የዓመቱ ምርጦች  መስከረም አበራ /መምህርት/

መስከረም በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህር ናት፤  የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝታለች፤በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ላይ እንዳንድ ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መፃፍ የጀመረችው መስከረም ፅሑፎቿን የሚያነቡ ሰዎች በሚሰጧት አስተያየትና ማበረታቻ የሀገሪቱን የፖለቲካ ውጥንቅጥ በስፋት እንድትመለከትና በድፍረት እንድትተች ዕድል ፈጥሮላታል፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የስርዓት ውጡን ተከትሎ ለውጡ ሀዲዱን እንዳይስት ለሁላችንም የምትሆን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትወለድ ሳይታክቱ ከሚፅፉ የአደባባይ ምሁራን መሀከል አንዷ ናች፡፡

<የዓመቱ ምርጦች አስቴር በዳኔ/ደራሲና ዳይሬክተር>

መስከረም እውነት ብላ የያዘችውን ሀቅ በጨዋ ቋንቋ በረጋ መንፈስ በትህትና መናገር የምትችል ቀንዲል ነች፤ ጋዜጠኛና ደራሲ ቃልኪዳን ሀይሉም መስከረምን ‹ወጥና የማይዛነፍ አቋ፤ የሃሳብ ጥራትና በየጊዜው ብስለትና ከፍታ የማይባት › ሲል ነው የሚገልጻት፡፡ የለውጡ መንግስት ከቡራዩ የማንነት ጭፍጨፋ ጀምሮ እስከ አርሲው ብሔር ተኮር ጥቃት እንዲሁም እስከ ከበቡሽ የድረሱልኝ ጥሪ ድረስ ወንጀለኞችን ወደ ፍትሕ አደባባይ ለማቆም  እያሳየ ያለውን ዳተኝነት ተችታለች፡፡ መስከረም ከኢትጵያዊነትም በላይ የሰው ልጅ ስብዕና በዚህ ደረጃ ላይ ሲወርድ አይታ ፊቷ ለማዞር የሚስችል ሞራል እንደሌላት አሳይታለች፡፡በተለይም እቆየ በሚያገረሸው የማንነት  ጥቃት ጋር ተያይዞ የመፈፀመውን ግፍ ለመሞገት እንቅልፍ እንደሌላት አሳይታለች፤‹ሰው ጥፋት ማጥፋቱ፣ሸርና ደባ መስራቱ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ይህን ስራውን የሚጠራበት ስም አቃሎ ሲጠቀም ማየት በአጥፊው መታረም ላይ ያለውን ተስፋ ያጨልመዋል፡፡ የሰረቀ ሰው ሌብነቱን “ኑሮን ለማሸነፍ መባዘን” ብሎ ከጠራው፣ይህንም ሽባ ሃሳቡን ሌሎች ይቀበሉኛ ብሎ አደባባይ ይዞት ከወጣ ከዚህ ሰው ጋር በምን ቋንቋ ተነጋግሮ መግባባት ይቻላል?>  ትላለች፤

መስከረም በዚህ ብቻ አታበቃም፤ ድርጊቱን እንደ ሌሎች የፆታ አጋሮቿ ዘር ማጥፋት መሆኑን በመኮነን ብቻ ሳታበቃ አካፋን አካፋ ለማለት አልዘገየችም በማስረጃ፤‹ዘር ማጥፋት የሚባለው የአንድ ዘውግ መሞት ብቻ አይደለም፡፡ የዘር ማጥፋት አጭር ትጓሜ ይህ ነው “Genocide is defined as the deliberate and systematic destruction of a racial, religious, political, or ethnic group” በዓለም የውርደት ታሪክ የሆነው የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት በቢለዋ የከተፉት ቱትሲዎች ብቻ አልነበሩም፤ሲዘገብም የሚዘገበው ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች የታረዱበት ዘር ማጥፋት ተብሎ ነው፡፡ እኛ ሃገርም በዘውጋቸው፣ወይ በሃይማኖታቸው ወይ በሁለቱም ማንነታቸው ምክንያት ስም ዝርዝራቸው ተይዞ፣መታወቂያቸው እየታየ ሰዎች ታርደዋል፡፡እውነታው ይህ ነው! ይህን መመደበቅ፣ማድበስበስ ሰው በላነት ነው፤ከሁሉም በላይ ወንጀል ነው፡፡ በሃገሬ ስለታየው ውርደት ከዚህ በላይ ምንም ማለት አልችልም፤አዝኛለሁ፣የምሰማውን መቋቋም የማልችል ደካማ ሆኛለሁ፣መንፈሴ ሳስቷል……› ነው ያለችው፡፡

<የዓመቱ ምርጦች ‹ኣርባዕቱ› እንስት ተሟጋቾች>

በቅርቡም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ በሌላኛዋ ምክትል ከንቲባ ያለ ህዝብ ምርጫና እውቅና ቦታ መለዋወጣቸው አላሳመናትም ፤ ይልቁንም ምክትል ከንቲባዋ ወደ ቢሮአቸው በገቡ ማግስት ለዓመታት ‹ቤት እናገኛለን› ብለው ገንዘባቸውን ሲቆጥቡ በነበሩ የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝጋቢዎች ላይ የወሰዱትን  ፍርደ ገምድል ውሳኔ ተችታላለች፤ ‹ድሞውኑ በአዲስ አበባ የከንቲባነት ወንበር ላይ ኦሮሞና አማራ ብቻ ይፈራረቁበት ያለው ማነው?› በማለትም ትጠይቃለች፤ ‹ሰው ለዘመናት የኑሮን ጫና ተቋቁሞ፣ከልጆቹ ጉሮሮ እየቀነሰ፣የህይወት አምሮቱን ወስኖ ቤት አገኛለሁ በሚል ተስፋ ቆጥቦ የሰራውን ቤት ስልጣን በሚሰጠው እብሪታዊ ቀማኛት የእኛ ላሉት ሁሉ ማከፋፋላቸውን የምናውቀው ሃቅ ነው፡፡› የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የሰሞኑ የድምጽ ንግግርንም ለማድበስበስና የግላቸው አቋም ተደርጎ እንዲወሰድ የሚሞከርበትን ስንኩል አካሄድ  ‹ለማንኛውም ሽመልስ አብዲሳ ምስጋና ይሁነውና መጋረጃ ተቀዷል፣ገበናው ፍንትው ብሏል….. ከዚህ በኋላ የሚታለል የለም፤የምታታልሉት ራሳችሁን መሆኑን እወቁ!> በማለት ነው የፖለቲካ ቁማሩን ጨዋታ ያቃለለችው፡፡ ያም ሆኖ ሰሞኑን መነጋጋሪያ የሆነውን የአቶ ሽመልስን ንግግር የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ከማውገዝ ይልቅ ሊያስተባብል መባተሉ ገርሟታል፤‹የሃጫሉን ሞት ተከትሎ የደረሰውን የህይወት እና የንብረት ውድመት ከዚህ የበለጠ ተስፋፍቶ ወደ ሱዳን እንዳይዛመት፣ወደ ጅቡቲ እንዳይገሰግስ፣ዩጋንዳን እንዳያጥለቀልቅ ፣ኬንያን እንዳይረብሽ ቀን ከሌት ደፋ ቀና ብሎ በአጭር እንዲቀር ያደረገውን የኦሮሚያን የፀጥታ መዋቅር ማን እውቅና ይሰጠው ነበር?› ከለውጡ ጋር ያለው የብሔርተኞች የፖለቲካ እቅድ  ሀገሪቷን አደጋ ላይ ስለመጣላቸው መስከረም ሁሌም ትናገራለች፤ሀገሪቷም ህመም ላይ መሆኗን ታምናለች፤‹ኢትዮጵያችን በፅኑ ህሙማን ክፍል ያለ ታካሚን ትመስላለች። ህመሟ ብርቱና ለዘመናት የተጠራቀመ ነው።ሁነኛ ሃኪም (ከመሪም ከተመሪም)ሳታገኝ በመኖሯ የቆየው በሽታዋ እየደረደረ፣በላዩ ላይ ሌላው እየተጨመረ በፅኑ ታማሚ አድርጓታል።› ባይ ነች፤

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ  የሀገራችን ሚዲያዎች ቢያንስ የመንግስቶቹ በተሻለ የሙያ ነጻነት ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ተስፋ ነበር፤ ይህ ተስፋ በመስከረም ዘንድም የነበረ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንደ ፋና ያሉ  ሚዲያዎች ሳይቀሩ አንድን ግልሰብ ይዘው ስቱዲዮ በመግባት በስፍራው የሌለን ግለሰብ ስም እያነሱ የማብጠልጠላቸው ጉዳይ ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነባት አልሸሸገችም፤‹ ትዝብቴ መንግስትን ይመለከታል፡፡ ለውጥ ለውጥ ሲባል አንድ ተስፋዬ የነበረው ሚዲያዎች እንዲህ ካለ የፕሮፖጋንዳ ስራ ወጥተው ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያስችሉ ይሆናሉ የሚል ነበር:: አሁን የተያዘው ግን ወያኔ ሞላ አስገዶምን አምጥታ ታስቀባጥር የነበረውን የመድገም ነገር ነው፡፡ መጥፎውን አዙሪት የመዞር ትልቅ እርግማን!>ብላዋለች፡፡ ከለውጡ በኋላ እንደሚዲያው ሁሉ የፍትሕ ስርዓቱም ከመሻሻል ይልቅ የባሰ አለ የሚያሰኙ ድርጊቶች እዚህም እዚያም ታይተዋል፤ ለፍትህና ለእኩልነት፤ እንዲሁም ለሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት እንደሚታገል ፀሐፊ መስከረም ቅሬታዋን ለአዲሷ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ይድረስ ብላለች፤ ‹እንደሚታወቀው እርስዎ ወደ ስልጣን ሲመጡ የዳኝነት ስርዓቱ ይሻሻላል በማለት ብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ አድርገው ነበር። ነገር ግን ብዙ ሳንቆይ ትዕዛዝ የሚቀበል አስፈፃሚ አካል ጠፋ እርስዎም እርምጃ ሳይወስዱ ቀሩ።› ብላለች፡፡

<የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በዘር ላይ የተመሠረተ ያለዉ ጥቃት በአስቸኳይ…>

የኦሮሚያ ብልፅግና (የኦሮሞ ብሔርተኞች) አዲስ አበባን ከራሷ ማንነት ለማናጠብና ለመጠቅለል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እያየለ በመጣበት ወቅት የመስከረም ግምገማ ይህንን ይመስላል፤ ‹እነሱ በአዲስ አበባ ላይ ያላቸውን አቋም ውስጥ ለውስጥ ከሚሰሩት ባለፈ በአቶ ሽመልስ አብዲሳና በአቶ ለማ መገርሳ በኩል በግልፅ ነግረውናል። እንዳለመታደል ሆኖ ይህንን የታቀደልንን ሴራ በግልፅ ተረድቶ የሚመክት አደረጃጀት አላየሁም። የአዲስ አበባን ጉዳይ በንቃት ይዞ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ባልደራስ የብሔርተኞቹ ሹል ጥፍሮች አርፈውበት አቅሙ ተወስኗል። የአማራ ብልፅግና አዲስ አበባ ውስጥ ድርሻ እንዳለው እንኳ የሚያውቅ አይመስለኝም። አብን አዲስ አበባ ላይ እዚህ ግባ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያደርግ አላየሁም። ኢዜማ እስካሁን ከአንፀባረቀው አቋም እና አካሄድ አንፃር ተስፋ የሚጣልበት ሆኖ አልታየኝም(የወደፊቱ የሚታይ ይሆናል)።በተናጥል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም እነዚህ ብሔርተኞች በሚያሾልኩልን መረጃ የፕሮፓጋንዳ ምላሽ ከመስጠትና ከሰሞነኛ ጫጫታ ያለፈ አይደለም። አዲስ አበባ የታቀደላትን መከራ የሚመክት የትግል ስልት ትሻለች። አብይ ኢትዮጵያን ይወዳል የሚለው ጨዋታም የትም አያደርሰንም።› መስከረም በማህበራዊ ትስስር ገፆች ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መፍካት በትጋት ከምትፅፋቸው ሀሳቦች በተጨማሪ በአባይ ሚዲያ ላይ የተለያዩ ግለሰቦችን ቃለ መጠይቅ ታደርግላቸዋለች፤ እሷም በሚዲያዎች ላይ ስትጋበዝ አቋሟ ግልፅ ለማድረግ አትቸገርም፤

በተለይም በተደጋጋሚ ቀርባ ትንታግነቷን ያሳየችበትን ቃለ ምልልስ ከስዩም ተሾመ ጋር ታደርጋች፡፡ ስዩም እንደ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን እንደ ተወያይም እየተከራከረ የአቋም ለውጥ እንድታሳይ ቢሞግታትም ‹አንድ ኢንች!› ከአቋሟ ፈቀቅ ሳትል ከስቱዲዮ እንደምትወጣ አሳይታለች፤ ስዩም ‹መስኪ የምትናገራቸው ቃላት እንደ ሰይፍ የሰሉ፣ እንደ መርፌ የሾሉ፣ እንደ ሳማ የሚለበልቡ ናቸው።› በማለት ምስክርነቱን ሰጥቶላታል፡፡ ‹ዕድላችን አንድ ነው› የምትለው መስከረም ‹ ወይ አብሮ መኖር አልያም አብሮ መጥፋት ነው፤በማናቸውም ጉዳዮች ነፍሴን አስይዤ ፤በህይወቴ ተወራርጄ ነው የምናገረው፤› ትላለች፡፡ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ለሀገሪቱ መላ ለማፈላለግ ከመረጣቸው 50 ሰዎች መሀከልም አንዷ ናት መስከረም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe