የዓመቱ ምርጦች – ኤልሳቤት ከበደ/የሕግ ባለሙያ/

የህግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ የሆነችው ኤልሳቤት ከበደ ባለፈው መጋቢት ወር ማብቂያ ላይ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ‹ከሀረሪ ክልል ተልከን ነው የመጣነው› የሚል የመያዥያ ትዕዛዝ የያዙ ፖሊሶች ቤቷን ያንኳኳሉ፡ ፡ ኤልሳቤት ሀገር አማን ነው ብላ በሯን ስትከፍት የመጠሪያ ደብዳቤ በማሳየት ይዘዋት ወደ አዲስ አባባ ፖሊስ ኮሚሽን ይሄዳሉ፤ ‹በወቅቱ በፒጃማ እያለሁ ነው ይዘውኝ የወጡት፤ ልብስ ለመቀየር እንኳ ጊዜ አልሰጡኝም› ትላለች፡፡ ጠዋት ከእንቅፍፏ ቀስቅሰው ወደ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዷት ኤልሳቤት እስከ ቀኑ 11 ሰኣት ድረስ ከፖሊስ ጣቢያ እንዳትወጣ በማድረግ የመብት ጥሰቱ ተጀመረ፡፡ ኤልሳቤት የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበርን በሙያዋ የምትረዳ ጠበቃና የህግ አማካሪ በመሆኗ መብትና ግዴታዋን ጠንቅቃ የምታውቅ ነች፡፡

አንድ ሰው በፖሊስ ተጠርጥሮ ሲያዝ በምን ምክንያት እንደተያዘ ሊነገረው እንደሚገባ በማስረዳት ‹የተያዝኩበት ምክንያት ምንድነው?› ብትልም የሚሰማት አልነበረም፤ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ለምታውቃቸው የበላይ ሃላፊዎች ሳይቀር ጥፋቴ ምንድነው? ብትልም ይዘዋት እንዲመጡ ከሀረር አዲስ አበባ ለተላኩት ፖሊሶች አሳልፈው ከመስጠት የዘለለ ሊያደርጉላት የሚችሉት ጉዳይ አልነበረም፤ እናም አንድ ቀን እዛው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ከህግ ውጭ መብቷ ተጥሶ አሳድረዋት በማግስቱ ጠዋት በተዘጋጀው መኪና ወደ ሀረሪ ክልል ይዘዋት ይሄዳሉ፤ መጀመሪያ ላይ ‹በሀረሪ ክልል የተፈፀመ ወንጀል ስላለ ለምስክርት ትፈለጊያለሽ› ብለው ነበር መኪና ላይ የጫኗት፤ከአዲስ አበባ ይዘዋት በሄዱ በማግስቱ ሀረሪ ክልክ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበች፡፡ ከአዲስ አበባ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀረሪ ክልል የተወሰደችበትን ወንጀል ፖሊስ ‹የጥላቻ ንግርን አዋጅን በመተላለፍ› መጠርጠሯን በመግለፅ ፍርድ ቤቱን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይጠይቅባታል፤ ፍርድ ቤቱም ይህንኑ ይፈቃዳል፡፡ ኤልሳቤት ያለምንም ክስ ከአዲስ አበባ ወደ ሀረር መወሰዷና ያለምንም ክስ ከአንድ ወር በላይ ትታሰራለች፡፡

<በአዲስ አበባ ሕገወጥ የመሬት ወረራ የወጣው ሪፖርት “ሃሰተኛ” ነው- የቀድሞው ምክትል…>

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ፤ የኢትዮጵያ ሴት ህግ ባለመያዎችን ማህበርና ታዋቂ ሰዎች መግለጫ በማውጣት ጭምር ቢያወግዙትም ኤልሳቤት ‹ፈጸመች› የተባለው ወንጀል ምን እንደሆነ በግልጽ ለፍርድ ቤት ሊቀርብ አልቻለም፤ ይልቁንም ኤልሳቤት ማበሚያ ቤት እያለች ወደ ፍርድ ቤት ሳትወሰድ የጊዜ ቀጠሮ የሚራዘምባት ሆነች፡፡ ኤልሳቤት ከበደ ለዚህ ኢ ህገ መግስታዊ እስር ያበቃት ሌላ ሳይሆን በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ በሀረሪ ክልል ውስጥ የሚፈፀመውን ህገ ወጥ ተግባራት ሳትታክት በማጋለጧ ነው፡፡ ኤልሳቤት የተማረችውን የህግ ትምህርት መሠረት አድርጋ ከሐረሪ ህገ መንግስት ጀምሮ ያለውን የህግ ክፍተትና ስርዓታዊ የብሔር አድልዎ ሳትታክት በዩቲብ ቻናሏ ላይ በመረጃ አስደግፋ አጋልጣለች፡፡‹የክልሉ ህገ መንግስት በመግቢያው ላይ የክልሉ ዋና ተጠቃሚ ህዝቦች ሐረሪና ኦሮሞ ናቸው በማላት ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን እንደሌሉና እንዳልተፈጠሩ የሚቆጠር ነው› ትላለች፡፡‹ የክልሉ ምክር ቤት አደረጃጃትም ሌሎችን ያገለለና በሐረሪዎች ብቻ የተያዘ የሌላ ብሄር ተወላጅ የሆነና በክልሉ የሚኖር ሰው የማይገባበት ነው› በማለት የአፖርታድ ስርዓት ሩቅ ሳይኬድ እዚሁ በሀገራችን ውስጥ ህገ መንግስታዊ እውቅና አግኝቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ትላለች፡፡ በሐረሪ ክልል ስለሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች ምን አይነት መንግስታዊ አፖርታይድ እንዳለ ያጋለጠችው ኤልሳቤት በተለይም ነፍጠኛ የሚል ስያሜ በህገ መንግስታቸው ላይ ያሰፈሩትን ብሔር ወደ ክልሉ ሲሄዱ በቃላት ሊደልሉት እንደሚሞክሩ የሐረሪ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦርዲን በድሪ በቅርቡ ወደ አማራ ክልል ባቀኑበት ወቅት የተናገሩትን በመጥቀስ ነው፡፡‹ ስለ አማራ የሚወራዉ ሐሰተኛ ትርክት ሊቆም ይገባል” ያሉት አቶ ኦርዲን ክልላቸው የሚመራበትን አስደናቂዉ የሐረሪ ክልል ህገመንግስት መግቢያ ላይ ያለውን አንድን ህዝብ እንዳለ የሚፈርጅ ሐሰተኛ ትርክት? አላዩት ይሆን ሚስተር ፕሬዚዳንት ? › ስትል ትጠይቃለች፡፡

‹ሙስና በሐረሪ ክልል ተንሰራፍቷ› የሚለው ቃል አይገልፀውም የምትለው ኤልሳቤት ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማክበሪያ በሚል በጥድፊያ የተሰራው የሐረር አባድር ስታዲዮም 1. 5 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ሲነገር ቢያንስ አሳማኝ ግንባታ እንኳ ሳይደረግ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ የክልሉ አጠቃላይ በጀት 3 ቢሊየን እንኳ የማይሞላ መሆኑ ነው፡፡ ኤልሳቤጥ በክልሉ መንግስትና ሹማምንት ጥርስ የተነከሰባት ያደራጀችው ሀይል ኖሮ አልያም ጦር አስተዳደሩ ላይ ስለሰበቀች አይደለም፡፡ ‹ስለ ሐረሪ ክልል የመንግስት አወቃቀር፤ ስለአፓርታይድ ስርአት እና ስለ ህገመንግስቱ ችግር እኔ ስፅፈዉ… የሐረሪ ብሄረሰብ ጭፍን ጥላቻ አለሽ እባላለሁ› ትላለች፡፡ ‹ እኔ ግን በህዝቡ ላይ ምንም አይነት ጥላቻም ሆነ ቅሬታ የለኝም፤ሐረር ላይ የተንሰራፋዉን የአፓርታይድ ስርአቱን ያየ ሌላ ሰው ሊናገረው ያልቻለውን ነገር በግልጽ በአደባባይ ስለተናገርኩት ነው፡፡ የሐረሪ ጉባኤ በሀረር ከፍተኛዉን ስልጣን ይዟል። ሐረር ተወልዶ ያደገ አማራ፤ ኦሮሞ፤ ሶማሌ፤ ትግሬ፤ አርጎባ፤ ጉራጌ፤ ወዘተ ለእዚህ ጉባኤ የመምረጥም የመመረጥም መብት የለዉም።በመላዉ ኢትዮጵያ የሚኖረዉ አደሬ ግን ከሌላ ከተማ መጥቶ ይመርጣል፤ ይመረጣል።›በማላት ብዙም የውይይት አጀንዳ ያልሆነውን የክልሉን አሰራር ትተቻለች፡፡ “ብዙሃኑ ያስተዳድራል አናሳዉ መብቱ ይጠበቃል”የሚለው የፌደራሉ ህግ መንግስት”አናሳዉ ያስተዳድራል አናሳዉ መብቱ ይጠበቃል”ከሚለው የሐረሪ ህገ መንግስት ጋር ግልፅ ተቃርኖ እንዳለው የምትሞግተው ኤልሳቤት 27አመት በሐረሪ አንድ ፓርቲ ብቻ ያለ በመሆኑ በኢትዮጵያ ዉስጥ አንዱን ኢትዮጵያዊ አሳንሶ አንዱን የተለየ መብት የሚሰጥ ህግ በዜጎች መካከል ልዩነት ፈጥሯል › ስትል ትከራከራለች፡፡ ይህን ግልጽ መድሎ ዩኔስኮ ቢመለከት ኖሮ ከጀጎል ግንብ ይልቅ ይህንን ህገ መንግስት ነበር በዓለም ቅርስነት የሚመዘግበው› ስትልም ታክላለች፡፡ ኤልሳቤት ምናልባትም ይህ ሙግቷ ሳይሆን አይቀርም በክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ዘንድ ጥርስ ያስነከሰባትና ያለምንም ክስ ከአንድ ወር በላይ በእስር ቤት እንድትማቅቅ ያደረጋት፡፡

በሐረር ያለው ማህበራዊ መፈናቅሎችን መለስ ብሎ ዜጎችን የሚያቋቁምና የሚረዳ አመራር እንደሌለ ማሳያ አድርጋ ከምታቀርባቸው ማስረጃዎቿ መሀከል አንዱ ይህን ይመስላል፤‹ ሐረር ከገንዴ ቤታቸዉ ተቃጥሎ የተፈናቀሉ ከ15 አባወራዎች በላይ ሐረር ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ዉስጥ መኖር ከጀመሩ ሶስተኛ አመታቸዉ መጣ… እግዚአብሄር ያሳያችሁ ሽንት ቤት ፈንድቶ በሚጠጡት ዉሃ ስር ያልፋል፤ በሚተኙበት በረንዳ ስር ያልፋል…እዛዉ ጋር ይተኛሉ፤ እዛዉ ጋር ምግብ ያበስላሉ…የትም ያልታየ የሰዉ ልጅ ጭካኔ… ለዚህ የበቁት በ2010አንድ ወጣት ተገድሎ ነበር፤ ገዳዩ አብሮ አደግ ጓደኛዉ ነበር።ለገዳዩ ገንዘብ ተሰጥቶት በተቀመጠበት በዱላ መትቶ ገደለዉ። በዚህ የተቆጡ የአከባቢዉ ሰዎች የገዳይ ቤተሰቦችንን እና በከባቢዉ የሚገኙ ቤቶችን በአንድነት አቃጠሉ። እነዚህም ሙሉ በሙሉ ቤትና ንብረታቸዉ በመዉደሙ ወደ ቤታቸዉ መመለስ ስላልቻሉ በሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ዉስጥ ለግዜዉ ተብሎ እንዲቆዩ ቢደረግም የክልሉ መንግስት ረስቷቸዉ ይሄዉ እንደምታዩት እንዲህ ነዉ የሚኖሩት› በማለት እንደ ሰብዓዊ መብት ጠበቃነቷን በፎቶ አስደግፋ በማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ አውጥታለች፡፡ በሐረር ከሚያንገፈግፈዉ ነገር አንዱ የከተማ ልማት ህግ ነው› የምትለው ኤልሳቤት ‹እኛ የቀበሌ ቤት ቢፈርስብን ማቃናት እንጂ እንደ አዲስ መገንባት አንችልም..እነሱሳ?እነሱማ የቀበሌ ቤት አፍርሰዉ የግል ይዞታ ማረጋገጫ አዉጥተዉበት ህንፃ ይሰሩበታል..ነዋሪዉ በአመት ለዘመን መለወጫ እንኳን ቀለም ለመቀባት ደንብ አስከባሪዎች አዩኝ አላዩኝ ብሎ እየተሳቀቀ ነዉ የሚቀባዉ…እኛ የፈረሰ አጥራችንን በቆርቆሮ ብቻ ማጠር ሲፈቀድልን እነሱ በግንብ ያጥራሉ ….የግላቸዉም ያደርጉታል…እና ይሄ እኛና እነሱ /ኔቲቮቹ እኩል የምንሆነዉ መቼ ነዉ? ፍትህ ለሐረር ህዝብ የምንለዉ ለዚህ ነዉ!ነ› ትላለች፡፡

በ1997 በቲቲአይ መምህርነት ተምረዉ ሙልጭ ብለዉ ተሰደው ከሐረር ስለወጡ ባይተዋር የሐረር ልጆች አመከራና ችግር የምታጋልጠው ኤልሳቤት ‹እነዚህ የ1990ዎቹ የሐረር ልጆች ያልተበተኑበት የኢትዮጵያ ምድር የለም።አሉ። አሁን ሐረር እንደድሮዉ ፊቷን እንዳዞረችባቸዉ ናት። እትብታቸዉ የተቀበረባት ተወልደዉ ያደጉባት ከተማ ከልጅነት እስከ እዉቀት አንገታቸዉን አስደፍታቸዋለች።› ትላለች፡፡ የክልልን የሚያስተዳድረው ሐብሊ የተባለው የብልፅግና ፖርቲ አባላት ወጣቱን ስራ የሚፈጥርለት አጥቶ በየመንገዱና በየጆተኒ ቤት ጫት ሲቅም የመዋሉ ጉዳይ እንደማያሳስበው የምትናገረው ኤልሳቤት ‹ከህዝቡ የሚሰበሰበሰው ግብር የታለ ??የክልሉ በጀትስ?? ሐረር ወጣት ማዕከል እንኳን በሌለበት ጫት ቤትና ጥናት ቤቶች በሞሉበት ከተማ ስፖርትን ማበረታታትና ወጣቱን ከሱስ ማለቀቅ ሲገባዉ ራሱም ሱስ ዉስጥ የተዘፈቀ የመንግስት አመራርና ሰራተኛ በምን መልኩ ወጣቱን ችግር ይፈታል?› ስትል ትጠይቃለች፡፡ በቅርቡ በሐረር ከተማ የተነሳው ግጭትን አስታከው ብሔርተኞች የራስ መኮንን ሐውልትን በማፍረሳቸው ተቃውሞዋን የገለፀችው ኤልሳቤት አሳዛኙ ነገር የሐሰት ትርክት ሲጋቱ በከረሙ ወጣቶች ሀውልቱ ሲፈርስ የከተማው ፖሊስ ዝም ብሎ ማየቱ ሳይሆን ሐውልቱን በተሻለ ሁኔታ መልሶ ለማቆም የተዋቀረው ኮሚቴ መግለጫ ሲሰጥ የክልሉ ባለስጣናት መቃወማቸው ነው ስትል በቁጭት ትናገራለች፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe