ጃል መሮ
ኩምሳ ዲሪባ ወይም በትግል ስሙ ጃል መሮ ተብሎ የሚታወቀው በምዕራብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ጦር አዛዥ ነው። በተጠናቀቀው አመት አነጋጋሪ ከነበሩ ግለሰቦች አንዱ ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ በቢቢሲ በኩል ብቅ እያለ አነጋጋሪ አስተያየቱን አስነብቦናል፡፡
በኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና በመንግሥት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከፍተኛ ውጥረትን አንግሶ እንደነበር ይታወሳል። ይህን ብቻ ሳይሆን በክልሉ ውስጥ ለሚፈጸሙ ግድያዎች እና ዘረፋዎች መንግሥት ኦነግን ተጠያቂ ሲያደርግ ቆይቷል።
የክልሉ ፖሊስ እና ባለስልጣናት በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ኦነግን የአከባቢው አስተዳደሮችን ይገድላል፣ ጦር መሳሪያ ይዘርፋል እንዲሁም ሚሊሻዎችን ትጥቅ ያስፈታል ሲሉ ከሰዋል።
ጃል መሮ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚንቀሳቀሳው የኦነግ ሠራዊት ዘንድ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ብቻም ሳይሆን አንዳንዶች ከሊቀመንበሩ ዳውድ ኢብሳ እዝ ነጻ ሆኖ በራሱ የሚንቀሳቀስ ቡድንን የሚመራ እንደሆነ ይነገርለታል።
ቢቢሲም በምዕራብ ኦሮሚያ ስላለው ሁኔታ እና ከኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስላለው ግነኙነት ከጃል መሮ ቃለምልልስ አድርጎ ነበር። ‹‹ኦነግ የራሱ የሆነ ፍላጎት ወይም ተልዕኮ የለውም። ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎትን ነው የሚያስጠብቀው። ጦሩም የኦነግን ተልዕኮ ነው የሚወጣው›› የሚለው ጃል መሮ አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀመንበር እና የጦሩ የበላይ አዛዥ በመሆናቸው እንገናኛለን ማለቱም ይታወሳል። ‹‹ከእሳቸው ጋር ብዙ ጉዳዮች ያገናኙናል። ብዙ ጉዳዮች ላይ እንወያያለን። ውይይታችንም አንዴ ወይም ሁለት ጊዜ አይደለም። በቋሚነት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንወያያለን። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። የተወያየንበትን ርዕሰ ጉዳይ ማወቅ ካሻህ ግን እሳቸውን ደውለህ ጠይቅ።›› ብሎ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአባገዳዎችን የሰላም ጥሪም ሳይቀበል ቀርቷል፡፡ ጃል መሮ ባለው ሁኔታ ስምምነቱን ተቀብሎ ለመግባት ዝግጁ እንዳልሆነ ገልጿል።
የአባገዳዎችን ጥሪ ለመቀበል እና እርቅ ለማውረድ ዝግጁ ስለመሆኑ ሲጠየቅም “የእርቅ የተባለው ኮሚቴ እኔን በአካል አግኝተው ለማነጋገር ፍላጎት የላቸውም። ትኩረት ያደረጉት ጦሩን አንድ በአንድ እጁን እንዲሰጥ ማድረግ ላይ ነው” በማለት እሱም እነሱን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ይናገራል።
እንዲያውም “ጦሩን የመበታተን ዓላማ ይዘው ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት” ሲል ይከሳል።
‹‹የዓመቱ ሰዎች››
