የውጭ ባንኮች እና የኢትዮጵያን ገበያ

የውጭ ባንኮች የኢትዮጵያን ገበያ መቀላቀላቸውን አስመልክቶ የተለያዩ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሐሳቦች እየተንጸባረቁ ነው። በዝርዝር ለመተቸትም ሆነ ለመደገፍ ፖሊሲዎች የኘፈጻጸም መመሪያዎች እስኪወጡ መጠበቅ ተገቢ ስለሆነ፣ ለዛሬው ጥቅል ሐሳቦችንና ትኩረት የሚሹ ነጥቦች ብቻ በጨረፍታ አቀርባለሁ።

የዓለም አቀፍ ገበያ ድርጅትን (WTO) ለመቀላቀል አንዱ መስፈርት የሆነው ባንክና ቴሌን የመሳሰሉ ተቋማትን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ ነው። በዚህ ምክንያትም የውጭ ሀገር ባንኮች የሀገራችንን የባንኪንግ ኢንደስትሪ የመቀላቀላቸው ጉዳይ የጊዜ ጉዳይ እንጂ አይቀሬ እንደነበር የሚታወቅ ነው።

አሁን ሊያወያየን የሚችለው ጉዳይ ባንኮቹ ገበያውን እንዲቀላቀሉ የተፈቀደበት ወቅት ተገቢ ነበር ወይ? የመንግስት፣ የብሔራዊ ባንክና ሀገር በቀል ባንኮች አቅምና ቅደም ዝግጅታቸውስ ምን ይመስላል? የገበያችንን ስርዓት ( Market Structure) ምን ያህል ሕጋዊነትን የተከተለና ለወንጀልና ወንጀለኞች ያልተጋለጠ ነው።

የግብር አከፋፈል፣ የመረጃ አሰባሰብና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂያችን ምን ያህል ጥብቅና ለውንብድናና ለጠለፋ ( Hacking ) ያልተጋለጡ ናቸው የሚሉትና መሰል ጉዳዮች ይሆናሉ

የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ሀገራችን የሚመጡት ገበያ፣ ነባርና አዲስ ደንበኛና ትርፍ ፍለጋ ስለሆነ ስለ ሀገር እድገት በተለይ የሚጨነቁና የማይጠበቡ ልማታዊ እሳቤም የሌላቸው እንደሆነ የሚታወቅ ነው።

የሚቀላቀሉት ገበያ ያለበት ሀገርም ሀገራቸው ስላልሆነ ትርፍ እስካገኙ ድረስ በማንኛውም መንገድ ከማትረፍ ወደኃላ የማይሉና የሕግ አስገዳጅነት እንጂ የሞራል ጥያቄ እምብዛም የማይገዳቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ታሳቢ መሆን አለበት።

በተቃራኒው ደግሞ ሀገር በቀል ባንኮች ከትርፍ ባሻገር የሀገራቸው፣ የመንግስትና የልማታቸው አጋር ስለሆኑ ከሕግ ባሻገር በርካታ የውዴታ ግዴታና የሞራል ፈተና ስላለባቸው ውድድሩ የተለየ ጫና ሊያሳድርባቸው ይችላል።

የውጭ ሀገር ባንኮች በርካታ የውጭ ምንዛሬ ያመጣሉ የሚለውም እሳቤ የተጋነና በአብዛኛው የተሳሳተ መረጃ ነው። የውጭ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ በገፍ ይዘው መጥተው በብር የመለወጥ ፍላጎት አይኖራቸውም። በአብዛኛውም ያለችውን ገበያና የውጭ ምንዛሪ መቀራመት ላይ እንደማያተኩሩ ይገመታል።

ትርፋቸውንም በውጭ ምንዛሪ ከሀገር የማውጣት እድላቸው ጠባብ ስለሆነና ዋና መስርያ ቤታቸውን እንዲገነቡ ለሚሰበስቡት ብር ተመጣጣኝና ኃላፊነትና ግዴታ (Risk) እንዲወስዱ ካልተገደዱ በስተቀር የባንክ ስራ ቅርንጫፍ ተከራይቶ ቁሳቁስ በማሟላትና ገንዘብ በመሰብሰብ በትንሽ ኢንቨስትመንት የሚሰራ ዘርፍ ስለሆነ ኢንቨስትመንታቸውም ውስን በማድረግ ያለ በቂ ኃላፊነት፣ ስጋትና መተማመኛ ሊነግዱ ይችላሉ።

ሌላው ሀገር በቀል ባንኮች ከተደራሽነትና ሕዝብን ከማገልገል አኳያ ትርፍ ኖረም አልኖረ እንደ አቅማቸው ሁሉም ቦታ ቅርንጫፍ ይከፍታሉ።

የውጭ ባንኮች ግን ሀብትና ኢኮኖሚያዊ አቅም በስፋት የሚታይባቸው አካባቢዎች ላይ ብቻ አትኩረው ሊሰሩ ስለሚችሉ አቅም ባለበት ቦታ ላይ ብቻ የሚኖረው ውድድሩ በሚፈጥረው ሽሚያ በሚፈጠረው አቅም መዳከም ምክንያት ቀሪው አካባቢና ማህበረሰብ የባንክ አገልግሎት ላያገኝ ይችላል።

ሌላው ሀገራችን ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ አስቀማጭና ተበዳሪዎች በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ሰለሆኑ እነዚህን ደንበኞችና ገበያ (Niche Market) ላይ ብቻ በማተኮር ወይም ከፍተኛ እጥረት ያለበት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በማባበያነት በመጠቀም፣ የኢንዱስትሪውን አቅም ከ70 በመቶ በላይ በቀላሉ ለመቆጣጠር ይችላሉ።

ይህ ደግሞ የተዛባና ወደ አንድ ጎን ያጋደለ (Economic imbalance) ፣ ኢ-ፍትሐዊ ወይም ሚዛናዊ ያልሆነ ውድድር (Unfair Competition ) ሊፈጥሩ ይችላሉ።

በዚህ መንገድ ከሞላ ጎደል ገበያውን መሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ስለሚችሉም የፈለጉትን የአገልግሎት ዋጋ በመጣል፣ ወለድ በመተማንና ለፈቀዱለትና ለሚመስላቸው ዘርፍ ብቻ በማበደር ኢኮኖሚውን ወደ ፈለጉበት በመጠምዘዝ ልማታዊ እድሎችን እስከማደናቀፍ ሊደርሱ ይችላሉ።

የውጭ ምንዛሪ ሲፈቅዱ የሀገራቸው ምርት ብቻ እንዲገባ በማድረግም ሀገሪቱን የሸቀጥ ማራገፊያ ( Damping ground) ሊያደርገት ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት አካሄዶች በማደግ ላይ ባሉ በርካታ ሀገራት ላይ ያጋጠመ ፈተናና ችግር ነው።

በአንዳድ ሀገራትም አንዴ ባንኮቹ ጡንቻ ካፈረጠሙ በኃላ ለተለያዮ ኃይሎች የፖለቲካ መሳርያ በመሆን የመንግስትን እጅ እስከ መጠምዘዝ የደረሱበት ሁኔታም ታይቷል።

የውጭ ባንኮች ወድ ሀገር ውስጥ መግባታቸው በጠንካራ ጎንነት ሊወሳ የሚችለው የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ዘመናዊ የባንክ ሙያና እውቀት ስርጸት፣ አዳዲስ የማኔጅመንትና የአመራር ጥበብ ሽግግር የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።

ከዚህም በላይ ለነባርና ብቃት ላላቸው የባንክ ሰራተኞችን ጨምሮ ለአዳዲስ ስራተኞችም የስሬ እድል ይፈጥራል።

የውጭ ባንኮቹ ሀገር ውስጥ መኖራቸው በወጭና በገቢ ንግድ ላይ የነበረውን የተንዛዛ አሰራርና ተደራራቢ የክፍያ ስርዓት ሊቀንስ ይችላል።

ኢንደስትሪው በስርዓትና በሕግ ከተመራም የዘመነና ጤናማ ውድድርን ሊያስከትል ይችላል።

በአጠቃላይ ዘመናዊ አሰራር በማስተዋወቅ አዲስ ሃብት በማሸጋገርና በማበልጸግ የተቀማጭም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ይበልጥ እንዲሳለጥና Economics of Scale ከፍ እንዲል ሊያግዝ ይችላል።
ሙሼ ሰሙ እንደፃፉት  ገፅ የተገኘ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe