የዓለማችን ሴት ቢሊየነሮች
የፎርብስ መረጃ እንደሚጠቁመው ዓለማችን ላይ 244 ቢሊየነር ሴቶች እንዳሉ ይገመታል፡፡ ሴቶቹ ሃብቱን የሚያካብትቱ በተለያየ መንገድ ሲሆን አንዳንዶቹ ከባላቸው ጋር ስፋቱ የሚያገኙት ሃብት ብቻውን ቢሊየነር ተብለው እንዲጠሩ ያስችላቸዋል፡፡ በቅርቡ የአማዞን ድረገጽ መስራችና ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ከባለቤቱ ማኬንዚ ጋር ፍቺ ሲፈጽም ሴትዮዋ ከፍተኛ የሆነ ሃብትን ተካፍላለች፡፡ ከአለማችን ሴት ቢሊነሮች ጎራ መሰለፍም ችላለች፡፡
በስምምነታቸው መሰረት ማኬንዚ የአማዞንን 4 በመቶ የሃብት ድርሻ የምትወስድ ሲሆን ድርሻዋ እስከ 35.6 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ዋጋ ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ብቻውን የዓለማችን ሦስተኛዋ ሃብታም ሴት ያደርጋታል። በአጠቃላይ ደግሞ ከዓለማችን 24ኛዋ ሃብታም ሰው መሆን ችላለች።
በዓለማችን ላይ ካሉ ቢሊየነር ሴቶች መካከል አምስቱን በቅደም ተከተል እንመልከት፡፡
1) ፍራንሷዝ ቤተንኩር ሜየርስ
ሴትዮዋ ሀብቱን የወረሰችው ከእናቷ ነው፡፡ ፍራንሷዝ ቤተንኩር ሜየርስ በፈረንጆቹ 2017 የ94 ዓመት እናቷ ሊሊየን ቤተንኩር ህይወቷ ሲያልፍ የኮስሞቲክ ካምፓኒ የሆነውን ሎሪያል የተሰኘውን ድርጅት ከነሙሉ ሃብቱ ወረሰች። የተጣራ ሃብቷ 49.3 ቢሊየን ዶላር ሲሆን እንደ ፎርብስ መጽሄት ከሆነ የዓለማችን 15ኛዋ ሃብታም ነች።
ይህች የ65 ዓመት ፈረንሳያዊት ‘ሎሪያል’ የተባለው የመዋቢያ እቃዎች አምራች ድርጅት ወራሽ ስትሆን የድርጅቱን 33 በመቶ ድርሻ የግሏ ማድረግ ችላለች።
ፍራንሷዝ ቤተንኩር ሜየርስ የታወቀች ምሁር ስትሆን በብዙ ቅጅ የተሸጡ ሁለት መጽሃፎችንም ማሳተም ችላለች።
2) አሊስ ዋልተን
ያላት የተጣራ ሃብት 44.4 ቢሊየን ዶላር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዓለማችን ካሉ ሃብታሞች መካከል በ17ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የ69 ዓመቷ አሜሪካዊት ‘ዋልማርት’ የተባለው ታዋቂ ሱፐርማርኬት መስራች ሳም ዋልተን ልጅ ነች። ነገር ግን ከሁለቱ ወንድሞቿ በተለየ መልኩ የቤተሰቡን የንግድ ሥራ ወደ ጎን በማለት ወደ ጥበብ ሥራዎች ፊቷን አዙራለች። በአሁኑ ሰዓትም ‘ክሪስታል ብሪጅስ ሚዩዚየም ኦፍ አሜሪካን አርትስ’ የተባለ ድርጅት ዋና ኅላፊ ሆናም እየሰራች ነው።
3) ማኬንዚ ቤዞስ
ቢያንስ 35.6 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ሃብት እንዳላት የሚገመት ሲሆን ከባለቤቷ ጋር ፍቺ ስትፈጽም ከአማዞን ድርሻ ያገኘችው ነው።
በ2006 የአሜሪካ ቡክ አዋርድ ተሸላሚ መሆን የቻለችው ማኬንዜ በድርሰት ስራዎቿም ትታወቃለች፡፡ ሁለት ተነባቢ መጽሐፍትን አሳትማለች፡፡ የ48 ዓመቷ ማኬንዚ ከአማዞን መስራች ባለቤቷ ጄፍ ቤዞስ ጋር በፈረንጆቹ ከ1993 ጀምሮ በትዳር የቆየች ሲሆን አራት ልጆችንም ወልዳለች፡፡
4) ጃከሊን ማርስ
ያላት የተጣራ ሃብት 23.9 ቢሊየን ዶላር እንደሆነ ይነገራል፡፡ የዓለማችን 33ኛ ሃብታም ሰው ነች። የ79 ዓመቷ ቢሊየነር ጃከሊን ማርስ ‹ማርስ› የተባለው የከረሚላ አምራች ድርጅት አንድ ሦስተኛ ድርሻ ባለቤት ስትሆን በድርጅቱ ውስጥ ለ20 ዓመታት አገልግላለች።
5) ያን ሁዊያን
22.1 ቢሊየን ዶላር የተጣራ ሃብት እንዳላት ይታመናል። በቻይና አንደኛ ሴት ቢሊየነር፣ የዓለማችን 42ኛ ባለሃብትና በሴቶች 5ኛ ሃብታም ሴት ነች። የ37 ዓመት ጎልማሳ የሆነችው ያን የቻይና በግንባታ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሯል ተብሎ የሚጠራው ‘ካንትሪ ጋርደን ሆልዲንግስ’ አብዛኛው ድርሻ ባለቤት ነች።
የኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ ምሩቋ ያን 57 በመቶ የሚሆነውን የድርጅቱን ድርሻ ከአባቷ ነው የወረሰችው።
ሱዛን ክላተን ሌላኛዋ ቢሊየነር ሴት ነች፡፡ 21 ቢሊየን ዶላር የተጣራ ሃብት አላት፡፡ የዓለማችን 46ኛ ሃብታም ነች። የ56 ዓመቷ ሱዛን ክላተን ጀርመናዊ ዜግነት ያላት ሲሆን በመኪና ማምረትና የመድሃኒት ምርቶችን በመሸጥ ላይ የተመሰረተ የንግድ ዘርፍ ውስጥ ነው ተሰማርታ የምትገኘው።
የድርጅቱ መስራች የሆኑት ቤተሰቦቿ ህይወታቸው ሲያልፍ 50 በመቶ የሚሆነውን የመድሃኒት ድርጅት ድርሻ መውረስ ችላለች። ከዚህ በተጨማሪ እሷና ወንድሟ የታዋቂው መኪና አምራች ድርጅት ‘ቢኤምደብልዩ’ 50 በመቶ ድርሻም አላቸው።
የአፕል መስራች የሆነው ስቲቭ ጆብስ ባለቤት ላውረን ፖል ጆብስ የተጣራ ሃብቷ 18.6 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሲሆን ይህም በዓለማችን 54ኛ ሃብታም ሰው ያደርጋታል።ባለቤቷ ህይወቱ ካለፈ በኋላ የድርጅቱን ጥቂት የማይባል ድርሻ በመውረስ 20 ቢሊየን ዶላር የግሏ ማድረግ ችላለች።