‹የዓመቱ ምርጦች› ዶ/ር ሰላሜነሽ ጽጌ

የዓመታት በፊት የሆነ እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡ ግለሰቡ የካንሰር ህመምተኛ ናቸው፡፡  ለትራንስፖርት አስቸጋሪ ከሆነ የባሌ ገጠራማ መንደር ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የመጡት ከህመማቸው የመፈወስ ተስፋ ሰንቀው ነው፡፡ግለሰቡ የያዙት ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ ህክምናቸውን በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ያልቃል፡፡የሚበሉት አጥተው የሰው እጅ ማየት የየዕለት ፈተናቸው ሆነ፤ማደሪያ አጥተውም በሆስፒታሉ ኩሪደር ሲሚንቶ ላይ  ማደር ይጀምራሉ፡፡

‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ› ሀኪም የኬሞቴራፒ ህክምና እንዲጀምሩ ቢያዝም የት ሆነው እየተመላለሱ ህክምና ያድርጉ?  የምግብ ብቻ ሳይሆን የመጠለያ ችግራቸውን ያዩ የሆስፒታሉ ሰራተኞች ማረፊያ ሲያገኙ  እንዲመጡ እስከዛው ተደውሎ እንደሚጠሩ በማግባባት  በተዋጣ ገንዘብ ወደ መጡበት የትውልድ መንደራቸው  ይሸኛሉ፡፡

ከአንድ ዓመት ከስምንት ወራት በኋላ ግን ሆስፒታሉ ከእሳቸው በፊት ያሉትን ህመምተኞች አክሞ መጥተው ህክምናውን እንዲጀምሩ ለመንገር ስልክ የደወለችው ነርስ በእዚያኛው የስልክ ጫፍ  የሰማችውን ማመን አልቻለችም፡፡ ህምተኛው ወደ ትውልድ መንደራቸው በተመለሱ ወር እንኳ ሳይሆናቸው ነበር ከዚህ ዓለም በሞት ተተለዩት፡፡

የዚህ አይነት ታሪክ በኢትዮጵያ ሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች ውስጥ እንደ ዘበት የሚተረክ ታሪክ ነው፡፡ አንዳች የመዳን ተስፋ ብቻ ይዘው ከብቶቻቸውን ሸጠው ከገጠር የሚመጡ ህመምተኞች አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ የያዙት ጥሪት አይደለም ለህክምና ለቀለብ ማብቃቃት እያቃታቸው እጃቸውን ለልመና ሲዘረጉ መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

<‹የዓመቱ ምርጦች› ቀዳማይ እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው>

ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው የሚያርፉበት ቦታ ያጡና ህክምናቸውን መከታተል ያልቻሉ ህሙማን በየመንግስት ሆስፒታሉ ኮሪደርና ጥጋጥግ ላይ ከእነ ህመማቸው ተኝተው ሲያቃስቱ መመልከት ልብ ይሰብራል፡፡ ይህኑን ችግር ተማሪ በነበረችብት ወቅት እዛው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ትመለከት የነበረችው የ29 ዓመቷ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር ሰላሜነሽ ጽጌ   ጓደኞቿ በማስተባበር ከሚደርሳት ደሞዝ ላይ የተወሰነ ገንዘብ በማዋጣት   በየኮሪደሩ የወደቁ ህሙማንን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የጀመሩት የዛሬ 7 ዓመት ነበር፡፡

ውሎ ሲያደር ይህ የበጎ አድራጎት ተግባር የብዙዎችን ትኩረት መሳብና ድጋፍ ማሰባሰብ  ሲጀምሩ  በሳምንት ለአንድ ቀን ምግብ ማብላታቸውን ወደ ሁለት ቀናትና ወደ ሶስት ቀናት ማሳደግ ቻሉ፡፡ ዶ/ር ሰላሜነሽ ትምህርቷን አጠናቃ ስትመረቅም ይህንን የበጎ አድርጎት ተቋም ከሌሎች ልበ ቅን  ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባባር ‹ጎጆ አቅም የለሽ የህሙማን ማረፊያ ማዕከልን› መሰረቱ፡፡

ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ማረፊያ የሌላቸው ህሙማንን ሊያሳደር የሚችል ህንፃ የማስገንባት ሀሳብ ከሌሎች የሆስፒታሉ ሀኪሞች ጋር መማከር የጀመሩት ወዲያውኑ ነው፡፡

ይህን የበጎ አድራጎት ስራ የደገፉ ሁለት ተቋማት ማለትም  የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ እና የቃሊቲ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ማምረቻ ፋብሪካ በጋራ ህንፃውን በአጭር ጊዜ ገንብተው አስረከቡ፡፡ህንፃው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል  ግቢ አቅራቢያ የሚገኘው ተክለሃማኖት ጤና ጣቢያ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገነባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት  አቅም የለሽ የህሙማን ማረፊያ ማዕከል ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

በዶ/ር ሰላሜነሽና በጥቂት የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሃኪሞች ሃሳብ ጠንሳሽነት ታህሳስ 2007 ዓ.ም የተመሰረተው ይህን  ተቋም ዶ/ር ሰላሜነሽ በዋና ዳይሬክተርነት እየመራች ሲሆን  ህሙማን ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሪፈራል ምክንያት ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ በኋላ ህክምናቸውን ለመከታተል ለመኝታና ለምግብ የሚከፍሉት ገንዘብ የሌላቸው ህሙማን መጠለያ በመስጠትና የምግብ አገልግሎት በማቅረብ ወገኖችን እያገዘ ነው፡፡

የጎጆ ህሙማን ማረፊያ ማዕከል በአሁኑ ወቅት የምግብ፣ የሻወር፣ የመኝታና አልባሳት አገልግሎትን ይሰጣል፡፡ ማዕከሉ 52 አልጋዎች ያሉት ሲሆን በቀን አስታማሚዎችን ጨምሮ ለ104 ሰዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ወደ ማዕከሉ የሚገቡ ህሙማን በአማካኝ እስከ ሁለት ሳምንት የቆይታ ጊዜ ያላቸው ሲሆን አገልግሎታቸውን የጨረሱ እና የሪፈራል ጊዜያቸው ከሶስት ሳምንት በላይ የሆኑትን ደግሞ የትራንስፖርት ወጪ ተሸፍኖላቸው ወደ መጡበት አካባቢ እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡

የተለያዩ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሚያደርጉት ልገሳ በሳምንት ለአራት ቀናት ማለትም ሰኞ፤ ረብዕ፤ ሐሙስና አርብ የምግብ አገልግሎት ከመጠለያ ጋር አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ጎጆ የህሙማን ማረፊያ በአቅም ችግርና በመጠጊያ እጦት ሳቢያ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይታይ የነበረውን ልብ ሰባሪ ክስተት በተወሰነ ደረጃ መቅረፍ ቢቻልም ከመላ ሀገሪቱ ተመሳሳይ ህክምና ፍለጋ መጥተው አሁንም በየኮርደሩ ተኝተው የሚያቃስቱ ህሙማን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡

<‹የዓመቱ ምርጦች› ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገብረመድኀን>

‹ ከአገልግሎት ፈላጊዎች አኳያ ሲታይ አሁን አገልግሎት የሚሰጥበት ቦታ በቂ ባለመሆኑ ግለሰቦች፣ድርጅቶችና የሚመለከታቸው አካላት ማዕከሉን እንዲጎበኙና ድጋፍ እንዲያደርጉ › ስትል የማዕከሉ አስተባባሪ ዶ/ር ሰላሜነሽ ጥሪዋን ዘወትር ታቀርባለች፡፡

ብዙም ባይሆኑ ይህኑን ጥሪ የተቀበሉና የህሙማንን ፈውስ የሚናፍቁ የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማትም በየጊዜው ወደ ማዕከሉ በማምራት የበኩላቸውን የገንዘብ፤ የአይነትና የጉልበት ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡አንዳንድ ሰዎች ከቤሰቦቻቸው ጋር በመማከር እንደ ተስካርና ሰደቃ አይነት ማህበራዊና መንፈሳዊ ግዴታቸውን  ለማከናወን ሊያወጡት የነበረውን ገንዘብ ምግብ በማዘጋጀት ህሙማንን ሲጠይቁ ታይተዋል፡፡

እንደ አብነትም በጋሻው የሺጥላ እና ኤደን በላይ የተባሉ የማረፊያው ቤተሰብ ያለፈውን የኪዳነምህረትን ዝክርን በማስመልከት ህሙማኑን በማሠብ የህሙማኑን ማረፊያ በመጎብኝት፣ ህሙማኑን በመመገብ እና በማፅናናት አሳልፈዋል። ፍቅርተ ማሪያምም  የተባሉ ግለሰብም ‹አስራት በኩራት›  በማለት ህሙማኑን በመጎብኝት ምግብ በመመገብ ለፅዳትና ለምግብ ግባትነት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በማምጣት ህሙማኑን ጠይቀዋል፡፡  ዶክተር ኢብራሂም የተባሉ የጎጆ ቤተሰብም በሙስሊም በዓል ሁሌም እንደሚያደርጉት፤የኢድ አል አድሃ የአረፋን በዓል ምክንያት በማድረግ የማረፊያው ተጠቃሚ ህሙማን ምግብ አብልተዋል ይላል የማዕከሉ ድረ ገፅ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህፃናት ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆነችው ዶ/ር ሰላሜነሽ በህፃናት ህክምና በተለይም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ህጻናትን በማከምና በማማከር ስመ ጥር ከሆኑ ሀኪሞች መሀከል አንዷ ናት ፡፡ከህክምናና ከማስተማር ስራዋ ጎን ለጎንም የምስራቅ አፍሪካ አካል ጉዳተኛ ህፃናት አካዳሚ የኮሚየኒኬሽንና ፕሮሞሽን ሀላፊ ሆና ትሰራለች ፡፡የዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኛ ህፃናት የትምህርትና ስልጠና ትብብር የአፍሪካ ተጠሪ ሆናም ትሰራለች፡፡ ከዚህ ሌላም ዶ/ር ሰላሜነሽ በአካል ጉዳተኛ ህጻናት ስነ ባህሪን በማጥናት በዘርፉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ የአካል ጉዳተኛ ህጻናት ስፔሻሊስት ሀኪም ነች፡፡

ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህም ለዚህ የአካ ጉዳተኛ ህፃናት ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል በጥቁር አንባሳ ሆስፒታል ውስጥ በማቋቋም አካል ጉዳተኛ ህጻናትን በተለየ መልኩ ህክምና እየሰጠች ትገኛለች፡፡ ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጋርም ግንኙነት በመፍጠር አካል ጉዳት ባለባቸው ህጻናት ላይ የሚከሰተውን ስውር አድልዎና መገለል ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ትሰጣለች፡፡

ላለፉት ሰባት ዓመታት አቅም የሌላቸውንና በፅኑ ህመም የተያዙ ህሙማን የምገባና ጊዜያዊ መጠለያ የአገልግሎት የሰጠውን ማዕከል የመራችው ዶ/ር ሰላሜነሽ እስከ አሁን ድረስ ከ80 ሺ በላይ የሚሆኑ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መጥተው ማረፊያ ያጡና የትራንስፖርት ወጪ የቸገራቸው ወገኖችን በማገዝ ህክምናቸውን ጨርሰው ወደየመጡበት አካባቢ እንዲመለሱ አድርጋለች፡፡

ይህ የበጎ አድራጎት ስራዋ ከሀገር አልፎ በመላው ኣለም የተሰማው ዶ/ር ሰላሜነሽ በቅርቡ በአሜሪካ በተካሄደው  የወጣት አፍሪካውያን የወደፊቱ መሪዎች ፕሮግራም ማንዴላ ፊሎሽፕ ‹ Mandela Washington fellow ›ተመርጣ ወደ ዋሽንግተን በማምራት ልምዷን ለሌሎች አፍሪካውያን ወጣቶች አጋርታለች፡፡ ባለፈው ዓመት መግቢያ ላይም   መጠለያ ለሌላቸው ህሙማን ባቋቋመችው ማእከል አማካይኝነት የሰጠችውን አገልግሎት በማስመልከት‹ Ethiopian Woman of Excellence › የተሰኘ ሽልማትና እውቅን አግኘታለች፡፡

ይህንኑ ትጋቷን መሠረት በማድረግ ቁም ነገር መፅሔት ዶ/ር ሰላሜነሽን  የ2013 ዓ.ም ምርጥ የበጎ አድራጎት ሰው ብላታለች፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe