የወታደሮችን ልብስ ከማጥበብ እስከ ቢሊየነርነት የደረሱት – አቶ ሰዒድ መሐመድብርሀን

ከፊታቸው ፈገግታ የማይጠፋው ባለሀብቱ አቶ ሰዒድ፣ እንዲሁ ሲታዩ በ40ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሚገኝ ጎረምሳ እንጂ የ63 ዓመት ጎልማሳ አይመስሉም።

“በጠዋቱ ተነስቼ ፑሽ አፕ እሠራለሁኝ፤ ወክ አደርጋለሁኝ፤ ዋናተኛም ነኝ፤ ትላልቅ ባይሆንም ትናንሽ ብረትም ስለማነሳ የ63 ዕድሜ ባለፀጋ ሽማግሌ አልመስልም” ይላሉ አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሀን።

የሥራ ሕይወታቸውን የጀመሩት የወታደር ልብስ አጥብቦ ከመስፋት ነው።

አሁን ሀብታቸው በቢሊዮኖች ይቆጠራል።

አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሃን በ1953 ዓ.ም. በትግራይ ከሽረ እንዳ ሥላሴ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ትንሽ የገጠር መንደር ነው የተወለዱት።

በልጅነታቸው እንደ ማንኛውም በግብርና ሥራ ከሚተዳደሩ ቤተሰቦች እንደተወለደ ልጅ፣ ከብቶች ጠብቀው እንዳደጉ የሚያስታውሱት አቶ ሰዒድ፣ ወላጅ አባታቸው “ልጆቼ እናንተ እንደ እኔ ገበሬ መሆን የለባችሁም” ብለው ዓዲ ዳዕሮ ወደ ሚገኘው ትምህርት ቤት እንደላኳቸው ያስታውሳሉ።የአባታቸው ፍላጎት ግን ልጆቻቸው ተምረው እንዲመረቁ ሳይሆን ማንበብ እና መጻፍ እንዲችሉ ብቻ ነበር።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያታቸው በትምህርት ዓለም ከሚገኝ ስኬት ይልቅ ልጆቻቸው ነጋዴ እንዲሆኑ አጥብቀው መሻታቸው ነበር።

“[አባቴ] አንድ ክረምት ባድመ አካባቢ ወደሚገኝ በረሀ ሄዶ፣ ሰሊጥ ዘርቶ ያገኛትን 600 ብር አስይዞ ከታላቅ ወንድሜ ጋር ልብስ ስፌት እንድንሠራ እዚያው ዓዲ ዳዕሮ ከተማ አስገባን” ይላሉ።

በ1966 ዓ.ም. የ13 ዓመት ጎረምሳ የነበሩት አቶ ሰዒድ፣ የትውልድ ቀያቸውን በወቅቱ አማጺያን ለትጥቅ ትግል ራሳቸውን የሚፈትሹበት እንደነበር ያስታውሳሉ።

“ከትውልድ ቀያችን የጥይት ድምጽ የማይጠፋበት ጊዜ ስለነበረ ለአቅመ አዳም የደረሰ ሁሉ እዚያው አካባቢ ወደሚንቀሳቀሱት ኃይሎች ይቀላቀል ነበር።”

ወላጅ አባታቸው ግን ልጆቻቸው በሕይወት ቆይተው፣ ሀብት እንዲያፈሩ ይፈልጉ ስለነበር ጦርነት ከሚበዛበት አድያቦ አውጥተው መቀለ ከተማ ላክዋቸው።

አቶ ሰዒድ መቀለ ግን እንደ ጠበቁዋት ሆና አልጠበቀቻቸውም።

“በስንት መከራ መቀለ ከገባን በኋላ አንድ የተዋወኳቸው አባት ‘እዚሁ መቀለም ሥራ ቀዝቀዝ ያለ ነው’ ስላሉን ጊዜ ሳላጠፋ ከመቀለ አቅራቢያ ወደ ምትገኝ ኩሃ ከተማ ሄድኩኝ” ይላሉ።

በወቅቱ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ የነበረባት ኩሃ ፈገግ ብላ የተቀበለቻቸው አቶ ሰዒድ፣ ወታደሮቹ የተሰጣቸው መለዮ ስለሚሰፋቸው፣ 24 ሰዓት የደንብ ልብሶቻቸውን በማጥበብ ሥራ ተጠመዱ።

“ሳምንት ሙሉ ባለማቋረጥ የወታደሮቹን ልብስ ነው የምስፋው። እሁድ 10 ሰዓት ገደማ ሲሆን ልብሶቼን ለማጠብ ብቻ እረፍት እወስዳለሁ። ለ11 ወራት እንደ ልቤ ሠርቼ ያጠራቀምኩትን 3 ሺህ ብር ይዤ ተመልሼ ወደ መቀለ ገባሁኝ” ይላሉ።

አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሀን ሥራቸውን ከጀመሩባት የስፌት መኪና ጋር

የፎቶው ባለመብት,SAID

የምስሉ መግለጫ,አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሀን ሥራቸውን ከጀመሩባት የስፌት መኪና ጋር

በአንድ ሺህ ብር የራሳቸው የልብስ ስፌት ማሽን፣ በቀሪው ሁለት ሺህ ደግሞ ሱቅ ተከራዩ።

በዚያች ሱቅ ጠንክረው ሠርተው ሁለት መኪና ከነተሳቢያቸው መግዛት ቻሉ።

አቶ ሰዒድ በዚህች ሱቅ እየሠሩ ሀብት ቢያፈሩም በ1980ዎቹ መጨረሻ ኪሳራ ስለገጠማቸው ወደ ልብስ ሰፊነት ተመልሰው ገቡ።

በተለይም መቀለ በ1981 ዓ.ም. አጋማሽ አካባቢ በህወሓት ቁጥጥር ስር ስለወደቀች፣ ልብስ የሚያሰፋ ወታደር በመጥፋቱ አቶ ሰዒድ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ወሰኑ።

በወቅቱ ከመቀለ አዲስ አበባ ለመግባት፣ እንደ አሁኑ ከአሉላ አባነጋ አየር ማረፍያ ተነስቶ በ45 ደቂቃ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፍያ መድረስ አይታሰብም ነበር።

ከዚያ ይልቅ ከመቀለ አሥመራ፣ ከዚያ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ነበር የሚኬደው።

አቶ ሰዒድም ከኪሳራ የተረፉት የልብስ ስፌት መሳርያዎቻቸውን፣ ያልተሰፉ ጨርቆችን ጠቅልለው ወደ አሥመራ ሲጓዙ ያልጠበቁት ክስተት እንደገጠማቸው ያስታውሳሉ።

“በወቅቱ በዛላምበሳ እና ሰነዓፈ መካከል በምትገኝ የገጠር መንደር የሚገኝ የወታደሮች ኬላ ማለፍ ግዴታ ነበር። እኔም ከመቀለ እንደመጣሁ ስነግራቸው ‘እንዴት ማለፍ ቻልክ?’ ብለው ከተሳፈርኩባት መኪና አውርደው ለተጨማሪ ምርመራ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ። በዚህ መካከል ከኪሳራ የተረፉት የልብስ ስፌት መሳርያዎቼን ከወረሱኝ ምን ይቀረኛል ብዬ ወደ ህወሓት ለመቀላቀል እያስበኩኝ ሳለ ወታደሮቹ መጥተው ‘ንብረትህን ሸክፈህ ውጣ’ ሲሉኝ አሥመራ ሄጄ በአውሮፕላን አዲስ አበባ ገባሁ።”

አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሃን አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ በአገሪቷ ዋነኛው የንግድ መኛኽሪያ ወደ ሆነው መርካቶ ከተሙ።

እዚያው መርካቶ “አምባሳደር ልብስ ስፌት” የሚል ታፔላ ለጥፈው የሚሰሩ አቶ ታዬ ተስፋዬ የተባሉ ነጋዴን ተዋወቁ።

ትውውቃቸውም ከሰላምታ አልፎ አብረው እስከ መሥራት አደጎ የአሁኑ ግዙፍ አምባሳደር ኩባንያዎች ተወለደ።

አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሀን

የፎቶው ባለመብት,SAID

የምስሉ መግለጫ,አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሀን

አቶ ሰዒድ በሕይወታቸው ለሁለተኛ ጊዜ ተስፋ የቆረጡት በ1981 ዓ.ም. በቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በተደረገበት ወቅት እንደነበር አይዘነጉም።

“በ1981 በፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ላይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ ሰፈራችን በኃይለኛ ተኩስ ተናጠ። እኔም ውጊያ ካለበት አካባቢ ለቅቄ ወደ ተሻለ አገር መጣሁኝ ብዬ ፈጣሪን አመስግኜ ሳልጨርስ እንዲሁ በመፈጠሩ ‘አላህ ምን በድዬህ ነው’ ብዬ በሕይወቴ ለሁለተኛ ተስፋ የቆረጥኩበት አጋጣሚ ነበር።”

አቶ ሰዒድ ከግለሰብ የገዙዋትን አምባሳደር ልብስ ስፌት ወደ ፋብሪካ አሳድገው፤ በገርጂ ትልቅ የጋርመንት ፋብሪካ ከፈቱ።

በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ታዋቂ የሆነውን አምባሳደር ሱፍ ማምረት ጀምረው፣ አምባሳደር ሱፍ በተለይም በቴሌቪዥን በብዛት ይተዋወቅ ነበር።

ምርትን ማስተዋወቅ ለሥራቸው ስኬትን እንደሚያመጣ ቀድመው የተረዱት አቶ ሰዒድ፣ “በዚያን ወቅት የማርኬቲንግ ትምህርቱ ባይኖረኝም ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ መርካቶ የከፈትኩዋትን ትንሽዋን የአምባሳደር ልብስ ስፌት ሱቄን እንዲያስተዋውቅልኝ አደርግ ነበር” ሲሉም ያስታውሳሉ።

በአንዲት የልብስ ስፌት መኪና የተጀመረው የንግድ ጉዞ፣ በአሁኑ ሰዓት ገርጂ የሚገኘው የአምባሳደር ልብስ ስፌት ፋብሪካ፣ ቦሌ ሚሌኒየም አዳራሽ አጠገብ የሚገኘው አምባሳደር ሆቴል እና 4 ኪሎ የሚገኘው ግዙፍ አምባሳደር ሞል ባለቤት አድርጓቸዋል።

ቢቢሲ- አቶ ሰዒድ አሁን ቢልየነር ነዎት?

አቶ ሰዒድ- “በብር ቢልየነር ከሆነማ ቆይተናል፤ በዶላር እንዳታደርገው እንጂ” (ሳቅ)

አቶ ሰዒድ ተወልደው ያደጉባት ዓዲ ዳዕሮ ከጥቂት ዓመታት በፊት በትግራይ ተጀምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት ምክንያት እጅግ ከተጎዱት የትግራይ አከባቢዎች አንዷ ናት።

በልጅነት ዕድሜያቸው በአቅራቢያቸው ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ሲከነክናቸው የነበሩት አቶ ሰዒድ፣ ሀብት ካፈሩ በኋላ በዚያች የገጠር መንደር በወላጅ አባታቸው ስም ‘መሐመድ ብርሀን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት’ አስገንብተው ለመንግሥት አስረክበዋል።

በወላጅ እናታቸው ስም ደግሞ ትልቅ ቤተ መፅሐፍት እና የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ቢያሠሩም በጦርነቱ ምክንያት ወድሞ ማየታቸው እንዳሳዘናቸው ይናገራሉ።

በአምባሳደር ኩባንያዎች በጠቅላላ እስከ 700 ሠራተኞች እንዳለው የሚናገሩት አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሃን፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከፍተኛ የሰው እና የንብረት ኪሳራ የደረሳቸው ጀርመን እና ጃፓን ከጦርነቱ ማግስት “በቃን እንዳይደገም” ብለው በመነሳት በዓለም ደረጃ ትልቅ ኢኮኖሚ እንደገነቡ ሁሉ እኛም ከእነሱ ትምህርት መውሰድ ይኖርብናል ይላሉ።

“ልጆቼ ባለሀብት እንጂ ገበሬዎች አይሆኑም” በማለት ለፍተው ያገኝዋትን 600 ብር የሰሊጥ ሽያጭ አስይዘው ወደ ከተማ እንዲገቡ ያደረጓቸው ወላጅ አባታቸው የልጃቸውን ስኬት አይተው እንደሆኑ አቶ ሰዒድን ጠይቀናቸው ነበር።

“አባቴም እናቴም በ90ቹ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት። ገርጂ ያስገነባሁት ትልቁ የልብስ ስፌት ፋብሪካ ሥራ ጀምሮ ስለነበር አዲስ አበባ አምጥቼ የአምባሳደር የልብስ ስፌት ውጤት በሆነው አምባሳደር ሱፍ ዝንጥ ብለው ጋዜጣ ለማንበብ በቅተው ነው ያለፉት። ስለዚህ የልጃቸው የስኬት ጉዞ አይተው እና አጣጥመው ስላረፉ በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላሉ።

አቶ ሰዒድ መሐመድ ብርሃን የሰባት ልጆች አባት እና የ14 የልጅ ልጆች አያት ለመሆን በቅተዋል።

Sourceቢቢሲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe