ቀዳማይ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራትን የሚመሩ ወንድ መሪዎች የትዳር አጋሮቻቸው በልዩ ልዩ ተግባሮቻችው ነው የሚታወቁት፡፡ አንዳንድ መሪዎች ሚስቶቻቸውን በአደባባይ ይዘው ሲታዩ ሌሎች ‹ወንድ ከደጅ ሴት ከማጀት› የሚለውን የሀገራችን ብሂል ወደ የቋንቋቸው አስተርጉመው ብቻቸውን በአደባባይ ይታያሉ፤ ሌሎች የሀገራት መሪዎች ደግሞ ከአንድ በላይ ሚስት በማግባት እየቀያየሩ ህዝብ ፊት ይታያሉ፤ ከሁሉም የሚገርሙት መሪዎች ግን ስንት ሚስት እንዳላቸው እንኳ ህዝቡ ራሳቸውም የማያውቁ መኖራቸው ነው፡፡
ከዚህ አንፃር በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን ላይ የሚወጡ ሀገራት መሪዎች ሚስቶች ቀዳማይ እመቤት ወይም /First lady/ ተብለው ይጠራሉ፤ ብዙ ጊዜ ይህ ስልጣን በወንዶች እጅ ስለሚገባ ነው እንጂ ሴት የሀገር መሪ ባልም ቀዳሚ ጌታ ወይም /First Gentelman/ ተብሎ እንደሚጠራ ይነገራል፡፡ በዚህ ረገድ የመጀመሪያው የሀገር ቀዳሚው ‹ጌታ› ማን እንደሆነ የምታውቁ ሰዎች ብታጋሩን ደስ ይለናል፡፡
በየሀገራቱ ያሉ ቀዳማይ እመቤቶች እንደ ባሎቻቸው ባይሆንም በልዩ ልዩ ተግባሮቻቸው የሚታወቁ አሉ፤ አንዳንዶቹ የፋሽን ተከታይ በመሆን ባላቸውን ልብስና ጫማ ብዛት ሲታወሱ ሌሎች እንደ ሞዴልና የፊልም አክተር በየመድረኩ የጋዜጠኞች ካሜራ ትኩረት ሆነው ይታያሉ፤ ጥፍራቸውን ሲሞርዱና በየሪዞርቱ እየዞሩ ጀርባቸውን ማሳጅ በመታሸት የሚያሳልፉ ቀዳማይ እመቤቶች የመኖራቸውን ያህል አደባባይ ወጥተው ከባለቤታቸው ባላነሰ የማህበረሰቡን ችግሮችን ለመፍታት በግላቸው አልያም ከባላቸው ጋር ሆነው የሚታትሩ ቀዳማይ እመቤቶች ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ግን አሉ፡፡
በሀገራችን በ2010 ዓ.ም የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለዚህ ክብርና ትልቅ ሀገራዊ ስልጣን ለመብቃት የባለቤታቸው ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ወሰን የለሽ ድጋፍ ቀዳሚ ስለመሆኑ የተናገሩት በመጀመሪያው የፖርላማ ንግግራቸው ወቅት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ የእሳቸውን ንግግር ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖርላማ ወደ ቤተመንግስት ሲገቡ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ይዘው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታዩ ቀዳማዊት እመቤቷ እንደ ባለቤታቸው ተናጋሪ፤ ተስፈኛና ታታሪ ስለመሆን አለመሆናቸው ይሰጡ የነበሩ ግምቶች ብዙ ነበሩ፡፡
ውሎ ሲያድር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤት ወ/ሮ ዝናሽ ከባለቤታቸው ጋር ብቻ ተያይዘው ወደ አደባባይ መውጣታቸውን ትተው የራሳቸውን ፕሮጀክቶች ቀርፀው ትምህርት ቤት በሌለባቸው የገጠር መንደሮች በመዝለቅ ትምህርት ቤቶችን ማስገንባት ጀመሩ፤ ወ/ሮ ዝናሽ በተለይም እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት መጀመሪያ ጀምረው በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎችና መንደሮች የመሰረት ድንጋይ ሲጥሉ ዓመቱ የምርጫ ማካሄጃ ከመሆኑ ጋር አያይዘው ‹ጠቅላይ ሚነስትሩ የምርጫ ዘመቻ› በባለቤታቸው በኩል ማድረግ የጀመሩ አድርገው የገመቱ ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ወ/ሮ ዝናሽ በየክልል ከተሞች በያዝነው ዓመት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠው አስገንብተው ያጠናቀቋቸው የትምህርት ቤቶች ብዛት 20 በላይ ነው፤ ወ/ሮ ዝናሽ ከመንግስት በጀት ሳያስመድቡ ነው እነዚህን ሁሉ ትምህር ቤቶች ያስገነቡት፤ ከባለቤታቸው ጋር ለስራ ጉዳይም ሆነ ለጉብኝት ከሀገር ሲወጡ ከእጃቸው የማይለይ የትምህርት ቤት ማሰሪያ ፕሮፖዛል አይጠፋም ነው የሚባለው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ አጀንዳቸውን ከጨረሱ በኋላ ወ/ሮ ዝናሽ የትምህርት ያላገኙ በየገጠሩ ለሚገኙ ህጻናት ትምህርት ቤት ማስገንቢያ ፕሮጀክት እቅዳቸውን በማቅረብ ለጋሾች የቻሉትን ያህል እንዲደግፉ ይጠይቃሉ፡፡
ከውጭ ለጋሾች በላይ ደግሞ ባለቤታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከመደመር መፅሐፍ ሽያጭ ያገኙትን ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ለቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በመለገሳቸው እያንዳንዳቸው በአማካይ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣባቸውን ትምህርት ቤቶች ለማስገንባት ችለዋል፡፡ያስገነቡትንም ትምህርት ቤቶች በአካል ተገኝተው በማስመረቅ ቁልፉን ለአካባቢው ህብረተሰብ ሲያስረክቡ ከርመዋል፡፡
በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ያስገነቧቸው ሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የትምህርት ፍላጎት ባለባቸው አካባቢዎች የተገነቡ ናቸው፤ ሩቅ የእግር መንገድ በሚያስኬዱት ስፍራዎችና ምንም አይነት ትምህርት ቤቶች ባልተገነቡባቸው ቦታዎች በጥናት የተሰሩ ናቸው፡፡ ቀደም ሲል ወታደራዊ ካምፕ የነበሩባቸው ቦታዎችና እንደ ሱማሌ ክልል ባሉ ቦታዎች ደግሞ የማሰቃያ ስፍራዎች የነበሩ ስፍራዎች ዛሬ ትምህርት ቤት ተገንብቶባቸው ተማሪዎችን መቀበል ጀምረዋል፡፡ትምህርት ቤቶቹ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የተገነቡ መሆናቸውን ስንመለከት ደግሞ እመቤቷ የሁሉምን ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትምህርት ፍላጎት ለመቅረፍ ፍላጉት እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል፤
ትምህርት ቤቶች በዉስጣቸው የአስተዳደር ህንጻ፤የመማሪያ ክፍሎች ፤ላብራቶሪ ፤የቤተ መጽሀፍ የኮምፕዩተር ላብራቶሪ እና የመጸዳጃ ህንጻዎችን ያካተቱ ሲሆን ቀዳማዊት እመቤት ከትምህርት ቤቱ ግንባታ በተጨማሪም ለተማሪዎቹ ዩኒፎርም ፣ቦርሳና የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን በስጦታ አበርክተዋል።ትምህርት ቤቶቹ አገልግሎት ሲሰጡ በአንድ ፈረቃ 1800 ያህል ተማሪዎችን የመቀበል አቅም አላቸው ተብሏል፡፡ትምህርት ቤቶቹ በአፋር ክልል ዱብቲ ፣በጋምቤላ አኝዋክ ዞን፣ በቤንሻንጉል ክልል አሶሳ እና መተከል ፣ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ 02 እና 06 ቀበሌዎች ፣ በአማራ ክልል ጎንደር ደባርቅ ከተማ እና ዋግኽምራ ዞን ሳህላ ሰለምት ወረዳ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን፤ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ውጫሌ ወረዳ፤ በሊበን ጭቋ ወረዳ ወዘተ የተገነቡ ናቸው ፡፡
ቀዳማዊት እመቤቷ ያስገነቧቸውና ተማሪዎችን ተቀብለው እያስተማሩ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ዝርዝር በከፊል የሚከተለውን ይመስላል፤
1ኛ/ በምእራብ ጉጂ ሱሮ ባርጉዳ የተገነባዉ የኢፈ ቱላ ሱሮ ብርሀን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፡፡
2ኛ/ በኦሮሚያ ክልል ሎዛ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
3ኛ/ በ13.8 ሚሊየን ብር የተገነባዉ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዉጫሌ ወረዳ የሚገኘዉ የኢፋ ሰላሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት
4ኛ/ በደቡብ ወሎ መስተዳድር ዞን በአልብኮ ወረዳ በጦሳ ፈላና ቀበሌ በቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት የተገነባውን የወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፡፡
5ኛ/በኦሮሚያ ብ/ክ/መ ምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላ ወረዳ ያስገነባዉን ኢፋ ሊበን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፡፡
6ኛ/ በአማራ ብ/ክ/መ ደባርቅ ከተማ አስተዳደር የደባርቅ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
7ኛ/በአማራ ብ/ክ/መ በዋግህምራ ዞን ሳህላ ሰየምት ወረዳ ብርሀን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፡፡
8ኛ/ በሶማሌ/ብ/ክ/መ በጅግጅጋ ከተማ በአመንጄ ዮጎል ቀበሌ ያስገነባዉን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፡፡
9ኛ/በሶማሌ/ብ/ክ/መ በጅግጅጋ ከተማ ገራድ መክተል ጣሂር ሁለተኛውን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
10ኛ/ በቤ/ብ/ክ/መ በአሶሳ ዞን አሶሳ ወረዳ ነባር ሆሚሽጋ ብርሀን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
11ኛ/ በጋ/ብ/ክ/መ በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር 05 ቀበሌ ያስገነባዉን ጋምቤላ ብርሀን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
12ኛ/ በኦሮሚያ/ብ/ክ/መ በምእራብ ጉጂ ሱሮ ቡርጉዳ ወረዳ የተገነባዉ ኢፋ ሱሮ ቡርጉዳ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
13ኛ/ በአፋር/ብ/ክ/መ በአዉሲ ራሱ ዱብቲ ወረዳ የተገነባዉን ዱብቲ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
14ኛው በደ/ብ/ብ/ክ/መ በጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳ ባንቆ ዳዳቱ ቀበሌ ባንቆ ዳዳቱ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት
15ኛው በቤንሻልጉል ጉሙዝ /ብ/ክ/መ መተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ዋላምባ ቀበሌዋላምባ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
16 ኛ/ በኦሮሚያ/ብ/ክ/መ ሀዊ ጉዲና ወረዳ ዳሮ ቢሊቃ ቀበሌ ኢፈ ቢሊቃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
17ኛ/ በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ማሻ ወረዳ ደገሌ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት፤
ቀዳማዊት እመቤቷ ከትምህርት ቤቶች ግንባታ በተጨማሪ በልዩ ልዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የህጻናት እንክብካቤ ማዕከላትን በማስገንባትና የውስጥ ቁሳቁስ እንዲያሟላ በማድረግ አርአያ የሆነ ስራ አከናውነዋል፡፡ እንደ አብነትም በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት የተገነባው ብርሃን የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ግንባታው ተጠናቆ ባለፈው ዓመት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ከተለያዩ ለጋሽ አካላት ያሰባሰባቸዉን የህክምና እቃዎች እና መገልገያ መሳሪያዎችም ለጎንደር ሆሰፒታል በስጦታ መልክ አስረክቧል፡፡ የተሰጡ እቃዎች የህፃናት አልጋ ፤ የደም ማስቀመጫ ፍሪጆች ፤ ICU አልጋ፤ የላብራቶሪ ማሽኖች በአጠቃላይ አስራ ሰባት (17) የህክምና ቁሳቁሶች በአጠቃላይ ከ 5,630,000 ብር በላይ ግምት ያላቸዉን የህክምና እቃዎችን ፤ ለጎንደር ሆስፒታል፤ ለሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆሰፒታል እና ለአማኑኤል አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ለ30 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አይነ-ስውራን ተማሪዎች የላፕቶፕ ስጦታ ማበርከታቸው የሚታወስ ሲሆን ስጦታዉ የተበረከተላቸዉ ተማሪዎች ትምህርታቸዉን ለመከታተልና የመመረቂያ ጽሁፋቸዉን ለማዘጋጀት የላፕቶፕ ችግር ያለባቸዉ ተማሪዎች ተለይተዉ ነዉ፡፡ ላፕቶፓቹ ታይዋን ከሚገኝ ASHL FOUNDATION ከተባለ ድርጅት በጽ/ቤታቸዉ በኩል የተገኙ ናቸዉ፡፡
ከ4 ህጻናት ማሳደጊያዎች የተመረጡ ወላጆቻቸውን ያጡ 5 የ7ኛ ክፍል ተማሪዎችንም ወደ ናይጀሪያው በሮቻስ ፋዉንዴሽን አማካይነት ነጻ የትምህርት እድል አፈላልገው ከመላካቸው በፊት ታዳጊዎችን ቢሮአቸዉ ድረስ ጋብዘው አነጋግረዋል፡፡የቀዳማዊት እመቤት ፅ/ቤት ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም የተከሰተውን የCOVID-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲያግዝ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለሰብሳቢ ኮሚቴው አስረክቧል ፡፡ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በፅ/ቤቱ ስም ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ፍራሽ፣ አንሶላ፣ብርድልብስ ዊልቸር እና የህክምና እቃዎችን ለጤና ሚኒስትር በስጦታ ስለማበርከታቸው በወቅቱ ተዘግቧል፡፡
በጽ/ቤቱ በተለያዩ ከተሞች እንዳደረገዉ ሁሉ የዊልቸር ድጋፍ በደቡበ እና በሲዳማ ክልሎች ለሚገኙ 28 አካል ጉዳተኞች ያበረከተ ሲሆን ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸዉ በሃዋሳ ክተማ ተገኝተው የዊልቸር ስጦታው አስረክበዋል፡፡ ዊልቸሮቹ የተገኙት ሞቢሊቲ ወርልድ ዋይድ ከተባለ የውጭ ሃገር ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን ወደ አገር ውስጥ የገባው የአብ ሜዲካል ሴንተር በተባለ ሃገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ነዉ ተብሏል፡፡
ከዚህ ሌላም ለገጣፎ አካባቢ በሚገኘው ዲቦራ ፋዉንዴሽን ማእከል የአእምሮ ዉስንነት ላለባቸዉ ወጣቶች አገልግሎት የሚዉል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በዲቦራ ፋዉንዴሽን ለሚገነባዉ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት ፕሮጀክት 19 ሚሊዩን ብር መድቧል፡፡ ለኢፋ ቦሮ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይም በዚህ ዓመት ተቀምጦ ግንባታው እየተፋጠኑ ካሉ ትምህርት ቤቶች መሀከል ይጠቀሳል፡፡ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ክ/ከተማ በ3.3 ሄክታር መሬት ላይ በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት እየተገነባ የሚገኘዉና 300 አይነስዉራንን የማስተናገድ አቅም ያለዉ ዘመናዊ የአይነስዉራን አዳሪ ትምህርት ቤትም ግንባታው በመጪው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሌላው ቀዳማዊት እመቤት ጽ / ቤት ከተባባሩት አረብ ኤሚሬት MohamedBinZayed ለጋሽነት ለችግረኞች ድጋፍ ለመስጠት እየተገነባ ያለው የዳቦ ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ሲውል በቀን አንድ ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም እንዳለው ተገልጧል፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት 4 ልጆችን በአንድ ጊዜ ለተገላገለች የሰመራ ነዋሪ የህጻናቶቹን የህክምና ወጪ 700 000 ብር መሸፈኑም የሚታወስ ሲሆን በተገነቡት ትምህርት ቤቶችወ/ሮ ዝናሽ እየተገኙ ከተማሪዎች ጋር ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸወን አኑረዋል፡፡
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ ለዚህም የበጎ አድራጎት ስራቸው ከተለያዩ አካላት የእውቅና የክብር ሽልማት ያገኙ ሲሆን በትምህርት ላይ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የምስጋናና የእውቅና መርሃ ግብር የኢፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅቶ ከፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ባለፉት አመታት ትምህርት ላይ አተኩረው በመስራታቸውም ከኦሮሚያ ት/ት ቢሮ የምስክር ወረቀትና ለላቀ የትምህርት ልማት አጋርነት ሽልማት እንደተበረከተላቸው ይታወሳል፡፡
የካቲት 5 ቀን 1970 ዓ.ም ጎንደር ውስጥ የተወለዱት ወ/ሮ ዝናሽ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ትዳር ከመመስረታቸው በፊት ሁለቱም በውትድርና ሙያ ሀገራቸውን ያገለገሉ ሲሆን የተዋወቁትም እዚያው ነው፡፡ ወ/ሮ ዝናሽ በወቅቱ የሙዚቃ ሰው እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አሁን በበጎ አድራጎት ስራዎችና በዘማሪነት የሚታወቁት ወ/ሮ ዝናሽ ዲቦራ፤ ርብቃና አሜን የተባሉ የሶስት ልጆች እናት ሲሆኑ ከሶስት ዓመት በፊትም ሚሊዮን የተባለ የ15 ቀን የጉጂፈቻ ልጅ ተቀብለው እያሳደጉ ነው፡፡
ይህንኑ ትጋታቸውን መሠረት በማድረግ ቁም ነገር መፅሔት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸውን የ2013 ዓ.ም ምርጥ የበጎ አድራጎት ሰው ብላቸዋለች፡፡