በመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንጀምር፤ እየሱስ ክርስቶስ የአምስት ገበያ ህዝብ አስከትሎ እያስተማረ ወደ እየሩሳሌም ሲያመራ ከውልደቱ ጀምሮ አይነ ስውር የነበረ አንድ አዛውንት የእኔ ብጤ ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር፤ ክርስቶስ በእዚያ በኩል ሲያልፍ በሚከተለው ህዝብ ብዛት ያለ ወትሮው ግርግር የተሰማው የእኔ ብጤ እንደምንም ብሎ በአጠገቡ የሚያልፈን አንድ ሰው ልብሱን ጨምድዶ ‹ምንድነው እዚህ አካባቢ እየሆነ ያለው ?› ሲል ይጠይቀዋል፤
ክርስቶስን እየተከተለ ያለው ሰው ልብሱን ከሽማግሌው እየመነጨቀ ‹የናዝሬቱ እየሱስ በእዚሀ በኩል እያለፈ ነው!› ይለዋል፤ ይህን ግዜ በክርስቶስ ላይ ፅኑ እምነት ያለው የእኔ ብጤ እየጮኸ ‹ እየሱስ! እየሱስ! የእግዚአብሐር ልጅ! አድነኝ!› እያለ ክርስቶስ ወደ ሄደበት አቅጣጫ ቦታ ሲሄድ ክርስቶስ ድምፁን ሰምቶ ቆም ይልና ‹አምጡት ወዲህ!› ይላል፤
ከደቀመዛሙርቱ መሀከል ሁለቱ የእኔ ብጤውን አይነ ስውር ግራና ቀኝ ደግፈው ይዘው ክርስቶስ ፊት ያቀርቡታል፤
‹ምን እንዳደርግልህ ትሻለህ?› አለው ክርስቶስ፤
‹ማየት እፈልጋለሁ!› አለው ፤ክርስቶስም ሁለት እጆቹን አይኑ ላይ አድርጎ ‹እይ!› አለው፡፡ ሽማግሌው አይኑ በራ፤ በአካባቢው ያሉ ሰዎችንና ጀምበሯን የተመለከተው ሽማግሌ መፈንጠዝ ጀመረ፤
X X X X X X
ይህ የመፅሐፍ ቅዱስ ታሪክ በእግዚአብሔር ለሚያምኑና በእውቀት ላይ ተመስርተው ወገኖቻቸውን ለሚያገለግሉ ሁሉ የሚሰራ ይመስላል፤ ከውልደታቸው ጀምሮና ከጊዜ በኋላ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ከ22 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንን የዓይን ሞራ ግርዶሽ በቀዶ ጥገና በማከም የአይን ብርሃናቸውን የመለሱት የአይን ስፔሻሊስት ሐኪሙ ዶ/ር ጌትነት ንጉሴ ከእንደነዚህ አይነት ባለሙያዎች መሀከል ይጠቀሳሉ፤
ዶ/ር ጌትነት ንጉሴ ባለፉት 30 ዓመታት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በመዘዋወር የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ወገኖቹን ብርሃን በመመለስ ሙያዊ ግዴታቸውን የተወጡ ሰው ናቸው፡፡ ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከሃብታም፣ እስከ ድሃ፤ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከአርሶ አደር እስከ ነጋዴ፤ ከሙስሊም እስከ ክርስቲያን ወዘተ ዶ/ር ጌትነት ሁሉንም አይነት ወገኖች በነፃ በማገልገል የዓይን ብርሃናቸውን መልሰዋል፡፡
በአይን ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በኢትዮጵያ ቢያንስ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን አይነ ስውራን ሰዎች ሲኖሩ ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 50 ከመቶው ሊታከም በሚችለው በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ናቸው፡፡ በዶ/ር ጌትነትና ሌሎች በጎ አድርራጊ ተቋማት በየጊዜው በሚደረገው በየጊዜው የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ቁጥሩን ለመቀነስ ጥረት ቢደረግም ቁጥሩ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም የሚሄደው፡፡
‹ምክንያቱም› ይላሉ ዶ/ር ጌትነት ከዚህ በፊት በህክምና እጦት በአይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር እንዳለ ሆኖ ከስር ከስር ደግሞ በየዓመቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸውን የሚያጡበት ሀገር ነው፤ እድሜ ሲጨምር አይን በሞራ የመጋረድ እድሉ ሰፊ ስለሆነ ቁጥሩ እየጨመ እንጂ እየቀነሰ አይሄድም ይላሉ፡፡

ዶ/ር ጌትነት እንደሚሉት በግላኮማ፤ በስኳር፤ በደም ግፊትና በልዩ ልዩ በሽታዎች ሳቢያ የዓይን ብርሃናቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ያም ሆኖ በህክምና እርዳታ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህመም ተጠቂዎችን ዶ/ር ጌትነትና የስራ ባልደረቦቻቸው ኑሮአቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አድርገው ብርሃን ላጡ ብርሃን እየሆኑ ነው፡፡ ከ100 በሚሊዮን በላይ ህዝብ ባለባት በሀገራችን የዓይን ሐኪሞች ቁጥር ከ120 በላይ አይደለም፤ያም ሆኖ ግን በግለሰብ ደረጃ ለ22 ሺ ሰዎችን ብርሃናቸውን መመለስ የውቅያኖስን ውሃ በማንኪያ ቢመስልም ጉዳዩ የዓይን ጉዳይ መሆኑ ሲታሰብ የዶ/ር ጌትነት ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ አካባቢ የተወለዱት የ53 ዓመቱ ሐኪም ዶ/ር ጌትነት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በፈለገ ህይወት፤በየካቲት 23 እና ከዚያም በኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጀ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት፡፡ ከትምህርት ቤቱ ጎበዝ ተማሪዎች መሀከል አንዱ የነበሩት ዶ/ር ጌትነት የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አምጥተው የህከምና ትምህርት ለመማር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመግባት ከሰባት ዓመታት በኋላ በጠቅላላ ሐኪምነት ተመርቀዋል፡፡
የመጀመሪያ የስራ ዓለምን የተቀላቀሉት በመራሐ ቤቴ አለም ከተማ ነበር፤ አዲስ አበባ ሊያውም መርካቶ አካባቢ ተወልዶ ላደገና ከከተማ ወጥቶ ለማያውቅ ሰው አለም ከተማ ከባድ ፈተናው ነች፤ ለዶ/ር ጌትነትም ገጠራማዋና ተራራማዋ አለም ከተማ ፈትናቸዋለች፤ መብራና ውሃ እንደልብ ባልነበረባት አለም ከተማ በየጊዜው የሚመደቡ ሀኪሞች አይበረክቱባትም ነበር፤ ዶ/ር ጌትነትም ተመድበው እንደሄዱ የአካባቢው ሽማግሌዎች እንደ ሌሎች ሀኪሞች ተማረው ለቆው እንዳይሄዱ ፕሮግራም አዘጋጅትው ነበር የተቀበሏቸው፤ እየዋለ ሲያድር የእዚያ ገጠር ህዝብ ችግርን በሙያቸው መጋፈጥ ጀመሩ፤ለራሳቸውም ቃል ገቡ፤

ለሶስት ዓመት በአለም ከተማ ሲቆዩ የአካባቢውን ህብረተሰብ ባህል አጠኑ፤ እንደባህል ከተያዙ ጉዳዮች መሀከል ልጆችን ክትባት ማስከተብ አልተለመደም፤ ዶ/ር ጌትነት ቦታው ላይ ሲሄዱ በአካባቢው ከሚወለዱ ህጻናት 36 ከመቶ ብቻ ነበሩ የሚከተቡት፤ ይህንኑ ችግር በመመልከት ከሜንሽን ፎር ሜንሽን ከተባለው የጀርመን ድርጅት ጋር በመተባባር ፕሮጀክት በመቅረፅ የአካባቢውን የክትባት መጠን ‹ከ36 ከመቶ ወደ አንድ መቶ ከመቶ አደርሰዋለሁ› ብለው ለክልሉ ጤና ቢሮ እቅድ አስገቡ ፤ የክልሉ ሰዎች ‹ሊሆን የማይችል እቅድ!!› በሚል ስሜት ቢቀበሏቸውም እቅዱ ይሳካል የሚል እምነት አልነበራቸውም፤ ግን የጠየቁትን በጀት ፈቀዱላቸው፤ በዓመቱ ግን የአካባቢው ህብረተሰብ የህጻናት ክትባት ምጣኔ 106 በመቶ መሆኑ በጥናት ተረጋጠገጠ፤ በወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳር በነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ በተገኙበት ዶ/ር ጌትነት እውቅና አገኙ፤
ከመርሀ ቤቴ ወደ ደብረብርሃን ተዛውረወ ለ3 ዓመታት ያህል የሰሩት ዶ/ር ጌትነት ወደ አዲስ አበባ ተመልሰውም ተወልደው ያደጉበት በአዲስ ከተማ አካባቢ የግላቸውን ክሊኒክ ከፈቱ፤ ክሊኒኩ ለበርካታ ሰዎች አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ቢሆንም አትራፊ ሆኖ ሊቀጥል አልቻለም፤ ክሊኒኩ አትራፊ ሊሆን ያልቻለው የሚያስከፍለው ክፍያ እንደ መንግስት ሆስፒታል በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ቁጥራቸው ቀላል ለማይባሉ ሰዎች በየዕለቱ በነፃ ህክምና በመስጠቱ ነበር፤ ‹ተወልጄ ባደኩበት ሰፈር ያሉ ሰዎችን እንዴት ብዬ ነው የማስከፍላቸው› ይላሉ ዶ/ር ጌትነት ክሊኒኩ ስለተዘጋበት ምክንያት ሲናገሩ፡፡
ክሊኒኩ ሲዘጋ ዶ/ር ጌትነት ትምሀርት ቤት ገቡ፤ ከጠቅላላ ሀኪምነት የዓይን ህክምና በመማር የዓይን ስፔሻሊስት ሀኪም ሆኑ፤ የጠፋውን የወገኖቻቸውን ዓይን የማብራት ተግባራቸውን ‹ ሀ ›ብለው የጀመሩት ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው፡፡በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያሉ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ወገናቸውን ለመርዳትም ከኦርቢት ኢንተርናሽናል ጋር ይገናኛሉ፤ ኦርቢስ በገጠር አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነፃ የዓይን ህክምና ይሰጥ ስለነበር ለዶ/ር ጌትነት ዓይን የማብራት ፍላጎታቸውን አሳካላቸው፤
የመጀመሪያ ጉዟቸው ወደ ወልቂጤ ነበር፤ የ300 ሰዎች ዓይን ቀዶ ጥገና በማድረግ ብርሃናቸው መለሱ፤ እንደገና በወሩ እዚያው ወልቂጤ ተጨማሪ 300 ሰዎች በድምሩ ለ600 ሰዎች ህክምና አደረጉ፤ ለዓመታት ዓይነ ስውር ሆነው በመንገድ መሪና በረዳት ተቸግረው የነበሩ ሰዎች ዓይናቸውን ታክመው ዓይናቸው ሲበራ ፊታቸው ላይ የሚያየው ደስታ ያረካቸው ጀመር፤ ዓይናቸው የበራላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተሰቦቻቸውም ጭምር መርቀውት መርቀውት አልረካ ሲሉ ‹ሆድ ይመርቅ !› ብለውት ነበር የሚሄዱት፡፡
በወልቂጤ የተጀመረው የአይን ብርሃን የማብራት ህክምና ላለፉት 30 ዓመታት በመላ ሀገሪቱ በመዟዟር ለተቸገሩና ብርሃን ላጡ ወገኖች ብርሃን መሆን ችለዋል፤ ከጉራጌ ዞን ቸሃ ወደ አላባ፤ወላይታ፤ከምባታ፤ሶማሌ ደገሃቡር፤ ጂግጂጋ፤ቀብሪዳሃር፤ ሐረር፤ደሴ፤ደብረማርቆስ፤ወልዲያ፤ጎዴ፤ አሰበ ተፈሪ፤ አሳይታ፤ አሰላ፤ ፍኖተ ሰላም፤ ደብረ ታቦር፤ ወዘተ የአይን ብርሃን የማብራት ስራቸውን ኑሮአቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አድርገው ለብዙዎች ተስፋ ሰጥተዋል፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከ600 እስከ 1200 ድረስ ሰዎች ህክምናውን ያገኙ ነበር፤
ዶ/ር ጌትነት በመጀመሪዎቹ ሁለት ዓመታት በገጠር እየዞሩ ህክምናቸውን ሲሰጡ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ገቡ፤ የዓይን ህክምና ክፍል ሀላፊ ሆነው በአስተዳደርም በህክምና ስራ ለ7 ዓመታት ያህል ቆዩ፤ በወቅቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ለዓይን ህክምና ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የዓይን ብርሃን ያጡ ሰዎች በወቅቱ የሚሰጣቸው ቀጠሮ 2 ወር ከ15 ቀን ነበር፤ ዶ/ር ጌትነት ክፍሉን በበላይነት መምራት ከጀመሩ በኋላ ግን ከሀኪሞች ጋር በመነጋገርና ፕሮግራም በማውጣት ዛሬ የመጣ ሰው ነገ ቀጥሮ ተሰጥቶት ታክሞ አይኑ በርቶ ወደቤተሰቦቹ እንዲሄድ ማስደረግ ችለዋል፤ የተበላሹ የሆስፒታሉ የህክምና መስጫ መሳሪያዎችንም ከኪሱ አውጥቶ በማሰራት የህክምና ሂደቱ እንዳይስተጓጎል ብርቱ ጥረት አድርጓል፤ ሐኪሞች ከመደበኛ የስራ ሰኣታቸው በኃላ በዚያው በሆስፒታሉ ውስጥ በተወሰነ የክፍያ ለውጥ ህክምና እንዲሰጡ የተደረገውም ዶ/ር ጌትነት ምንሊክ ሆስፒታልን በሚመሩበት ወቅት ነበር፡፡ ሰዎችን ከማከሙ በተጨማሪ የህክምና ቡድን አደራጅው ከላየንስ ክለብ ጋር በመተባበር ወደ ገጠር እያቀኑ የብዙዎችን ብርሃን መልሰዋል፡፡

ዶ/ር ጌትነት የህክምና ቡድኑን ይዘው የዓይን ሞራ ህክምና ወደሚደረግባቸው አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፕሮግራም መሰረት ሲሆን በመንግስት ሆስፒታል እዚያው አካባቢ ባሉሐኪሞች አማካይነት በዓይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ብርሃናቸውን ያጡ ሰዎች ተመርምረው አስቀድመው ተመዝግበው እንዲዘጋጁ ያደርጋል፤ ህክምናውም የሚሰጠው በመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከህክምናው በኋላ ክትትል የሚያስፈልጋቸውን ህመምተኞች የሆስፒታሉ ሀኪሞች እንዲከታተሏቸው እድል ይሰጣል፤ በመሆኑም ቡድኑ በቦታው ሲደርስ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ በቀጥታ ወደ ቀዶ ጥገናው ነው የሚገባው፤ በቀን ከ60 እስከ 80 ሰዎችን በአንድ የጉዞ ፕሮግራም እስከ 800 ሰዎችን የሚያክሙት ዶ/ር ጌትነትና ቡድናቸው ቀዶ ጥገና የተደረገለት ሰው ዛሬ ተሰርቶለት ነገ አይኑ ስለሚበራለት በሰው ድጋፍ የመጡ ሰዎች እየጨፈሩ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ መመልከት ስራውን እንዲወዱት እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡
ያም ሆኖ የመንግስት ፖሊሲ ቅድሚያ የሚሰጠው ለተላላፊ በሽታዎችና ገዳይ ለሚባሉ በሽታዎች በመሆኑ ለእንደዚህ አይነት የዓይን ህክምና ጉዳይ የሚይዘው በጀት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ህብረተሰቡም የዓይን ሞራ ግርዶሽ በህክምና በቀዶ ጥገና የሚስተካከል መሆኑን ስለማያውቅ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች አይናቸው ጠፍቶ ከምርታማነት ውጪ መሆናቸው ዶ/ር ጌትነትን ያስቆጫቸዋል፤
ይህኑን ችግር ለመፍታትም ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ከለጋሾች ጋር በመተባባር መንግስት ብሄራዊ የዓይነ ስውርነት ማስወገጃ ኮሚቴ // በመመስረት ችግሩን ለመቅረፍ ብዙ ተሞክሯል፤ የኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ጌትነት በዚህ በኩል ህክምና የማግኘት እድሉ ያልነበራቸው የገጠር ነዋሪዎች ህክምናውን በነፃ እንዲያገኙና ብርሃናቸው እንዲመለስ አድርገዋል፡፡
ምስክርነቶች
ዶ/ር ጌትነት የዓይን ብርሃን ያጡ ሰዎች ብርሃናቸው ተመልሶ ማየት ሲችሉ የሚያሳዩት ድርጊት እየማረካቸው ሲመጣ ቀዶ ጥገና የሚደረግላቸውን ሰዎች ከህክምናው በፊትና በኋላ በቪዲዪ ማስቀረፅ ጀምረዋል፤በዚህ መልክ ከሰራቸው ከ22 ሺ በላይ ሰዎች መሀከል ከ1500 በላይ የሚሆኑ ባለ ታሪኮችን በቪዲዮ አስቀርፀው ዶክመንት ይዘዋል፤ብዙዎቹ በሰዎች ድጋፍ ሲመጡ የሚታዩ ሰዎች ቃለ ምልልስ ሲደረግላቸው ዓይናቸው የሚበራ አይመስላቸውም፤ ህክምናው ተሰጥቷቸው ዓይናቸው ሲፈታ ደግሞ የሚታየው ሁኔታ ብዙ ጊዜ የሚያሳዝንና የሚያስለቅስ ነው፤ ዶ/ር ጌትነት ህክምናቸውን ሰርተው ዓይናቸውን ሲፈታ በአንዳንድ ሰዎች ድርጊት አብረው ሲያለቅሱ በቪዲዮ ላይ ይታያል፤
የአንዳንዶቹን ምስክርነት ማቅረብ ለእማኝነት ያግዛልና እነሆ!
አቶ አብዱ ሱማሌ ክልል ጎዴ ነዋሪ ናቸው፤ለ13 ዓመት አይነ ስውር ነበሩ፤ ከገጠር ወደ ከተማ በስንት መከራ እንዲመጡ ተደረገ፤ተሰራላቸውና ዓይናቸው በርቶ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፤ በማግስቱ አቶ አብዱ ተመልሰው መጡና ዶ/ር ጌትነትን ማግኘት እፈልጋለሁ አሉ፤
‹ምንድነው› ሲላቸው፤
‹ልጆቼ አታለውኛል› አሉ፤
‹በምን ምክንያት› ሲላቸው፤
ሰውየው በአካባቢው የታወቁ ሃብታም ናቸው፤ እናም ሶስተኛ ሚስት ማግባት እፈልጋለሁ ሲሉ ልጆቻቸው አንዲት ሴት አምጥተው ያጋቧቸዋል፤ ሁለት ዓመት አብረው ሲኖሩ ሚስት ልትወልድላቸው አልቻለችም፤ ‹በአላህ ስራ አልገባም› ብለው በተቀመጡበት ሰዓት ዓይናቸውን ታክመው ማየት ሲችሉ ያገቧት ሴት ድምፃ ነው እንጂ የልጅ ዕድሜዋ የገፋ መሆኑን ይመለከታሉ፤ በመሆኑንም ይላሉ አቶ አብዱ ‹በመሆኑም ይህቺን ሴት እውነታውን ደብቀው ልጆቼ ያጋቡኝ ወራሽ እንዳይመጣ ነው፤ ስለዚህ አሁን ካለኝ 60 ግመሎች ውስጥ ዓይኔን ስላበራህልኝ 30 ግመሎችን ልሰጥህ ነው መጣሁት› ይላል፤ ዶ/ር ጌትነት ግመሎቹን ባይቀበሉም ታሪኩን ተመዝግቦ እንዲቀመጥ አድርገዋል፤
የስምንት ዓመቷ ቀብሪዳሃር ከተማ ነዋሪ የሆነችው ታዳጊ ደግሞ ከውልደቷ ጀምሮ ዓይኗ አያይም ነበር፤ ዶ/ር ጌትነት ጋር በእናቷ አማካይነት መጥታ ቀዶ ጥገና ከተሰራላት በኋላ ዓይኗ ሲገለፅ በአካባቢያዋ ከነበሩ ሰዎች መሀከል እናቷ ነበረችበት፤ ነገር ግን እናቷን የምታውቃት በድምፃ ብቻ በመሆኑ እናቷ ምንም ነገር እንዳትናገር ተነግሯት ዝም አለች፤ ልጅቷ ማየት ስትጀምር እናቷን መለየት አልቻለችምና ግራ ተጋብታ እየጮኸች ወደ ውጭ ትሮጣለች፤ ይህን ጊዜ እናቷ ስሟን እየጠራች ስትከተላት ቆመች፤ለመጀመሪያ ጊዜ እናቷን አየቻትና ተቃቅፈው ሲላቀሱ ይታያል፤

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ56 ዓመቱ አርሶ አደር ከጊዜ በኋላ ዓይነስርውር ሆኖ ነበር፤ እናም የእነ ዶ/ር ጌትነት የህክምና ቡድን ሰቆጣ ሲመጣ ህክምናውን ለማግኘት ሆስፒታል መጣ፤ በየዓይኑ ምክንያት ስራ ፈትቶ ወደ ደጅ ለመውጣት እንኳ የሰዎችን እርዳታ ለመጠየቅ የተገደደው አርሶ አደር ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ዓይኑ ሲበራ ደስታው ወሰን አጣ፤ ‹አሁን ምን ታደርጋለህ?› ሲባል ‹ወደ ስራ ነዋ!› በማለት በማግስቱ ወደ እርሻ ስራ መግባቱ ታይቷል፤
ሽልማቶች
ድምፁን አጥፍቶ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየዞረ ብርሃን ላጡ ወገኖቹ ብርሃን ሲሰጥ የኖረው ዶ/ር ጌትነት ልታይ ልታይ የማይል ብርሃናቸው በተመለሰላቸው ሰዎች ደስታ የሚደሰት በጎ አድራጊ ነው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ላከናወናቸው ተግባራትም ከ53 በላይ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት በርካታ ምስክር ወረቀቶችና ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክተውላቸል፤
‹የእኔ ደስታ የወገኖቼ ብርሃን ተመልሶ ማየት ነው!› የሚሉት ዶ/ር ጌትነት በአሁኑ ወቅት ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ናቸው፡፡ የራሳቸውን ቦናፋይድ የተባለ የህክምና መሳሪያዎች አስመጪ ድርጅትም ከፍተው ከ100 በላይ ለሆኑ ወገናቸው የስራ ዕድል ከፍተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፤

