‹የዓመቱ ምርጦች› ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገብረመድኀን

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በመላው ዓለም የጤና ስጋት የሆነው የኮረና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባቱ ከታወቀበት ዕለት አንስቶ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር  ሊያ ታደሰ እረፍት አልነበራቸውም፤  ዜጎች በቫይረሱ እንዳይያዙና እንዳያልቁ የሚያሳስቡ መረጃዎችን በየዕለቱ ወደ መገናኛ ብዙሃን በማቅረብ ትጋታቸውን አሳይተዋል፡፡ አውሮፖውያንና አሜሪካውያን ከያዝነው ዓመት ጀምሮ በኮቪድ ምክንያት በቀን ሶስት ሺ እና አራት ሺ ዜጎቻቸውን ሲቀብሩ በኢትዮጵያ ግን በዓመቱ ውስጥ የሞቱ ሰዎችቁጥር  ከ4500 በታች ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ በሚመሩት ሚኒስትር ትጋትና ባስተባበሯቸው የጤና ባለሙያዎች መስዋዕትነት ጭምር ስለመሆኑ ብዙዎች ያምናሉ፡፡

ሀገራትን የወረርሽኙን መስፋፋት ለመመከት ከወሰዷቸው እርምጃዎች መሀከል ቀዳሚው የእንቅስቃሴ ገደብ ወይም / lockdown/ ሲሆን ሀገራችንም ይህንኑ የምዕራባውያን መንገድ እንድትከተል ያልተቋረጠ ጉትጎታ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ዶ/ር ሊያና የስራ መሪዎቻቸው ግን በሎክ ዳውን ምክንያት በቋፍ ላይ ያለው የሀገራችን ኢኮኖሚ እንዳይጎዳ የኮቪድ ፕሮቶኮልን በማውጣት እንዲተገበር አድርገዋል፡፡

ማናቸውም ህዝባዊ ዝግጅቶችና ማህበራዊ ፕሮግራች ከ50 ሰዎች ባልበለጠ እንዲካሄዱ በማድረግ የወረርሽኙን የጥፋት ደረጃ ለመገደብ ተሞክሯል፡፡ ከምርጫና ከትምህርት ቤት መከፈት ጋር ተያይዞ ያለውን ስጋትም ጥንቃቄ በተሞላበት ውሳኔ ለማስኬድ ተችሏ፡፡አንዳንዶች በአውሮፖና በአሜሪካ የተከሰተውን ወረርሽን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያም ከዚህ የከፋ እልቂት እንደሚከሰት በማህበራዊ ድረ ገፅ ከመፃፍ አልፈው እንደ ሞት ነጋዴ ‹በጥቂት ቀናት ውስጥ በኮቪድ የተነሳ 2 ሚሊዮን ሰዎች ያሞታሉ› የሚል መርዶ አይሉት ትንታኔ ሲሰጡ እነ ዶ/ር ሊያ ግን ህብረተሰቡ ስለ ቫይረስ የመተላለፊያ መንገዶች እንዲያውቅና ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ ያስተምሩ ነበር፡፡

በየዕለቱ ጠዋት ከማለዳው 12 ሰኣት ጀምሮ ከሞቀ አልጋቸው ላይ ባለቤታቸውንና ሶስት ልጆቻቸውን ጥለው የኮቮድ በሽታ መከላከያ ግብረ ሃይልን  ለመምራት በስራ ገበታቸው ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሊያ ከስጋት ይልቅ ተስፋን፤ ከሞት ይልቅ ህይወትን፤ ከህመም ይልቅ ፈውስን የያዙ  መልዕክቶች አንግበው የጤና ባለሙያዎችን አትግተዋ፤ ህሙማንና ቤተሰቦቻቻውን አበረታተዋል፡፡

ካለፈው ዓመት ተሻግሮ የስጋት ምንጭ መሆኑን ያላቆመው ኮቪድ በተለይ እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት መጀመሪያ ላይ ሀገሪቱ በጉጉት የምትጠብቅው ምርጫ ‹ ይካሄዳል› ወይስ ‹አይካሄድም› በሚል ትልቅ የውዝግብ ርዕስ ነበር፤ ጉዳዩን በተመለከተ የኮቪድን ሁኔታ ገምግሞ የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ ሃላፊነት የተጣላባው የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ አስፈላጊ የሆኑ የኮቪድ ፕሮቶኮል የጥንቃቄ እርምጃዎችን  በማዘጋጀት ‹ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል› በማለት ነው ሂደቱን እንዲጀመር ያደረጉት፡፡

ተቋርጦ የቀረው የመማር ማስተማር ሂደም የተማሪዎችን ቁጥር በመቀነስና ፈረቃ በማበጀት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እንዲችሉ አድርገዋል፡፡በተለይ ከተማሪዎች የጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ያለ መላክ ፍላጎት  ታይቶባቸው የነበረ ቢሆንም የመማር ማስተማር ሂደቱ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ያለምንም የጤና ችግር ዓመቱ ተጠናቋል ፤

ኮቪድ በሌላ ዓለም በታየው መጠን የብዙዎችን ህይወት በሀገራችን ሊቀጥፍ ያልቻለው በጤና ባለሙያዎች ሃላፊነት በተሞላበት ክትትል እንደሆነ ይታመናል፡፡ በጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የሚመሩት የኢትዮጵያ የጤና ሙያተኞች ራሳቸውን ህይወት አደጋ ላይ እየጣሉ ጭምር የኮቪድ  ህመምተኞችን ታድገዋል፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የጤና ባለሙያዎችም ህመምተኞቻቸውን ሲታደጉ በኮቪድ ተይዘው ህይወታቸው አልፏል፡፡

የህክምና ባለሙያዎችን መስዋእትነት ትልቅ ቦታ የሰጠው ጤና ሚኒስቴርም ፤‹ኢትዮጵያ ታመሰግናለች!› የሚል መርሃ ግብር ከሃምሌ 11-17, 2013 ዓ.ም – ድረስ ለአገር አቀፍ የጤና ባለሞያዎች እና ክብካቤ ሰራተኞች የምስጋና ፕሮግራም በማዘጋጀት ሚኒስቴሩ ባለሙያዎቹን እንዲያመሰግን ዶ/ር ሊያ የአንበሳውን ሚና ተጫውተዋል፡፡

ዘወትር ‹ምክንያት አልሆንም› የሚል መርሃቸውን ይዘው አደባባይ የሚወጡት ዶ/ር ሊያ በየጊዜው በህብረተሰቡ ላይ የሚታየው ቸልተኝነት ያሳስባቸዋል፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድርግ ብቻ 80 ከመቶ የኪቪድ ወረርሽ መከተላካል እንደሚቻል በየመድረኩ ወጥተው የሚናገሩት ሚኒስትሯ የቅርብ ጊዜው ጥናት የውጤት የሚያሳየው ግን መዘናጋት ቀላል በማይባል ደረጃ በህብረተሰቡ ውስጥ እንደተንሰራፋ ያሳያል፡፡ ከከተሞች ውጭ የገጠር የኮቪድ 19 ጥንቃቄ ደግሞ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት፤ በዶ/ር ሊያና የሚመራው  በህብረተሰብ ጤና ኢንስትት ስር የተቀዋቀው ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳዳር ቅመራና ትንተና ማዕከል ምልከታው ባደረገባቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የማስክ አጠቃቀም 75 በመቶ ሲሆን፣ የእጅ ንፅህና አጠቃቀም ደግሞ በ18 በመቶ ብቻ ተግባራዊ ነው፡፡ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ትምህርት ቤቶች ያለው የማስክ አጠቃቀም ከ35 በመቶ ከፍ ያላለ ሲሆን፣ የእጅ ንፅህና አጠባበቅ ከ4 በመቶ በታች መሆኑን ተሰምሮበታል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በ15 ከተሞች ነዋሪዎች ላይ እና በ48 ትምህርት ቤቶች ለተከታታይ 38 ሳምንታት የተደረገ የክትትል ጥናት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች በአግባቡ እንደማይተገበሩ አሳይቷል፡፡የእጅ ንፅህና አጠባበቅ ከ10 በመቶ በታች፣ የአካላዊ መራራቅ ትግበራ ከ25 በመቶ በታች፣ እንዲሁም የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ አጠቃቀም 58 በመቶ መሆኑን በክትትል ጥናቱ መታየቱ ተነግሯል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሀገራችን የወረሽኙ ምጣኔ በአንፃራዊ ሁኔታ ከነበረበት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ካለፉት 3 ሳምንታት ጀምሮ ግን በሳምንታዊ ሪፖርት በበሽታው የመያዝ መጠን በ 4 እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን፣ በጽኑ የሚታመሙ ሰዎች በ2.5 እጥፍ ማደጉንና ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖች ደግሞ በ2.8 እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱን ይህም አሳሳቢ እንደሆነ የጤና ሚኒስትሯ  አልሸሸጉም፡፡

በቫይረሱ የሚያዙ፣ ሕይወታቸውን የሚያጡና የፅኑ ህሙማን ብዛት እያሻቀበ በመምጣቱ፣ እንደ ኦከስጅን ያሉ የህክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማግኘት በዶ/ር ሊያ የሚመራው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ራስ ምታት ሆኖበታል፡፡ በመሆኑም ለዚህ አቅምን ለሚፈታትን ችግር  ቀዳሚው መፍትሔ ከኮቪድ 19 ወረርሽን ራስን ለመከላከል በሚኒስቴሩ የወጣውን የጥንቃቄ መመሪያዎች መተግበር ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሯ  ከመናገር ቦዝነው አያውቁም፡፡

ሚኒስትሯ በአንድ በኩል ወርሽኙ የሚያደርሰውን ጉዳት እየተከላከሉ በሌላ በኩል ደግሞ  በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ለማዳረስ ክትባቱን ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ተቋማት ለማግኘት ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል፡፡  እስካሁን ከትባቱን ያገኙት ዜጎች ብዛት ከ2 በመቶ የማይበልጥ ቢሆንም ከአሜሪካ መንግስት አንድ ጊዜ ብቻ የሚወሰደውን 1.6 ሚሊዮን ዶዝ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት በቅርቡ ሚኒስትሯ ባደረጉት ጥረት ወደ ሀገራችን ሊገባ ችሏል፡፡ ከእንግሊዝ መንግስትም ለኢትዮጵያ የተሰጠውን 499,200 ዶዝ አስታራዜኒካ የኮቪድ -19 ክትባቶችን ዶ/ር ሊያ ተረክበው ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀዳሚነት እንዲከተቡ አድርገዋል፡፡ ከቻይና መንግስትም ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የኮቪድ ክትባቶችን ማግኘት ችለዋል፡፡

ሚኒስትሯ በኮቮድ ሳቢያ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ከመመከት በተጨማሪ በሌሎች የጤና ዘርፎች ላይ መደረግ ያለባቸውን የንቅናቄ ስራዎች በማስጀመርና ግንባር ቀደም መሪ በመሆን የሀገራችን ጤና አገልግሎቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡ እንደ አብነትም  “ኤችአይቪ በደማቸው በሚገኝባቸው ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርስባቸውን ማግለል እና አድልዎ ለመቀነስ የሃይማኖት መሪዎች እና ተቋማት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው በማመን ከሀይማኖት መሪዎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡ በመድሃኒት አቅርቦትና ስርጭት ዘርፍ ያለውን ክፍተት ለመሙላትም ‹አቀርባለሁ፣ አሻሽላለሁ፣ እጠየቃለሁ ›በሚል መሪ ቃል /I supply/ በሚል የተሰየመው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የአስር አመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ማስተግበሪያ ፕሮግራም አስተዋውቀዋል፡፡ ጤና ተቋማቶች የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የመከላከል ስራውን ራሱን የቻለ ቦታ አዘጋጅተው ከመደበኛ ጤና አገልግሎቱ ጋር አጣምረው እንዲሰጡ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረትም የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር፣ የአይን፣ የአዕምሮና የቆዳ ምርመራና ህክምና መስጫ ማዕከላት ትኩረት አግኝተው እንዲተገበሩ የሚኒስትሯ ክትትል ከፍተኛ ነበር፡፡

የዛሬ 44 ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የመጀመሪያ ዲግሪያውን በፅንስና የማህፀን ህክምና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  እንዲሁም ሁለተኛና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በህብረተሰብ ጤና አጠባባቅ ትምህርት ከጂማ የዩኒቨርሲቲ ተአግኝተዋል፡፡ የጤና ባለሙያ ከሆኑ ወላጆች የተገኙት ዶ/ር ሊያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምርታቸውን በመስካዬ ኀዙናል፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ  በእቴጌ መነን በከፍተኛ ማዕረግ ማጠናቀቃቸው የትምርትና የስራ ማስረጃቸው ያሳያል፡፡

ዶ/ር ሊያ የጤና ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የአስተዳደር ችሎታ እንዳላቸው ያሳዩት በ1999ዓ.ም በአዲስ አበባ በተዘጋጀ የጤና ጉባኤ ላይ ባሳዩት ብቃት እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡ ጉባኤው የኢትዮጵያ የፅንስና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር ያዘጋጀው ጉባኤ ሲሆን በዚህ ስብሰባ ላይ ዶ/ር ሊያ አንድ ጥናታዊ ፅሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ ይህ መድረክ ዶ/ር ሊያን ወደ አስተዳደር ስራ እንዲመጡ በር ከፈተላቸው፡፡ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ከመመደባቸው በፊት በተለያዩ የሀላፊነት ቦታዎች ላይ ሰርተዋል፤ በጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ የጤና ፕሮግራም የጤና ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂስት ሆነው አገልግለዋል፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲና በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የእናቶችና ህጻናት ጤና እንክብካቤ ሃላፊና የስነ ተዋልዶ ጤና ስልጠና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል፡፡

በዚህ ሀላፊነት ሲሰሩም በሀገሪቱ ያሉትን የማህፀን ሀኪሞች ቁጥር ለመጨመር የስልጠና መርሃ ግብሮችን በመጀመር የሀኪሞችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ ችለዋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታልም አምስት ያህል አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች እንዲከፈቱ ከማድረጋቸው በተጨማሪ የድንተገኛ ህሙማን ማስተናገጃና የእናቶችና የህፃናት የጤና ማዕከልን አቋቁመዋል፡፡ በህክምና ፋክሊቲውም ከ15 ከመቶ በታች የነበረውን የሴት ተማሪዎች ቅበላ ከ20 እስከ 30 ከመቶ እንዲጨምር አድርገዋል፡፡ የአዳጊ ክልል ሴት ተማሪዎች ቅበላም ከሌሎች በተለየ መንገድ በማሳደግ የክልሎቹን የጤና አገልግሎት አሳድገዋል፡፡

ይህንኑ ትጋታቸውን መሠረት በማድረግ ቁም ነገር መፅሔት ዶ/ር ሊያ ታደሰን  የ2013 ዓ.ም ምርጥ የስራ መሪ ብላቸዋለች፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe