ከእያንዳንዱ ኩባንያዎች ጀርባ ያሉና ከ 5% ጀምሮ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ግለሰቦች መረጃ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲመዘገብ የሚያስገድድ አዲስ ደንብ ተፈጻሚ መሆን ጀመረ

በኢትዮጵያ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ እያንዳንዱ ኩባንያዎች ጀርባ ያሉና ከአምስት በመቶ (5%) ጀምሮ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው፣ ትክክለኛ ባለቤቶች ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የጥቅም ተጋሪ የሆኑ ግለሰቦች መረጃ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ቀርቦ እንዲመዘገብ የሚያስገድድ አዲስ ደንብ ተፈጻሚ መሆን መጀመሩ ተሰምቷል።
ይህ በይፋ የወጣው “የሕግ የሰውነት መብት ከተሰጣቸው አካላት ጀርባ ያሉ እውነተኛ ባለቤቶች መረጃ ግልጽነት ደንብ ቁጥር 592/2026”፤ በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ውስጥ ግልጽነትን ለማስፈን၊ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን (Money Laundering) ለመከላከል እና ለሽብርተኝነት የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን ለመግታት የታለመ መሆኑ ተገልጿል።
የድርሻ ምጣኔ እና መመዘኛዎች
አዲሱ ደንብ እውነተኛ ባለቤቶችን (Ultimate Beneficial Owners) ለመለየት የተለያዩ የድርሻ ገደቦችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዋናነት የሚከተሉትን ያካትታል፦
ልዩ ዘርፎች (5% እና ከዚያ በላይ)፦ በማዕድን፣ በኮንስትራክሽንና ሪል እስቴት፣ በአውቶሞቲቭ (የሞተር ተሽከርካሪዎች) እና በገቢ/ወጪ (Import/Export) ንግድ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ከአምስት በመቶ (5%) ጀምሮ የባለቤትነት ወይም የጥቅም ድርሻ ያላቸውን እውነተኛ ግለሰቦች መመዝገብ አለባቸው።
መደበኛ የአክሲዮን ማኅበራት (10% እና ከዚያ በላይ)፦ በተራ የንግድ ኩባንያዎች ውስጥ 10 በመቶና ከዚያ በላይ ድርሻ ያላቸው ግለሰቦች።
የፋይናንስ ተቋማት (2% እና ከዚያ በላይ)፦ እንደ ባንክና ኢንሹራንስ ባሉ ጥብቅ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ደግሞ የ2 በመቶ ድርሻ ያላቸው ባለቤቶች ጭምር መረጃቸው መመዝገብ ይኖርበታል።
የቁጥጥር ተፅዕኖ፦ ከዚህ በተጨማሪ ምንም ዓይነት የገንዘብ ድርሻ ባይኖራቸውም እንኳ በድርጅቱ ስትራቴጂክ ውሳኔዎች ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ፣ ዳይሬክተሮችን የሚሾሙ ወይም በቁጥጥር ስር ያዋሉ ግለሰቦች እንደ እውነተኛ ባለቤት ተቆጥረው እንዲመዘገቡ ደንቡ ያስገድዳል።
የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እና ግዴታዎች
በደንቡ መሠረት በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ ኩባንያዎች በሙሉ የእውነተኛ ባለቤቶቻቸውን መረጃ አሰባስበውና አረጋግጠው በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ መያዝ ይኖርባቸዋል። ይህንን መረጃ ደግሞ ደንቡ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ (እስከ መጪው ጥር/January ወር ድረስ) ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በይፋ አቅርበው ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል።
ኩባንያዎች መረጃውን በየጊዜው የመከለስ፣ በባለቤትነት መዋቅር ላይ ለውጥ ሲኖር በ14 ቀናት ውስጥ የማሳወቅ እና ጥያቄ ሲቀርብላቸው በ48 ሰዓታት ውስጥ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ከደንቡ መጣስ ጋር የተያያዙ ቅጣቶች
ይህንን አዲስ መመሪያ የማይተገብሩ፣ የተሳሳተ መረጃ የሚያቀርቡ ወይም መረጃ በመደበቅ በሌሎች ስም የሚነግዱ ተቋማት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ ተደንግጓል። ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ኩባንያዎች ከ100 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ የሚጣልባቸው ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ፈቃዳቸው ሊታገድ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸው ሊሰረዝ እንዲሁም ከመንግሥት የግዥ ጨረታዎች ሙሉ በሙሉ ሊገለሉ እንደሚችሉ በመመሪያው ላይ ተመልክቷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe