የከተማው መናኝ -ኤልያስ መልካ

ኤልያስ የኩላሊት ዕጥበቱን ካቆመ ስምንተኛ ቀኑ ላይ ይገኛል፡፡ ከአልጋው መነሳት እንኳን ቀላል አልሆነለትም ፡፡ የቤት ሰራተኛው ጀማነሽ ወርቁ እየደከመው መሄዱን ብትረዳም ጉልበቱ እስኪያብጥ ድረስ ተንበርክኮ መጸለይ መቻሉ ግን ግራ አጋብቷታል ፡፡
“ግራ ሲገባኝ ኤልያስ ግን የማይወዱህ ሰዎች እንዳትኖር ምን አድረገውብህ ይሆን ?አልኩት ፡፡ ሁሌም እንደሚለኝ ድሮ የሰራሁት ኀጢአት ነው ብሎ መለሰልኝ ፡፡ እሺ ሕክምና ለምንድነው የማትሔደው አልኩት? ላብራቶሪ የሰጠሁት ውጤት አለ እሱን እኮ እየጠበኩ ነው አለኝ ፡፡”ጀማነሽ ከክፍሉ ከወጣች በኋላ እምባዋን ተው ልትለው አልቻለችም ፡፡ ጓዳ ገብታ ማልቀስ ጀመረች ፡፡
ቅርርባቸው እንደ ታናሽ እህቱ እንጂ እንደ ቤት ሰራተኛው አልነበረም ፡፡ አንድ ዓመት ከሰራች በኋላ ሳትጠይቀው ደሞዟን እጥፍ አደረገላት ፡፡ የወር ደሞዝሽ መነካት የለበትም እያለ ቤተሰብ ጥየቃ ስትሄድ ወጭዋን የሚሸፍንላት እሱ ነበር ፡፡ ሁሉንም ሰው እኩል ማየቱ ይደንቀኛል ትለለች ፡፡
ጀማነሽ በደጉ ዘመን አብራው አሳልፋ በፈተናው ስዓት ጥላው የምትሄድ ሰው አልነበረችም ፡፡ በሕመሙ ወቅት አብራ ደክማለች ፡፡ ስቃዩ በበረታበት ስዓት ቀድማ አልቅሳለች ፡፡ ዛሬም የሆነው እሱ ነው ፡፡ የወንድም ያህል ለሚያቀርባት ኤልያስ መልካ ጓዳ ገብታ አለቀሰች ፡፡
ዕለቱ አርብ ነው ፡፡ ኤልያስ መልካ የኩላሊት ዕጥበት ሕክምናውን ካቆመ አስረኛ ቀኑ ላይ ይገኛል ፡፡ ጀማነሽ በጠዋት ወደ ክፍሉ ሔዳ እንደተለመደው ቁርስ ምን ልሥራልህ አለችው ፡፡“ቆንጆ የዶሮ ሾርባ አዘጋጅልኝ ”ብሎ መለሰላት ፡፡ ሰርታ ወሰደችለት ፡፡ እንደተኛ ነው ፡፡ “ደርሷል ተነስ” አለችው ፡፡ እሺ እበላለሁ አላት ፡፡
ከ30 ደቂቃ በኋላ ሳህኑን ለመውሰድ ስትመለስም ከአልጋው አልወረደም ፡፡ “ለምን አትነሳም?”አለችው ፡፡ በድካም ስሜት ውስጥ ሆኖ በቃ አሁን ልነሳ ነው ሲላት ሾርባውን ለማሞቅ ከክፍሉ ወጣች ፡፡ “ከአፍታ በኋላ ስመለስ ተንበርክኮ እየጸለየ ነበር ፡፡ አስቀመጥኩለት፡፡ መታመሙን ስላየሁ ልቤ ሊረጋጋ አልቻለም ፡፡
ትንሽ ቆይቼ እንደገና ሄድኩ ፡፡ ተንበርክኮ መጸለይ አላቆመም፡፡ላለመረበሽ ከበር ተመለስኩ፡፡
ከ30 ደቂቃ በኋላ ይጨርሳል ብዬ ሔጄ አየሁት አሁንም እየጸለየ ነው ፡፡ዛሬ ደግሞ በጣም አረዘመው እያልኩ ሳሎን ላሉት ቁርስ ላቀርብ ስል ከኤልያስ ክፍል የሚወድቅ ነገር ድምጽ ስማሁ ፡፡
የወንድሙን ልጅ ትንቢት ቀድሞኝ እየሮጠ ወጣ ፡፡ እኔም ተከትዬው ደረስኩ ፡፡ ኤልያስ በተንበረከከበት ሥፋራ ላይ ወደ አንድ አቅጣጫ ወድቋል፡፡ለሁለት አንስተን አልጋው ላይ አስተኛነው ፡፡በዛ ሁኔታ ምግብ ብላ ማለት ስላልቻልን ትንሽ ዕረፍት ያድርግ ብለን ከክፍሉ ወጣን ፡፡እኔ ግን ልቤ ሊያርፍልኝ አልቻለም ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ተመልሼ ሄድኩ ፡፡
ኤልያስ እንቅልፍ ወስዶታል፡፡ፊቱም ሙሉ በሙሉ ተቀያይሯል ፡፡ በጤንነቱ ጊዜ የነበረው መልኩ ተመልሶል ፡፡ ቀይ ሆኖ ታየኝ ፡፡ ደነገጥኩ ፡፡ በስመ አብ ወወልድ ብየ አማተብኩ ፡፡ “ኤልያስ !ኤልያስ!” እያልኩ ተጣራሁ ፡፡ ብንን ብሎ ፊቱን እየጠራረገ ቆንጆ ሕልም እያየሁ ነበር አቋረጥሽን አለኝ ፡፡ ምን? አየህ ብየ ጠየኩት ፡፡
በአረንጓዴ ሜዳ ላይ አንዲት ቀጭን መንገድ አገኘሁ በእሷ የሆነ በጣም የሚያምር ቦታ ደርሼ መጣሁ ሲል መለሰልኝ ፡፡
#ይነገር ጌታቸው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe