የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮን ላለፉት ስድስት ወራት ሲመሩ የቆዩት ብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጋቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
”ሰኞ ዕለት የተላከልኝ ደብዳቤ ከሥራ እንደተሰናበትኩ ይገልጻል” ሲሉ ብ/ጄኔራል ከማል ይናገራሉ። ከሥራ የተሰናበቱበትን ምክንያት እንደማያውቁ ብ/ጄኔራል ከማል ጨምረው ተናግረዋል።
የሥራ ስንብት ደብዳቤው ከመድረሱ በፊት ውይይቶች እና ግምገማዎች እንደነበሩ የሚያስታውሱት ብ/ጄኔራል ከማል – በስንብት ደብዳቤው ላይ የክልሉ ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ፊርማ እንዳረፈበት ያስረዳሉ።
ብርጋዴር ጄኔራል ከማል የክልሉ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ሊደርስ እንደሚችል ቀድመው ይገምቱ እንደነበር ተናግረዋል።
ለዚህ ግምታቸውም ሁለት ምክንያቶች እንዳሏቸው የሚገልጹት ብ/ጀ ከማል “በአስተዳደሩ ውስጥ የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራ የሚሰሩበት መንገድ በእኔ ፓርቲም ሆነ በግል እምነቴ ተቀባይነት የለውም። በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ላይ ፓርቲ ጣልቃ መግባት አለበት ብለን አናምንም” ሲሉ አንደኛውን ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።
አክለውም ሁለተኛውን ምክንያት ሲጠቅሱ ” መለስ ብዬ ሳስበው የፖለቲካ ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል እኔ ወደ ስልጣን እንድመጣ የተደረገው ውሳኔ አመራሩን ጥያቄ ውስጥ የጣለው ይመስለኛል” ሲሉ ይናገራሉ።
ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ ከ13 ዓመታት በኋላ የጠቅላይ ሚንስትሩን የሰላም ጥሪ ተከትለው ከኤርትራ ባለፈው ዓመት ወደ ሃገር መግባታቸው ይታወሳል። ከዚያም ጥቅምት ወር ላይ ነበር የክልሉ የአስተዳደርና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት።
ብ/ጄኔራሉ ክልሉን ያሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዲሞክራቲ ፓርቲ (ኦዲፓ) አባል አለመሆናቸው እና እራሳቸው የሚመሩት ፓርቲ መኖሩ ሹመታቸው በርካቶችን አስገርሞ ነበር።
ብ/ጄኔራሉ በሥራ ቆይታቸው በቢሮው የሰው ኃይል ስምሪት እና ቁጥጥር ላይ ገዢው የኦሮሞ ዲሞክራቲ ፓርቲ (ኦዲፓ) የበላይነት አለ ሲሉም ይወቅሳሉ።
በጉዳዩ ላይ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ኦዲፓ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመሩት የኦሮሚያ አንድነት እና ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ዲሞክራቲ ፓርቲ (ኦዲፓ) ‘እስከ ሽግግሩ ድረስ’ አብሮ ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
ስለሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት ሲናገሩ ”በሃሳብ ደረጃ ተስማማን እንጂ በጽሑፍ የተቀመጠ ነገር የለም” ሲሉ ብ/ጄኔራል ይናገራሉ። የብ/ጄኔራሉ ፓርቲ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ከተሸጋገር በኋላ ስያሜውን ወደ የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ ቀይሯል።