የዓለም የኤድስ ቀን ሲከበር በአዲስ አበባ ከ100 ሰዎች ሦስት ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው አለ ተባለ

የዓለም የኤድስ ቀን ሲከበር ኢትዮጵያ ከ9 ዓመታት በኋላ ኤችአይቪ ኤድስን ለመቆጣጠር ማቀዷ ተነገረ፤የዓለም ፀረ ኤድስ ቀን በተከበረበት በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ ያለው የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ ቢሆንም በጋምቤላ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስርጭት ምጣኔው ከፍተኛ መሆኑን ተነግሯል፤

የቫይረሱ ስርጭት በጋምቤላ 4.1 በመቶ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከ3 በመቶ በላይ ሲሆን በአዲስ አበባ ከመቶ ሰዎች ሦስት ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው አለ ተብሏል።

በዘውዲቱ ሆስፒታል የበሽታዎች መከላከል  ሀላፊና  በዘርፉ ለረዥም ዓመታት የሰሩት ዶ/ር አስቴር ሸዋ አማረ ለዶቼቬሌ እንደነገሩት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የፀረ ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያ መድሃኒት በቋሚነት እየወሰዱ ያሉት ህሙማን ቁጥር 670 ሺ ያህል ነው፡፡ የሟቾች ቁጥርም እየቀነሰ ሲሆን በተለይም ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈው የቫይረሱ መጠን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ ዕድሜያቸው አምስት ዓመት ሳይሞላቸው የሚሞቱ ህፃናትን ሞት ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በለጋሾች ድጋፍ ለሁሉም የኤችአይቪ ኤድስ ተጠቂዎች መድሃኒት በነፃ እየቀረበ ሲሆን ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ያለውን የሆስፒታል ምልልስ  ለመቀነስ ሲባልም ከዚህ በፊት ሲሰጥ የነበረውን የአንድ ወር መድሃኒት ለሶስት ወር ያህል እየተሰጠ ነው፤ መድሃኒቱን በማንኛውም ሆስፒታል የጤና ተቋምና ክሊኒክ እየቀረበ መሆኑንም ዶ/ር አስቴር ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ     በስዋዚላንድ፤       ደቡብ አፍሪካ፤ቦትሱዋና፤ሌሴቶ፤ማላዊ፤ናሚቢያ፤ናይጄሪያ፤ኬኒያና ዚምባብዌ የኤድስ ስርጭት ከፍተኛ መሆኑ የተመዘገበባቸው ሀገራት  ሲሆኑ በኢትዮጵያ  ግን ቀደም ባሉት ዓመታት ኤችአይቪን ለመቆጣጠር በጋራ በተሰራው ስራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው ተብላል፡፡

የዘንድሮው የዓለም ፀረ ኤድስ ቀን ‹የፀረ ኤድስ አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ፤ ወረርሽኙንም መግታት › በሚል ርዕስ ሲከበር ኢትዮጵያ ከ9 ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ በ2030 የኤድስ ህመምን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe