታ ነው የምንለው ለዚህ ነው፤ ግን  ሂደቱ የሆነ ቦታ መጀመር አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በሁሉም ሀይሎች ቅንጅትና ትብብር ነው፡፡የኢትዮጵያ ህመምን እንደ ሀበሻ መድሃኒት በአንድ አዋቂ ብቻ ይፈወሳል ማለት አይደለም፡፡ ችግራችን የሚፈታው አንዱ በፖለቲካ ፖርቲዎች ነው፤ ሌላው በሲቪክ ድርጅቶች ነው፤ ሌላው በግለሰቦች ነው፤ ሌላው በማህበራት፤ በነጋዴዎች እያለ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

<የዝሆኖቹ ፍልሚያ የት ድረስ ይዘልቃል?>

ቁም ነገር፡- አሁን በግል ነው የምትወዳደረው፤ ያለህ የመንግስት የስራ ሀላፊነት ደግሞ ብልፅግና ፖርቲን ነው የምታማክረው፤ ከዚህ አንጻር ብልፅግናን ነው የምትፎካከረው ማለት ነው?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እኔ ከማንም ጋር ተቃርኜ አልወዳደርም፤ የተሻለ ሀሳብ አለኝ ብዬ ነው የምቀርበው፤ የተሻለ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች ይመርጡኛል ብዬ ነው የማስበው እንጂ አንዱን ተቃውሜ ሌላው ተፎካካሪ ሆኜ አይደለም፡፡እኔ ከሌሎቹ እበልጣለሁ ብዬ እዚህ ወስጥ የገባሁት ባለኝ የሀሳብ የበላይነትና ልዕልና ነው እንጂ በመቃወምና በመቀናቀን ስሜት አይደለም፡፡ለምሳሌ አልጫና ቀይ ወጥ ቢቀርብልህ አልጫውን ትተህ ቀዩን አወጣህ ማለት እኮ ቀዩ ዋጋ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ለጊዜው አንተ አልጫውን መርጠሃል፤ ቀዩን ደግሞ መርጦ የሚያወጣ ይኖራል ነው የእኔ መርህ፡፡እንጂ ቀዩ ስለማይጣፍጥ ነው ብዬ አልከራከርም፡፡አውንታዊ የምርጫ ዘመቻ ነው አደርጋለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡

ቁም ነገር፡-ምን ማለት ነው አውንታዊ ማለት?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እኔ የተሻለ ሀሳብ አለኝ ብዬ እቀርባለሁ፤ ሌላው መጥፎ ይሁን አይሁን የሚወስነው ህዝቡ ነው፤ እኔ ግን የተሻለ የሀሳብ የበላይነት አለኝ ብዬ አስባለሁ፡፡

ቁም ነገር፡-ግን ለምርጫ ክርክር ላይ ስትቀርብ ከሌሎች በተሻለ ህዝቡ አንተን እንዲመርጥ ለማድረግ የሌሎችን ድክመት ጠቅሰህ መከራከርህ  ይቀራል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የእኛ ሀገር የምርጫ ህግ እኮ የፖለቲካ ፖርቲዎች እንጂ የግል ተወዳዳሪዎች የሚከራከሩበት መድረክ የላቸውም፤ ስለዚህ ክርክር ውስጥ የሚያስገባኝ ጉዳይ የለም፡፡

<የተናቀው ኮሮና ቫይረስና አስደንጋጭ ውጤቱ>

ቁም ነገር፡-ታዲያ እነዚያ ሰዎች ከሌሎች አንተን የተሻልክ መሆንህን አውቀው እንዴት ይመርጡሃል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የተሻለ ሀሳብ እንዳለኝ አስረዳለኋ፤

ቁም ነገር፡-እንዴት?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እሱንማ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሀሳቤን አቀርባለሁ፤ ቅድም እንዳልኩህ እኮ ነው፤ አልጫና ቀይ ወጥ ይርብለታል ህዝቡ፤ የተሻለ ብሎ የሚያስበውን ወጥ ያወጣል ፤የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር የሚፈታው በዚህ መልክ ነው ብዬ እኔ የራሴ አቀርባለሁ፤ ሌላውም የራሱን ያቀርባል፤ ህዝቡ የመረጠውን ያወጣል፤ የግድ የእኔ የተሻለ ነው ስል የሌላው አይረባም እንድል መጠበቅ የለበትም፡፡ ህዝቡ የሚረባውንም የማይረባውንም ያውቃል፡፡

ቁም ነገር፡-ይሄ አባባልህ የፖለቲካ ክርክር አስፈላጊ አይደለም ማለትህን አያሳይም?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የፖለቲካ ክርክር የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችና መከራከር ያለባቸው አካላት ይኖራሉ፡፡እነርሱ ይከራከሩ፤ ግን ስለምርጫ ውድድር ሲነሳ የግድ አንዱ አንዱን ጠላት አድርጎ የማቅረብ ባህላችን ትክክል አይመስለኝም፤ የግድ አይደለም ማንኛውንም ነገር በሁለት ከፍሎ ማስቀመጥ፤ ጥቁር ወይም ነጭ ብቻ አድርጎ ማቅረብ፤ስለዚህ ክርክር ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑ ሰዎች መድረክ አዘጋጅተው ወይም የተዘጋጀ መድረክ ላይ ሄደው ሊከራከሩ ይችላሉ፡፡ ክርክር አያስፈልግም ያለ ደግሞ  በመረጠው  መንገድ የምርጫ ዘመቻውን ያካሂድ፡፡ የእኔ የምርጫ ዘመቻ ያንን አይፈልግም፡፡የተሻለ የምትለውን ሀሳብ ብቻ ገበያ ላይ አቅርበው፤ ህዝቡ መርጦ ይገዛል፤ ብቻ አንተ የተሻለ የምትለውን ሀሳብ አምርት፡፡ሌላውን ማጣጣል አይጠበቅብህም ብዬ ነው የማስበው፡፡የእኔ አካሄድ የተሻለ ሀሳብ እንዳለኝ ማቅረብ ላይ ነው የሚያተኩረው እንጂ ሌላውን በማጣጣል ላይ አይደለም፡፡

ቁም ነገር፡-ንፅፅሩ በግልጽ ካልቀረበ የተሻለው ሀሳብ እንዴት ይታወቃል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እርሱን መስራት ያለበት እኮ ህዝቡ ነው፤ ገበያው ላይ ያለውን ሁሉ ከሰማ በኋላ አንተ አይደለህም የምትመርጥለት፤ ራሱ ያንን እርምጃ ይወስዳል፡፡ ሰዎች ያንን ውሳኔ የሚወስኑት በማነፃፀር ነው? በማወዳደር ነው ወይስ በአስተያየት ነው? የሚለውን ራሳቸው ይወስናሉ፡፡

ቁም ነገር፡- ግን  ይህን ለመመርመርና ለመወሰን የሚችል ንቃተ ህሊና ላይ ያለው ምን ያህሉ ህዝብ ነው?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እኔ የምወዳደርበት ወረዳ ላይ ያሉት ሰዎች በአብዛኛውን ያንን ነገር ለማድረግ የሚቸገሩ ናቸው ብዬ አላስብም፤ መመርምርና መወሰን የሚችሉ ናቸው፡፡ከወረዳው ህዝብ ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገናኝቻለሁ፤ እናም ለአወንታዊ የምርጫ ዘመቻ ራሳቸውን ያዘጋጁ ናቸው፡፡

ቁም ነገር፡-ግን ለሚነሱብህ መሰል ጥያቄዎች የምትሰጠው ምላሽ ምን ይሆናል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የእኔ አካሄድ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ በዋናነት መልስ ባለመስጠት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ቁም ነገር፡-በምንም ጉዳይ ላይ ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-በጣም መሠረታዊ ናቸው በምላቸው ጉዳዮች ላይ ካልሆነ በስተቀር ምንም ምላሽ አልሰጥም፤ የእኔ የእስካሁን አካሄድ የሚያሳየው ይህንን ነው፡፡ እስካሁን ለተነሱት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ በመስጠት ላይ አተኩሬ ቢሆን ኖሮ ምንም አይነት ስራ አልሰራም ነበር፡፡

ቁም ነገር፡- የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ላንተ ድምፃቸውን የሚሰጡህ ዓላማህ ምን ስለሆነ ምን ስለምታደርግላቸው ነው?

<ይልቅ ወሬ ልንገርህ:- ስለ ታማኝ በየነ ‹ሿ ሿ›>

ዲያቆን ዳንኤል ፡-በጣም ጥሩ፤ በሶስት ነገሮች ምክንያት ድምፅ ይሰጡኛል ብዬ አስባለሁ፡፡አንደኛ እስካሁን ድረስ ያገኘሁትን ልምድ መሠረት በማድረግ እንዲሁም ያለኝን አጋጣሚ ተጠቅሜ ለወረዳ ህዝብ የተሻለ ነገር ልሰራለት፤ ችግሩን ልፈታ እችላለሁ፤ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ ብዙ መንግስታዊ መዋቅሮችን አውቄያለሁ፤ ከብዙ መንግስታዊ ተቋማት ጋር በተለያየ  አጋጣሚ  ሰርቻለሁ፡፡አብዛኛዎቹ የልማትም ሆነ የኢኮኖሚ ችግሮቻችን ውስብስብ የሆኑት በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ባሉ ጥልፍልፎች ምክንያት ስለሆነ ያንን በዘረጋሁት መረብ አማካይነት ችግሮቹን ልፈታ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት የማይፈቱትን ችግሮች ደግሞ ብዙ የእርዳታ ድርጅቶችን፤ የሲቪክ ድርጅቶችን፤ በጎ አድራጊ ድርጀቶችን ወይም ግለሰቦችን በተሻለ መልኩ  ስለማውቅ የተሻለ ነገር እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ፤ለመፍታት እሞክራለሁ፡፡ እስከ ዛሬ  በነበረኝ ልምድና ከዚያም በፊት ባለኝ ልምድ ያንን አደርጋለሁ፡፡ሁለተኛ ከኢትዮጵያ ውጭ ብዙ ግንኙነት አለኝ፤ በጣም ብዙ ሀገሮች ዞሬያለሁ፤ ብዙ ሰዎችን አውቃለሁ፡፡ በዚህ ጉዞዬ ያላየሁት አህጉር አንታክቲካ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዕድል ተጠቅሜ ያወኳቸውን ሰዎች ኢትዮጵያውያን፤ የኢትዮጵያ ወዳጆችና ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት ያላቸው ሰዎችን ተጠቅሜ ኢኮኖሚያዊ በለው፤ ማህበራዊ በለው፤ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት በወረዳውና በእነዚህ አካላት መሀል ሆኜ ለዚህ በጎ ዓላማ ለመጠቀም የተሻለ አቅም ይፈጥርልኛል፡፡ ሶስተኛ የየካ ክፍለ ከተማ ህዝብ ለእኔ ድምጻቸውን ሲሰጡ እንደ ወረዳ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ይጠቅማል የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው ስለሆነ እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊ ባህሎችና ኢትዮጵያ እሴቶች እንዲያድጉና ጥቅም ላይ እንዲውሉ እና የሀገሪቱ ፖሊሲዎችና ህጎችና መመሪያዎች ውስጥ እንዲካተቱ  ፖርቲዎቹም ለእንደነዚህ አይነት ጉዳዮች ዕድል እንዲሰጡ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ከህዝቡ ጋር ስንወያይም እንደ በጎ ጎን ያዩት ይህን ነው፡፡

ቁም ነገር፡- ግን አሁን ልሰራ እችላለሁ ካልከው በላይ በተጨባጭ ምን መሬት ላይ  የወረደ ስራ ሰርተሃል ብሎ ለሚጠይቅህስ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እሱንማ የወረዳዬ ህዝብ እኮ ያውቀዋል፤ ምን እንደሰራሁ እንዴት እንደሰራሁ  በቢሮክራሲው ውስጥ ያውቃሉ  ፡፡ ምን ያህል ችግሮቻቸውን ስፈታ እንደነበር ያውቃሉ፡፡ ከወረዳው ውጭ ያሉ ሰዎችም ስለ እኔ ያውቃሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ብዙ የቀበሌዎችን ብዙ የክፍለ ተሞችን ችግሮች በመፍታት በኩል ያደረኩትን ጥረት ያውቃሉ፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ነው፤ አይደለም የአካባቢዬ ሰዎች የሌላ ክልል ሰዎችም ጭምር ያውቃሉ ምን እንደሰራሁ፡፡

ቁም ነገር፡- የመጀመሪያ የምርጫ መተዋወቂያ መድረክህ በቅርቡ በካፒታል ሆቴል አካሂደሃል፤ የምርጫ ዘመቻህን በምን መልኩ ለማስኬድ ነው ያሰብከው?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እንግዲህ እኛ ምርጫ ዘመቻ ስናደርግ እንደ መርህ እናደርጋቸዋልን ብለን የያዝናቸው ነገሮች አሉ፡፡የመጀመሪያው የላቀ የምርጫ አካሄድን መጠቀም አለብን ብለን እናስባለን፡፡  ከህዝቡ ንቃተ ህሊና ጋር አብሮ ከፍ ብሎ የሚታይ መሆን ይኖርበታል ዘመቻው፡፡ከተለመደው አካሄድም የተለየ ለማድረግ ነው እቅዳችን፡፡ ፈጠራ የታከለበትም መሆን ይኖርበታል፡፡ከዚህ ሌላ ዘመቻው አወንታዊ ዘመቻ መሆን ይኖርበታልን ፡፡ያም ሆኖ አሁን ያለንበት ወቅት የኮቪድ ወቅት ስለሆነ ይህንኑ ከግምት ባስገባ መልኩ ነው ዘመቻው የምናደርገው፤  እያንዳንድዱ ሰው ቤት ለቤት የሚደርስ ዘመቻ ነው ያቀድነው ፤ ያንን ለማድረግ ውጤታማ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ የኮቪድ ሁኔታ ፕሮግራማችንን የማያስተጓጉልብን ከሆነና ካልታገደ  አምስት ስድስት ህዝባዊ መድረኮንም አቅደናል፡፡

ቁም ነገር፡- አሁን ያለውና ያለፈው ሶስት ዓመት  የሀገራችን ፖለቲካ ባንተ ዕይታ ያለው ንፅፅር ምን ይመስላል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እንግዲህ እያንዳንዱ ዘመን የየራሱ እሴትና የየራሱ ድክመትን ይዟል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሁሉንም ነገር በአንድ ቅርጫት ውስጥ አስቀምጠህ እንዲህ ነው ላትለው ትችላለህ፡፡የአጼ  ኃይለስላሴ መንግስት የራሱ የሆኑ ጠንካራ ጎኖች ነበሩት፤ በተለይ ትምህርትን በማስፋፋት፤ በአፍሪካዊ ጉዳዮች ላይ፤የኢትዮጵያን ዘመናዊነት በማስቀጠልና አሁን አሉን የምንላቸውን ተቋማት በመመስረት በኩል ጥሩ ጥሩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ሀገራችን ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ጋር ያላትን ግንኙትን በማጠናከር በኩል ጉልህ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡በኢኮኖሚውም ዘርፍ ሰፋፊ የመንግስት እርሻዎች የተጀመሩበት በኋላ ደርግ ቢወርሳቸውም የተለያዩ እቅዶች ታቅደው ወደ ስራ የተገባበት ወቅት ነበር፡፡የአክሲዮን ገበያ ሁሉ እስከመክፈት የተደረሰበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ በኩል  የዲሞክና የሰብዓዊ መብቶችን በማክበርና የብሔሮችን እኩልነት በማረጋገጥ በኩል ድክመቶች ነበሩ፡፡በደርግ ጊዜ ደግሞ በጦርነት ውስጥ ሆኖ እንኳ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ለማምጣት የተደረገው ጥረት፤ የመሠረት ትምህርት ዘመቻን በማስጀመር ውጤት የማስመዝገቡን  እና የኢትዮጵያ አንድነት ላይ የነበረውን አቋም ስትመለከት እንደ ጠንካራ ጉዳዮች ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ብዙ ችግሮችን በሀይል ለመፍታት መሞከሩ ደግሞ ራሱን በራሱ ጠልፎ ለመጣል አብቅቶታል ብዬ አስባለሁ፡፡በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ተጨፍልቋል የተባለውን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለመመለስ ባህላቸውን ቋንቋቸውን ለማሳደግ ሙከራ ተደርጓል፤በትምህርት በጤናና በመንገድ መሠረት ልማቶች ላይ በበጎ ጎኑ ሊታዩ የሚችሉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የተፈፀሙ በርካታ ግፎች አሉ፡፡ የግለሰቦችን መብቶች በመጨፍለቅ ለቡድን መብቶች ሰፊ ቦታ መስጠት አካባቢያዊነት ከሀገርራዊነት በበለጠ እንዲቀነቀን አድርጓል፡፡ይህም ህዝባዊ ቁጣ ቀስቅሶ አሁን ወዳለው ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል፡፡ ያለፈውን ሶስት ዓመታት ሂደት የተመለከትን እንደሆነም ለሃያ ዓመታት በውጥረት ላይ የነበረውን የኤርትራን ጉዳይ ለመፍታት የተሄደበት መንገድ፤ ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ ለመስራት የተሞከረበት ሂደት፤የሚዲያ ምህዳሩን ለማስፋት ብዙ ተሞክሯል፡፡ከሚዲያ አንፃር ከአንድ ራዲዮ ስንት እንደደረሰ፤ ከአንድ ቴሌቪዥን አሁን ስንት እንደደረሰ፤ የፖለቲካ ምህዳሩንም  ለማስፋት የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመፍታቱን ሁኔታ  ስታይ ለውጥ መኖሩን ታያለህ፡፡ በሌላ በኩል ፅንፈኝነት የገነነበት፤ መገዳደል የዘወትር ዜና የሆነበት፤ሀሰተኛ መረጃዎች ደግሞ በስፋት እየተሰራጨ ለሰላሙ መደፍረስ የራሱን አስተዋፅኦ ያደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ በየዘመናቱ ጥንካሬም ድክመትም አለ፤ ከዚህ አንፃር ካለፈው ጥሩ ጥሩ የሚባለውን እያጎበቱ ድክመቱን እያረሙ መሄድ እንጂ ሁልጊዜ እያፈረስን የምንሄድ ከሆነ የተሻለ ነገር አናገኝም፡፡ ሀገር ልክ እንደ መኪናህ ሰርቪስ መደረግ አለባት፤ መኪናህን እየነዳሃት የሆነ ነገር ከጎደለ ታስተካክለዋለህ፤ የተበላሸ ዕቃ ካለ ይቀየራል፤ የጎደለ ዕቃ ካላ ይተካ፤ ሰርቪስ ደረጋል ጉዞ ይቀጥላል፡፡ፍሬን ሸራ መቀየር ካላብህ ትቀይራለህ፤ ዘይት መቀየር ካላብህ ትቀይራለህ እንጂ ሞተሩን አውጥተህ አትጥልም፡፡ቀጣዩ  አምስት ዓመታት ምርጫው በሰከነ መንገድ ከተከናወነ ስለወደፊቱ በፅሞና የምናስብበት ጊዜ ይሆናል ብዬ ነው የማስበው፡፡ የትኛው ይቅር የትኛው ይቀጥል ለማለት አመቺ ጊዜ ይሆናልው ብዬ ነው የምገምተው፡፡

<ኡጋንዳና ግብፅ “በወታደራዊው መረጃ” ልውውጥ መስክ ለመተባበር ተስማሙ>

ቁም ነገር፡- ግን የወቅቱ የሀገራችን ሁኔታ ተስፋ የሚሰጥ ነው ወይስ ስጋት የሚያጭር ነው ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ከምን አንፃር?

ቁም ነገር፡-ለምሳሌ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ከማድረግ አንፃር መቅደም ያለበት እየቀደመ ነው ማለት ይቻላል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-መቅደም ያለበት ምንድነው?

ቁም ነገር፡-ለምሳሌ ከምርጫው በፊት የዜጎች ደህንነትን ማስቀደም ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-በእኔ እምነት ይሄ ቀርቶ ይሄ ብቻ ቢሆን የሚባለው አካሄድ ትክክል አይመስለኝም፤ ሀገር ስትመራ ሁለቱንም በአንድነት ማስኬድ ይቻላል፡፡ምርጫ እያካሄዱ እኮ የህግ የበላይነትን ማስከበር ይቻላል፡፡ እንደ መንግስት እኮ ካሰብክ ምርጫን አለማድረግ ነው የሚሻለው፡፡ስጋት አለ እያለ ምርጫ ሳያደርግ ስልጣን ላይ ይቀመጣል፡፡ ሁሉንም በየልኩ ካየነው ከእንቁላልና ከዶሮ ማን ቀድማል አይነት እሽክርክሪት ውስጥ ነው የምንወድቀው፡፡ ምርጫውን መንግስት ትቶ ህግ ብቻ ላስከብር ብሎ ሰዎችን ቢያስር አንተ ማነህና ነው ሰዎችን የምታስረው ይባላል፤ እሺ ምርጫ እናካሂድና አሸናፊው ሀላፊነቱን ይያዝ ሲል ደግሞ ምርጫ አያስፈልግም ትባላለህ፤

ቁም ነገር፡-መንግስት እኮ እንደ መንግስትነቱ መስራት ያለበትን ስራ አይስራ የሚባል አይመስለኝም፤ ጥያቄ የሚቀድመው የቱ ነው መሰለኝ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ከመንግስት ስራዎች መሀከል አንዱ እኮ ምርጫ ስለሆነ ነው ምርጫን የሚያካሂደው፤ መንግስት ምርጫ ሲያካሂድ ህግ ማስከበሩን ትቶ ወይም ህግ ማስከበሩን ሲሰራ ምርጫውን ዘግቶ መሆን አለበት የሚለው ነው ትክክል ያልሆነው፡፡መሰራት ያለበት ስራ እየተሰራ ነው ምርጫ መካሄድ ያለበት፡፡ ባለፈው እንደውም ኮረና መጥቶ አስቀረው እንጂ ምርጫው የግድ መካሄድ ነበረበት፡፡ ስልጣን ከህዝብ የሚሰጥ ኮንትራት ነው፤ በዚያ ጊዜ ውስጥ መካሄድ ያለባቸው ነገሮች መካሄድ አለባቸው፡፡ እኔ በዚህ በኩል ወደ አንድ ፅንፍ ከሚሄዱ ሰዎች እለያለሁ፡፡ መንግስት በህግ የተሰጡትን ስራዎች ሁሉ እየሰራ ነው መቀጠል ያለበት፡፡ እዚህ ሀገር ያለው መረጃ ልክ እንደ ትራፊክ ሪፖርት ዜና እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ሚሊየን በላይ መኪናዎች አሉ፡፡ በየዕለቱ ዜና ስትሰራ ሰላሳ አርባ መኪናዎች ተጋጩ፤ ይህን ያህል ሰው ሞተ የሚል ዜና ትሰማለህ፡፡ ዛሬም ነገም፤ ከነገ ወዲያም ያ ዜና አለ፤ ግን ያንን አደጋ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ መኪናዎች አንፃር ካየኸው የሰላሳና አርባ መኪናዎች ችግር ነው፡፡ ሌሎቹ አንድ ሚሊየን ያህል መኪናዎች በሰላም ወጥተው ወደ ቤታቸው ገብተዋል፡፡ ዜናው ግን ያ አደጋው ደረሰበት ላይ ብቻ ስለሆነ ሀገሪቱ ሰላም የሆነች  አይመስልም፡፡ አንድም ሰው ላይ አደጋ መድረሱ ትክክል ነው ባይባልም ግን መላ ሀገሪቱን ጨለማ አድርጎ የማቅረግ ሁኔታ አለ፡፡

ቁም ነገር፡- ችግሩ እኮ ንፅፅሩ አይመስለኝም፤ የችግሩ እየባሰ መሄድ እንጂ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-እኔ ደግሞ እየባሰ ነው የሚል ግምት የለኝም፡፡

ቁም ነገር፡-እየባሰ አይደለም?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-በምን ዳታ ፤ በምን መረጃ? ፤ በፊት ይህን ያህል ነበር፤ አሁን ደግሞ በዚህን ያህል ጨምሯል ወይም ቀንሷል የሚል ዳታ የለም፡፡እየባሰ የሚሄድ ቢሆን መላ ሀገሪቱ በእሳት ነበር የምትቀጣጠለው፡፡ያልተፈቱ ችግሮች አሉ ወይ? አዎ አሉ፤ እየተፈቱ ያሉ ችግሮች አሉ? አዎ ፤ ግን ሁሉም ነገር የተባባሰና ጨለማ ነው ወደሚል የሚወስድ አይመስለኝም፡፡ የዛሬ አስር ዓመት እኮ ችግር ስላልነበረ አይደለም የባሰ ነገር እንደነበረ የማንናገረው፤ ያንን በወቅቱ የነበረውን ችግር የሚነግርህ ሚዲያ እንዳሁኑ ስላልነበረ ነው፡፡ ያኔ የነበሩት ሚዲያዎች ኢቲቪ ነው፤ ፋና ነው፤ ዋልታ ነው፤ ዛሬ ግን ብዙ ሚዲያ ስላለና ብዙሃኑም  በየራሱ ስለሚዘግብ ብዙ ችግር ያለ ይመስልሃል፡፡ ዛሬ ማንም ሰው በያዘው ሞባይል ስልክ የሆነ የፈለገውን ፅፎ ይለጥፋል፤ ያ ሁሉ ታዲያ እውነት ነው ማለት አይደለም፡፡ ይሄ ጉዳይ በዝቷል፤ አልበዛም፤ ከማለት በፊት ጥናት ያስፈጋል ባይ ነኝ፡፡

ቁም ነገር፡-ግን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ተከታትለው ሪፖርት ለማድረግ በሚል በመንግስት ራሱ የተቋቋሙ እንደ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አይነት ተቋማት የዜጎች ሰብኣዊ መብት ከምንጊዜውም በላይ አደጋ ላይ መውደቁን የሚጠቁሙ ተደጋጋሚ ሪፖርት እያወጡ አይደለም?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ኢትዮጵያ እውነተኛ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ያቋቋመችው  መቼ ነው? መስማት የተሳነው ሰው መስማት የጀመረ እለት ያብዳል ይባላል፤ አሁን ከምንሰማው ሪፖርት በላይ እኮ የባሱ የመብት ጥሰቶች የነበሩበት ሀገር ላይ ነበርን፤ ያኔ ስላልተነገረ፤ ሪፖርት ስላተደረገ ነው እንጂ፡፡ ያን ጊዜ ይወጣ የነበረውን የሰብኣዊ መብት ሪፖርት ሁሉም ያውቃል፤ አሁን ትክክለኛው ነገር መነገር ሲጀመር የተለየ ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ስለዚህ እየባሰ ነው በሚለው አልስማማም የምለው ለዚህ ነው፡፡ እየባሰ ነው ማለት ከአንድ ሁለት ከሁለት ሶስት እያለ እየጨመረ ሲመጣ ነው፡፡ አሜሪካ ሀገር እኮ አንድ ሰው ትምህርት ቤት ገብቶ የተወሰኑ ተማሪዎችን ይገድላል፤ ያ እንደ ወንጀል ዜና ይዘገባል እንጂ ሀገሪቱ ፈረሰች የሚያሰኝ ነገር የለውም፡፡ በብዙ መቶ ሚሊዮኖን የሚቆጠሩ ሰዎች እኮ በእዛን እለት በሰላም ወጥተው ገብተዋል፡፡ቅድም አንስቻለሁ፤ እኛም ሀገር ችግር የለም አላልኩም፤ ግን ያ ችግር ሀገሪቷን እየፈረሰች ነው የሚያሰኝ አይደለም ነው፡፡ሀገሪቱን ወደ ቀውስ እየወሰዳት ነው ወይ? አይመስለኝም ነው እያልኩ ያለሁት፡፡

ቁም ነገር፡-ችግሩን የመፍታት ጊዜው ወይም  መንገዱ መርዘሙስ ምን ያሳያል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ነው የሚያሳየው፡፡ ይሄ ለውጥ የዛሬ ሶስት ዓመት ሲመጣ እኮ በመላው የሀገሪቱ ከፍተኛ  ሊባል በሚችል ሁኔታ ፈንጂ ነበር፡፡ ያ ፈንጂ ደግሞ ይፈነዳ የነበረው እንደ የአካባቢው መልክዓ ምድር አይነት ለማክሸፍም በማይቻልበት ሁኔታ ነበር፡፡የተቀበረው ፈንጂ በጣም ብዙ ነው፡፡ እስራኤል ከአረቦች ጋር ጋር ያደረገችወ ጦርነት ያለቀው በአጭር ቀናት ነው፡፡ በወቅቱ ለጦርነቱ ተብሎ የተቀበረው ፈንጂ ግን እስከ ዛሬ ድረስ ተለቅሞ አላለቀም፤ የሰዎችን ህይወት ይቀጥፋል፡፡ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ተቀብረው የነበሩት ፈንጂዎች ተለቅመው ያለቁት አሁን ከ50 ዓመታት በኋላ ነው፡፡በእኛም ሀገር ፈንጂው የተቀበረበትን ቦታ ማወቅ አንድ ነገር ነው፤ ያንን ፈንጂ ለማምከን መስራት ደግሞ ሌላ ሀላፊነት ነው፡፡ በእኔ እምነት ፈንጂዎቹ የት የት እንዳሉ ታውቀዋል፤ አሁን እንደውም ወደ አንድ አካባቢ የተቀበሩ እንደሆነ እየታየ ነው፤ ያንን መለየትና ማወቅ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ እሳት ለማጥፋት እኮ ሁለት ነገር ነው የምታደርገው፤ የመጀመሪው እሳቱን የሚያባብስ ነገር ከእሳቱ ጎን ማራቅ፤ ሁለተኛው ሙሉ ለሙሉ እሳቱን ሊያጠፋ የሚችል ኬሚካል ይዘህ መምጣት ነው፡፡ ይህኛውን ለማምጣት ጊዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል፤ እሳቱን የሚያባብሱት አካላት ግን ተለይተው የማባባስ ስራቸውን እንዳይሰሩ መንግስት ስራውን በብቃት እየሰራ ነው፡፡ተጨማሪ ማገዶ አቅራቢዎች ግን እየቀነሱ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡

ቁም ነገር፡-የእሳቱ ማጥፊያ እስኪመጣ ድረስ የጠፋው የሰው ልጅ የንፁሃን ህይወትስ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡- በጣም ያሳዝናል የምልህ ያን ነው፡፡ የአንድም ንፁህ ሰው ህይወት ማለፉ ያስቆጫል፤ መንግስት ስራውን እየሰራ ነው፤ እሳቱን ለማጥፋት እየጣረ ነው ብዬ ነው የማስበው፤

ቁም ነገር፡-መንግስት በህግ የተፈቀደ ሀይል የመጠቀም ሙሉ መብት ያለው አካል  ሆኖ ሳለ ያንን መጠቀም አቅቶት ነው እሳቱ ያልጠፋው ወይስ ስላልፈለገ ነው  የሚል ጥያቄ ያላቸው ወገኖች አሉ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡- እኔ ደግሞ ሀይል እየተጠቀመ ነው ባይ ነኝ፤የችግሩን ስፋትና ውስብስብነት ካልተረዳን ሀይል እየተጠቀመ እሳቱን እያተፋው ስለመሆኑ ለማወቅ አንችልም፡፡ ችግሩን ለመፍታት እየሞከረ ነው መንግስት፤ በሚፈለገው ደረጃ ችግሩን አልፈታውም ልንል እንችላለን፤ ግን አላቃተውም፤ ይፈታዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡

<“በአደባባይ ንግግርና ድስኩር የበለፀገ ሀገርና የተፈታ ችግር የለም” ላቀ አያሌው አንተነህ>

ቁም ነገር፡- በኢትዮጵያ አንዱ ትልቅ ችግር የብሄር ፖለቲካ  እንደሆነ ይነገራል፤ ያንተ አስተያየት ምንድነው?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-የብሔር ፖለቲካ ዋናው ችግር ሳይሆን አንዱ ችግር አድርጌ ነው የማስበው፡፡ትልቅ ነው ትንሽ ነው የሚለው እንደየግለሰቡ አስተሳሰብ ይለያል፡፡ እንደ እኔ የብሔር ፖለቲካ ሳይሆን ችግር የሆነው የብሔር ፖለቲካ የተመነዘረበት መንገድ ነው ፡፡ የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ የ50 ዓመት ታሪክ አለው፡፡የብሔር ጥያቄ መጠየቅ በራሱ ችግር አይደለም፤ ተጨባጭ ችግሮችም አሉ፤ የብሔሮች ፖለቲካ ከሶስት ነገሮች ጋር ተቆራኝቶ ነው ያለው፤ አንዱ ከፖለቲካ ፖርቲዎች አደረጃጀት ጋር፤ ሁለተኛው ከክልሎች መልክዓምድር አቀማመጥና የህዝብ አሰፋፈር ጋር፤ ሶስተኛው ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር፤ እነዚህ ሶስት ነገሮች የግድ አንድ ላይ መሆን አይገባቸውም፡፡ እኔ እንደውም መስተካከል አለበት ብዬ የማስበው ብሔረሰብንና አካባቢያዊ ማንነትን አንድ ላይ ማድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ብለህ ፈጥረህ፤ አማራ ክልል ብለህ፤ ትግራይ፤ አፋር ክልል ብልህ ሰዎች ይሄ የእኔ ክልል እንጂ ያንተ አይደለም እንዲሉ ማድረግ ነው፡፡የብሔሮችን መብት ለማክበር እኮ የግድ በእያንዳንዱ ብሔር ስም ክልል መመስረት አያስፈልግም፡፡ደግሞም አይቻልም፤የሌሎች ሀገራት የፌደራሊዝም አወቃቀር ይህን አያሳያም፤ ለምሳሌ ስዊዘርላንድ ብትሔድ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች አራት ክልልሎች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ የሁለት ቋንቋ ተናጋሪዎች በስምምነት አንድ ክልል ይመሰርታሉ፡፡ ጀርመንኛና ፈረንሳይኛ የስራ ቋንቋቸው ሆኖ በሰላም ይኖራሉ፡፡ ይሄ እኛ ሀገር እንዳይተገበር ችግሩ ምንድነው ?ኢህአዴግ የብሔረሰቦችን መብት ለመመለስ ያደረገው ጥረት ጥሩ ሆኖ የሄደበት መንገድ ግን ስህተት ነው፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ቋንቋ የሚናገር ህዝብ በአራት አምስት ክልሎች ውስጥ የመኖር መብቱ መገደብ የለበትም፡፡ቋንቋው የስራ ቋንቋ ከሆነ ሰርቶ መኖር ይችላል፡፡

ቁም ነገር፡-ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት አምስት ስድስት ቋንቋ በየክልሉ የስራ ቋንቋን ማድረግ ይቻላል? አዋጭ ይሆናል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ለምን አይሆንም፤ ሌሎች ሀገሮች ላይ ያለምን ችግር ተግባራዊ ሆኗል፤ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ 12 የስራ ቋንቋ ነው ያላት ፤ ቋንቋ ችግር ሆኖ አያውቅም፤ ችግሩ ያለው አስተሳሰባችን ላይ ነው፡፡ ዋናው ነገር በህግ እውቅና መንግስት መስጠጥ ብቻ ነወ የሚጠበቅበት፤ ከዚያ ውጭ ያለው የህብረተሰቡና የሲቪክ ድርጅቶች ስራ ነው የሚሆነው፡፡ ገበያ ላይ መንግስት ፈቅዶ ነው እንዴ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች መጥተው ተገበያይተው የሚሄዱት? ቋንቋ የሚያድገው በወታደርና በነጋዴ ነው፡፡ ቋንቋ ችግር ሆኖ አያውቅም፡፡ ቋንቀ ያለውን ጠቀሜታ እያዩ ማሳደግ  ይገባል፡፡ ወደው ነው እንዴ ሰዎች እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ የሚማሩት? ጥቅም ስላለው ነው፡፡ ጥቅም ባለበት ቦታ ላይ ሁሉ የቋንቋ ሙሑራን ጭምር ጥናት ማድረግ አለባቸው፤ ያኔ ቋንቋው ያድጋል፤ ይጎለብታል፤ እኛ ግን ከዚህ ጠቀሜታው አውጥተን ህገ መንግስቱ ውስጥ ስለሰነቀርነው ነው ችግሩ የገዘፈው፡፡ ህግ መንግስቱ ውስጥ መሻሻል አለባቸው ከምላቸው ጉዳዩች ውስጥ አንዱ የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡የብሄረሰቦችን መብት ለማስከብር የግድ ከቋንቋ ጋር ማያያዝ አይገባም፡፡

ቁም ነገር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄሮች ጥያቄ እንደነበር ይታወቃል፤ ኢህአዴግም ያንን ጥያቄ መልስ ነው ብሎ ነው የመጣውና የዚህ አይነት ህገ መንግስት ያወጣው፤ ግን የብሄር ጥያቄ፤ ከጨቋኝና ተጨቋኝ ብሄር ትርክት ጋር አልተላቀቅንም፤ ባንተ እምነት ጨቋኝ ብሔር አለ ኢትዮጵያ ውስጥ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-በፍጽም የለም፤ሊኖርም አይችልም፤ የኢትዮጵያ ብሄሮችን ጠባይም እንደዛ እንዲሆኑ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ያ ቢሆንማ ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የታጠቀና በኢኮኖሚ የበለፀገ ማንም የማይደርስበት አንድ ብሔር ይኖር ነበር፤ ግን የለም፡፡ መሬትም ፋብሪካም ኢንዱስትሪም በአንድ ብሔር ቁጥጥር ስር ይኖር ነበር፤ለመሆኑ በአማራና በኦሮሞ ገበሬ መሀከል ምን ልዩነት አለ? በኦሮሞና በትግሬ? በትግሬና በጉራጌ በሁሉም አርሶ አደሮች መሀል ምን ልዩነት አለ? ሁሉም ጥያቄያቸው አንድ አይነት ነው፤የድህነታቸው ደረጃም ተመሳሳይ ነው፡፡ ጨቋኝ ብሔር ቢኖር ኖሮ ግን አንዱ ከሌሎች ልቆ ይታይ ነበር፡፡ ሁሉም አርሶ አደር በእግሩ የሚሄድ አሁንም የወንዝ ውሃ የሚጠጣ ነው፤ ልዩነት የላቸውም፤ ግን በህገ መንግስቱ ውስጥ ተቀብሮ የኖረ ፈንጂ ስላለ አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ አድርጎ እንዲከፋፈል አድርጓል፡፡ በእኔ እምነት የሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አንዱ የማይቀር ነገር የህገ መንግስት መሻሻል ጉዳይ ነወ፡፡የህዝብ ድምጽ የሚያገኝ ፖርቲ ሲመጣ ወይም በጥምር ሲመጡ የሚያደርጉት ነገር ይሆናል ብዬ ነው ማስበው፡፡ ብልፅግና ግን ብቻውን ወደ ህገ መንግስት መሻሻል ስራ ውስጥ የመግባት ማንዴት የለውም፤ መቶ ፐርሰንት በአንደ ፖርቲ በተያዘ ፖርላማ ህገመንግስ ይሻሻል ከተባለ የድሮው ነገር ተመልሶ ነው የሚመጣው፡፡

ቁም ነገር፡- ግን ህገ መንግስን ለማሻሻል የዚህ መንግስት ማንዴት ወይም ሀላፊነት አይደለም ከተባለ ምርጫ ማካሄድስ እንዴት መብቱ ይሆናል?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ምርጫ እኮ የሚያካሂደው መንግስት አይደለም ፤ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡

ቁም ነገር፡-ምርጫ ቦርድ ማን ነው የሰየመው? መንግስት አይደለም?

ዲያቆን ዳንኤል ፡- እሱማ መንግስት ነው፤ አማራጭ የለህማ፤ ከብዙ ሰይጣኖች መሀከል አንዱ የግድ መምረጥ አለብህ፤ አንድ መድሃኒት ስትወስድ እኮ አነስተኛ የጎንዮሽ ጉዳት ያለውን መርጠህ ብትወስድ ነው የመዳን ዕድል የሚኖርህ፤ ስለዚህ መንግስት ወሰደ ብዬ የማስበው ይህኛውን አነስተኛ ጎንዮሽ ጉዳት ያለውን ምርጫን ማድረግ ነው ፤ወደ ህገ መንገስት ማሻሻል ለመሄድም መጀመሪያ ምርጫው መደረግ ስላለበት ይመስለኛል ይህንን የመረጠው፡፡

ቁም ነገር፡-ግን በምርጫውስ ቢሆን መንግስትን ወይም ገዠውን ፖርቲ የሚገዳደር የፖለቲካ ድርጅት አሁን አለ ለማለት ይቻላል? ይገዳደሩታል ተብለው የሚታሰቡት ድርጅቶች በተለያየ ምክንያት ከምርጫው ውድድር እየወጡ ስለሆነ?

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ይህን በተመለከተ በትክክል ለመናገር ግምገማ ካደረጉ ሰዎች መሀል ነኝ ለማለት  አልችልም፤ እኔም እንደማንኛውም ሰው የሚነገረውን እሰማለሁ፤ ግን ደግሞ ብልፅግናን ለመገዳደር እየተዘጋጁ ያሉ ድርጅቶችም እንዳሉ ይታወቃል፤ ብልፅግና የራሱ የሆኑ ጥንካሬዎች አሉት፡፡ መንግስት ሆኖ የኖረ ፖርቲ መሆኑ፤ የኢኮኖሚ አቅሙም ከፍ ያለ መሆኑ፤ በርካታ አባል ያለው መሆኑ ወዘተ ይሄ በታሪክ አጋጣሚ ያገኛቸው መልካም እድሎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ግን ብልፅግና ፖርቲን በሀሳብም በአሰራርም ልንገዳደረው እንችላለን ብለው የመጡ የተመዘገቡ ፖርቲዎች እንዳሉ መዘንጋት አይገባም፡፡

ቁም ነገር፡-እሱማ በኢህአዴግ ምርጫም ወቅት እኮ እንገዳደራለን ብለው የተመዘገቡ ‹ፖርቲዎች› ነበሩ፤

ዲያቆን ዳንኤል ፡-ነበሩ፤ ግን አሁን ልዩነቱ ምንድነው? እምቢ የሚል ምርጫ ቦርድ አለ፡፡በእዛን ወቅት የነበሩት ፖርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ የነበረው ምርጫ ቦርድም  ምን እንደሆነ ይታወቃል፤ በወቅቱ ገዢው ፖርቲ  ሚዲያዎችን ሁሉንም የመቆጣጠር ፍላጎት ነበረው፤ አሁንም መንግስት እንደዚህ አይነት ፍላጎት ስለሌለው ሳይሆን ቢያንስ ይህንን ተፅእኖ አንቀበልም የሚሉ ሚዲያዎች አሉ፡፡አሁን ያለው የዓለም ሁኔታ እንደቀድሞው ሁሉንም ነገር ጨምድዶ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡ የሀሳብ ብዝሃነት የግድ የሆነበት ወቅት ላይ በመሆኑ መንግስት ቢፈልግ እንኳ ብቻውን ሮጦ ብቻውን ማሸነፍ የሚችልበት ዕድል የለም፡፡ ተፎካካሪዎች አሉ ፤ እንፎካከራለን ብለው ወደ ምርጫው የገቡ አሉ፡፡ ውድድሩ ለሁሉም ተከፍቷል፤ መፎካካር የእነርሱ ፋንታ ነው፡፡

ቁም ነገር፡- የመንግስትና የድርጅት ስራ መለያየት እንዳለበት ይታወቃል፤ ከሚዲያ አንፃር ግን ገዢው ፖርቲ አሁንም የመንግስት ሚዲያን ለእራሱ ብቻ አገልጋይ አድርጓል ሚል ቅሬታ ይሰማል፤ ከዚህ አንፃር ምርጫው ፍትሐዊ ይሆናል ለማለት ይቻላል?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እንግዲህ እስከማውቀው ድረስ የፖለቲካ ፖርቲዎች የፈረሙት የስነ ምግባር ደንብ አለ፤ እዛ ላይ በግልፅ የመንግስትና የፖርቲ ሚና መለያየት እንዳለበት በግልጽ ተቀምጧል፤

ቁም ነገር፡-ተግባሩስ?

ዲያቆን ዳንኤል፡-እየተሰራ ያለውም በዚሁ መልኩ ነው ብዬ ነው የማስበው፤ ምርጫ ቦርድ ከደለደለው የአየር ሰኣት ውጭ አድሎ ተደርጎ ከሆነ የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡

<በሀሰተኛ ሰነድ ወደ ኢትዮጵያ የገባ አራት ኮንቴይነር ገጀራ ተያዘ>

ቁም ነገር፡- ከድልድሉስ በፊት ገዢውን ፖርቲ ብቻ የሚያወድሱና የሚያጎሉ ዘገባዎች ይተላለፉ አልነበር?

ዲያቆን ዳንኤል፡-እንግዲህ እዚህ ላይ መረጃ ይዘን ብንነጋገር ጥሩ ነው የሚሆነው፡፡እንደውም ከሚዲዎቹ የሚነገረው ፖርቲዎች ምንም አይነት ዝግጅት ሲያዘጋጁ ለሚዲያዎች አይናገሩም፤ የምርጫ ማኔፌስቷቸውን ሳይቀር ሲያወጡ አይጠሯቸውም፤ ሳይጠሩን እንዴት እንዘግብላቸው ነው የሚሉት፡፡ እያንዳንዱ ሚዲያ ከምርጫ ጋር ተያይዞ የቅሬታ ማቅረቢያ ፎርም ሁሉ  አላቸው፡፡ ጥቆማም መስጪያ ዕድል አላቸው፡፡ግን ብዙዎቹ ያንን አያደርጉም፡፡

ቁም ነገር፡-ባንተ ግምገማ የፖርቲና የመንግስት ስራ የተለያየ ነው ለማለት ይቻላል?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እየተለያየ ነው፤

ቁም ነገር፡-በሁሉም ጉዳዮች?

ዲያቆን ዳንኤል፡-በሁሉም ጉዳዮች ለማለት እኮ ሁሉን ነገር መሬት ወርጄ  ማየት አለብኝ፡፡በዚህ መስሪያ ቤት በዚህ ቦታ ለማለት መረጃ ያስፈልገኛል፡፡

ቁም ነገር፡-አሁን ለምሳሌ አንዳንድ ባለስልጣናት በመንግስት መኪና ሄደው የብልጽግናን ቅስቀሳ አካሂደው የሚመለሱ አሉ፤

ዲያቆን ዳንኤል፡-እሱ ስህተት ነው፤  እንደዚህ አይነት ነገር ትክክል አይደለም፡፡ህጉም እንደዚህ አይነት ነገሮችን ለማረም ክፍት ነው፡፡ ፍፅም ነው የማልልህ ለዚህ ነው፡፡ ስህተቶች ይኖራሉ፤ ያ ደግሞ የሚታረምበት ስርዓት አለ፡፡ይሄ እንዲታረም መስራት ደግሞ የሁላችንም ሀላፊነት ነው፡፡ ሮም እኮ በአንድ ጊዜ አልተገነባችም የሚባል አባባል አለ፡፡

ቁም ነገር፡-የአሁኑ ብልጽግና ከቀድሞው ኢህአዴግ ከአንዳንደንድ ሰዎችና ከስም በቀር ለውጥ የለውም የሚሉ ወገኖች አሉ፤

ዲያቆን ዳንኤል፡-ሊኖሩ ይችላሉ፤ እኔ የፖርቲው አባል ስላልሆንኩ እዚህ ጉዳይ ላይ መናገር አልችልም፤ በማየውና ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን በዚህ አባባል አልስማማም፡፡ብልፅግና በብዙ መልኩ ካለፈው ኢህአዴግ የተለየ ስለመሆኑ ብዙ ምሳሌዎችን በማንሳት መናገር ይቻላል፡፡ይሄንን ግን በደንብ መግልጽ ያለበት ራሱ ብልፅግና ነው፡፡

ቁም ነገር፡- አንተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ነህ፤ የአንድ መሪ ጥንካሬም ሆነ ድክመት ከሚለካባቸው ጉዳዮች መሀከል አንዱ በዙሪያቸው የሚያስቀምጧቸው ሰዎች ማንነት ወሳኝ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበጎ ስራ ክሬዲቱን የሚወስዱ እንዳሉ ሁሉ ለድክመታቸውስ በዙሪያቸው ያላችሁት አማካሪዎች ሀላፊነት የለባችሁም?

ዲያቆን ዳንኤል፡-እሱ የሁሉም ነገር ድምር ውጤት ነው፡፡ግን ድክመቱ ከክፋት ወይም ካለመፈለግ የመጣ አይመስለኝም፡፡አቅሙ ሙሉ ለሙሉ እንዳይጠቀም ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡

ቁም ነገር፡- መንግስት አቅም አንሶት ማለት ነው?

ዲያቆን ዳንኤል፡-አዎ፤ መንግስት እንደምናስበው ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል አካል አድርገን  መውሰድ የለብንም፡፡መንግስት አቅሙን እንዳይጠቀም ብዙ እጁን የሚይዙት ነገሮች አሉ፡፡ እሱን መንግስት ስትሆን ነው የምታውቀው፡፡ ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር ነው፡፡ እኔም ብዙ ነገሮችን ስለመንግስት የተረዳሁት መንግስት ስራ ውስጥ ገብቼ ከተመለከትኩ በኋላ ነው፡፡ መንግስት ስትሆን ብዙ ማድረግ የምትፈልጋቸውን ነገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ላታደርግ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ የመንግስት ያለመፈልግ ነው ብዬ አላስብም፤ አብሬያቸው ስለምሰራ፤ 24 ሰዓት ሲደክሙ ስለምመለከት፡፡ዋናው ነገር የዚህ ሀገር መንግስት ስልጣን ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ያጣነው በጎ ህሊና አሁን አላቸው፤ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ የተሻለ ነገር ለመስራት ይደክማሉ፤

ቁም ነገር፡-በጎ ህሊና ግን መገለጫው ምንድነው ? ከሚታየው አንፃር?

ዲያቆን ዳንኤል፡- ብዙ ነገሮች አሉ፤ እየተገለጠ እኮ ነው በስራ፤ ብዙ የሚጨበጡ ነገሮች እየታዩ ነው፤ በሚፈለገው ደረጃ አይደለም ከሆነ አዎ፤ የረሃባችንን ያህል አልጠገብንም፤ለምሳሌ አንድ ሰው ተርቦ መሶብ ውስጥ ያለው ግማሽ እንጀራ ከሆነና ያንን ከሰጡት ሙሉውን ሰጥተውታል ማለት ነው፡፡ ግን ያንን ሙሉ እንጀራ በልቶም አልጠገበ ይሆናል፡፡በበላው እንጀራና በሰውየው ረሃብ መሀከል ክፍተት አለ፤ አልጠገበም፤ ላይጠግብ ይችላል ፤ መሶብ ውስጥ ያለውን እንጀራ በሙሉ ግን ተሰጥቶታትል፡፡

ቁም ነገር፡-ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዙሪያቸው ያሉት ተሻሚዎች በሙሉ ቀና ናቸው ለማለት ይቻላል?

ዲያቆን ዳንኤል፡- ታሜ ነገሩን አትቀላቅልብኝ፤  በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ማለትና የሾሟቸው ሰዎች ማለት የተለያየ ነው፡፡ በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች ቀናዎች እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡ እኔም ስላለሁበት ቀና መሆናቸውን መናገር እችላለሁ፡፡ ስለሾሟቸው ሰዎች ግን ብዙም የማውቀው ነገር የለም፡፡ የፓርቲም አባልም ስላልሆንኩ ያንን ጠለቅ ብዬ አላውቀውም፤ ሹመቱ የፓረቲ ስራ ነው፡፡

ቁም ነገር፡-በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፖርላማው በሰጡት ማብራሪያ ላይ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ መግባታውን አምነዋል፤ አንተ ደግሞ ቀደም ሲል በሰጠኸው ቃለ መጠይቅ ላይ ‹የኤርትራ ወታደሮች አልገቡም› የሚል ይዘት ያው መግለጫ ሰጥተሃል፤ ማነው የተሳሳተው?

<በጅማ እና በአማሮ የታጠቁ ሀይሎች በከፈቱት ተኩስ ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን ኢሰመኮ…>

ዲያቆን ዳንኤል፡-ማንም አልተሳሳተም፤ በትክክል አድምጠኸው ከሆነ በሁለታችን ንግግር መሀል የሚጋጭ ነገር የለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ‹ኤርትራ ድንበር ላይ የነበሩ የኤርትራ ወታደሮች ሮኬት ሲተኮስባቸው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተዋል› ነው ያሉት፡፡ እኔ የተናገርኩትን በደንብ ሰምተኸው ከሆነ ደግሞ  ‹ኢትዮጵያ ወታደር አንሷት ወይም  አቅም አንሷት የኤርትራን ወታደሮች ድጋፍ አልጠየቀችም› ነው ያልኩት፤ በመሆኑም የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጰያ ወታደሮች ጎን ቆመው አልተዋጉም፤ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በደቡብ ሱዳንና በሌሎች ሀገሮች ላይ ሰላም ለማስከበር የሄዱ በቂ ወታደሮች አሏት፤ የወታደር እጥረት ቢያጋጥም እንኳ ከዛ እናመጣለን እንጂ የኤርትራ ወታደሮችን ድጋፍ ጠይቀን አለብረን ልንዋጋ አንችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያሉት ይሄንን ነው፤ ኢትዮጵያ የሀይል እጥረት አጋጥሟት የኤርትራ ወታደሮችን ድጋፍ አልጠየቀችም፤ ከኢትዮጵያ ወታደር ጋር ተሰልፎ የተዋጋ የኤርትራ ወታደርም የለም ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ በይዘት ደረጃ ልዩነት ያለው ንግግር አይደለም፡፡

ቁም ነገር፡-የቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሲሾሙ አድንቀህ ተናግረህ ነበር፤ አሁን ላይ ያንን ንግግርህን ስታስበው ቅሬታ ይሰማሃል?

ዲያቆን ዳንኤል፡- ምንም ነገር መታየት ያለበት ወይም መመዘን ያለበት በተነገረበት ወቅት አንፃር  መሆን ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ፤ ያንን ንግግር ስናገር ከወቅቱ አንጻር በነበረኝ እውቀትና እምነት ላይ ሆኜ ነው፤ በመሆኑም ከወቅቱ አንፃር ትክክል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ያለው እውነታ ከዚያ የተለየ ሊሆን ይችላል፤

ቁም ነገር፡-አሁን ካለው እውነታ አንጻርስ?

ዲያቆን ዳንኤል፡-በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ባልሰጥ እመርጣለሁ፡፡

ቁም ነገር፡-የምርጫ ምልክትህ ሐ ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ግልጽ አይደለም ይላሉ?

ዲያቆን ዳንኤል፡- እንዴት ነው ግልጽ ያልሆነው? እንደውም እንደ እኔ የምርጫ ምልክት ለህብረተሰቡ ቅርብ የሆነ ምልክት ያለ አይለመስለኝም፤ ሐ መንሽ ነው፤ ገበሬው እህሉን ሲወቃ የሚያዘራበት ነው፤ መንሽን የሚያውቅ ኢትዮጵያዊ የለም እያልከኝ ነው? አይመስለኝም፤

ቁም ነገር፡- አመሰግናለሁ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe