የከተማ እና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ለፖርላማው  አልታዘዝም ማለቱ ተሰማ

በአዲስ አበባ   በስራ እድል ፈጠራ ሰበብ መሬት ሲሸነሸን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ዝምታን መርጧል ተብሏል፤ዝርዝር አለን፤

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማ እና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር የታየበትን የኦዲት ግኝት ትኩረት ሰጥቶ መፍታት እንዳልቻለ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህን ያለው የከተሞች ፕላን አተገባበርና ትስስር፣ የመረጃ አያያዝና የህብረተሰብ ተሳትፎን አስመልክቶ የፌደራል ዋና ኦዲተር ባቀረበው የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ ከተቋሙ የስራ ኃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ እንዳሉት የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ከ2012-2013 ዓ.ም በታየበት በኦዲት ግኝት መሰረት የተሰሩና ያልተሰሩ ስራዎችን ለይቶ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያደርግ በደብዳቤ ተጠይቆ ምላሽ አለመስጠቱ  ለኦዲት ግኝቱ ትኩረት ያለመስጠቱን ያመላክታል ብለዋል፡፡

የከተሞች ፕላን አተገባበር ትኩረት ሊሰጠውና ከክልሎችም ጋር ያለው ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ያስታወሱት ሰብሳቢው ከተሞች የነዋሪዎቻቸው ሃብት በመሆናቸው ህዝቡ በፕላን ዝግጅትና አተገባበሩ ዙሪያ እንዲሳተፍ ማድረግ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል አይነተኛ መሳሪያ መሆኑን መረዳት ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የከተሞች መሬት መረጃ አያያዝን ማዘመን እና ፕላኑን ከግለሰቦች ኪስ ማውጣት እንዳለበት አሳስበው በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ በስራ እድል ፈጠራ ሰበብ ለሌላ ተግባር የተቀመጠን መሬት መሸንሸን ህገ-ወጥነትን ማበረታታት በመሆኑ  ሚኒስቴሩ ትኩረት ሰጥቶ መከታተልና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኦዲት ግኝቱን አስመልክቶ ያዘጋጀውን የድርጊት መርሃ-ግብር እስከ ጥር 26/2014 ዓ.ም ድረስ ለቋሚ ኮሚቴውና ለፌደራል ዋና ኦዲተር መላክ እንዳለበት አቅጣጫ የሰጡት አቶ ክርስቲያን ፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ዋና ኦዲተር እና የፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አፈጻጸሙን እንዲከታተሉና በተለይ የሚዲያ ተቋት ይህ ዘርፍ ከፍተኛ የህዝብ ሃብት የሚባክንበት መሆኑን በመገንዘብ ከዜና ሽፋን ባሻገር የምርመራ ዘገባ እየሰራችሁ የህዝቡን መረጃ የማግኘት መብት ልታረጋግጡ ይገባል ሲሉ አደራ ሰጥተዋል፡፡

የፌደራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የሁሉም ክልል ከተሞች ፕላን ተግባራዊ አለመደረጉን አንስተው የከተማ ልማት ትግበራ ዝግጅትም 30 በመቶ ለህዝብ መገልገያ 40 በመቶ ለግንባታ የሚለው ፕላን ተግባራዊ አለመደረጉንና ይህም የአቅም ችግር ሳይሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መስራት የሚገባውን ባለመስራቱ እንደሆነ በኦዲት ግኝቱ አረጋግጠናል ማለታቸውን ዜና ፖርላማ ዘግቧል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe