የዓመቱ ምርጦች ‹ኣርባዕቱ› እንስት ተሟጋቾች

በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኤሌትሪክ በሩቁ ሲባል ያደገው ትውልድ አባላት ናቸው፤ ከፖለቲካ ኤሌትሪክ መጨበጥ በሚመረጥበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዋጋ እንዳጣ ሸቀጥ ሲቀል አይተዋል፤ የፖለቲካ ፖርቲ አባላትና መሪ ምሑራን ሳይቀሩ በብሔር ካባ ተሸሞንሙነው ‹ቅድሚያ ለብሔሬ› በሚሉበት በዚህ ሰዓት እነዚህ አራት እንስቶች ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግና እኩልነት እንዲሰፍን የሀሳብ ሙግት ይዘው አደባባይ የወጡ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እንስቶች መዓዛ መሐመድ/ጋዜጠኛ/ መስከረም አበራ/ መምህርት/ አስቴር በዳኔ/ደራሲ/ እንዲሁም ኤልሳቤት ከበደ/የህግ ባለሙያ/ ኢትዮጵያዊነት ጊዜያዊ ስልጣንና ዝና ማግኛ ሲሆን ሁኔታውን በዝምታ መመልከት አልፈለጉም፤ ይልቁንም በራቸውን ዘግተው ‹ፖለቲካና ኤሌትሪክ በሩቁ› ከሚሉት ከብዙዎቹ የሀገራችን እንስቶች ተለይተው በራሳቸው ጎዳና የሚራመዱ ናቸው፤ ሴትነት ለፖለቲካ ሰዎች የስልጣን መወጣጫ መሰላል ነው፤ ይህንን ሸፍጥ ጠንቅቀው የተረዱት እነዚህ እንስቶች ያመኑበትን ነገር ያለምንም መሸማቀቅና ይሉኝታ በየሚዲያውና በማህበራዊ መድረኮች ላይ በማስተጋባት ላይ ናቸው፡ ፡ የሀገራችን ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ዘኬ ከመልቀም የዘለለ ታላላቅ ሃሳቦችን ማራመድ የሚችሉ መሆናቸውን እያስተጋቡ ነው፡፡

[ንጉሱ ጥላሁን የሽመልስ አብዲሳን ንግግር ተቹ]

እየተጠናቀቀ ባለው 2012 ዓ.ም የሀገራችን ፖለቲካ ብዙ ውጣ ውረድና የሰብዓዊ ቀውስ የታየበት ዓመት እንደሆነ ይታወቃል፤ የሰዎች በግፍ መገደል፤ ቤትና ንብረታቸው መውደም፤ ኢ ሰብዓዊ የሆነ የጭካኔ አያያዝና ግፍ ታይቷል፡፡ ይህ ሁሉ የአደባባይ ኢ ሰብዓዊ ተግባር ሲፈፀም በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ በማንነታቸውና በእምነታቸው ሳቢያ ጭዳ ሲሆኑ አንዳንዶች ‹ሀገር ለማዳን ፤ ሌሎች የፖለቲካ ስርዓቱ ችግር እንዳይገጥመው ሌሎች ደግሞ ጥቅማቸው እንዳይነካ› በሚል ዝምታን ሲመርጡ እነዚህ አራት እንስቶች ግን ለህሊናቸው መገዛትን ቀዳሚ ዓላማቸው አድርገው ነበርና የተሰተውን ነገር በይፋ አደባባይ በመውጣት ተናግረዋል ፤ አውግዘዋልም፤ አራቱ እንስቶች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ብቻ በጋራ የሚያኗኗር ድርና ማግ መሆኑን ከመስበክም አልፈው በብዙዎች ተስፋ ተጣለበትን የለውጥ ጎዳና ገንቢ በሆነ መልኩ ሲመለከቱ ቆይተዋል፡፡ ቀዳሚውን ህወሃት መራሽ መንግስትንም በግላቸው ሲቃወሙ ፤ ሲተቹና የአፖርታይድ ስርኣትነቱን ሲያጋልጡ የነበሩ ናቸው፡፡ የብዙዎች ተስፋ የሆነው ለውጥ በጥቂቶች የቀነጨረ ብሄረተኝነት ፖለቲካ ወደኋላ ሲጎተት ብሎም የሰዎችን ህይወትና ንብረት በአደባባይ ሲወድም ድርጊቱን ከማውገዝ አልፈው አካፋን በስሙ ‹አካፋ!› ብለው ለመጥራት አልዘገዩም፤

በመሆኑም እነዚህ አራት እንስቶች በየተሰማሩበት ሙያ ሆነው የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ብለው በአደባባይ ሀሳባቸውን በማካፈል ብቻ ሳይወሰኑ በመሟገት ሃሳብና እምነታቸውን እንደ እነርሱ ወጥተው የመግልጽ ዕድሉ ለሌላቸው ሚሊዮኖች ተስፋ መሆናቸውን አሳይተዋል፤ በተለይም ከህብረተሰቡ ግማሽ ናቸው እየተባለ የፖለቲካ መነገጃ ለሆኑትን የሀገራችን ሴቶች አንደበት ሆነዋል፤ በመገፋት ሳይሆን በብቃት ሀላፊነት መቀበል የሚችሉ ሴቶች መኖራቸውን አርአያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላል፤ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ሲባል የካቢኔውን 50 ከመቶ ሴቶች ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ የጾታ ተዋፅኦ ላይ እንጂ ብቃት ላይ ባለማተኮሩ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ካቢኔው ሁለት ሴት ሚኒስትሮችን ቀንሶ ወደ 40 ከመቶ ወርዷል፡፡ የሴቶች ተሳትፎ በተዋፅኦ ሳይሆን በብቃት ላይ የሚመሰረት ከሆነ በቂ የትምህርት ዝግጅትና ትጥቅ ባላቸው የማይዛነፍ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ባላቸው ጥቂት ሴቶች ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑንም የቁም ነገር መፅሔት ኤዲቶሪያል ቦርድ ለብዙዎች ማሳያ የሆኑ እነዚህን አራት ተሟጋቾች ‹የ2012 ዓ.ም የዓመቱ ምርጦች› በሚል ሰይሟቸዋል፡፡ /ዝርዝሩን በገፅ 5 ላይ ይመልከቱ/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe