‹‹የዓመቱ ሰዎች››

እስክንድር ነጋ
ታላቁ እስክንድር ወይም እስክንድር 3ኛ ዘመቄዶን (364-331 ዓክልበ.) ከ344 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ መሞቱ ድረስ የመቄዶንያ ንጉሥ ነበረ። ታላቁ እስክንድር የተወለደው ጁላይ 20 በ356 ከክርስቶስ ልደት በፊት ፒላ በምትባለው ጥንታዊት የግሪክ መንደር ሲሆን በ20 ዓመቱ የአባቱን ፊሊፕ 2ኛ ንግስትና እስከሚይዝ ድረስ ለማመን የሚከብዱ ጦርነቶች ላይ በመሳተፍ የውጊያ ብቃቱን ያስመሰከረ ወጣት ነበር፡፡ ጦርነቱንም ከግሪክ እስከ እስያና ሰሜን አፍሪካ ካይሮ ድረስ የተዘረጋ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በ30 ዓመቱም በዓለማችን ላይ በትልቅነቱ የሚጠቀሰውን ኢምፓየር ከግሪክ እስከ ሰሜን ምዕራብ ህንድ ድረስ ዘርግቶ ገዝቷል፤ በአልበገር ባይነቱና በውጊያ ብቃቱ የሚታወቀው ታላቁ እስክንድር በውትድርና ሙያው አቻ የሌለው ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡፡ ታላቁ እስክድር በልጅነቱ ለጥበብን ለፍልስፍና ቅርበት እንደነበረው ይነገራል፡፡ በ16 ዓመቱም መምህሩ የነበረው አሪስቶትል እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ ታላቁ እስክንድር ከሚጠቀሱለት ባህሪዎቹ መሀከል ለዓላማው ሟች ሰው መሆኑ አንዱ ነው፡፡ በውትድርና ሙያው በውጊያ ለአንድም ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞት አያውቅም፡፡ ሁሌም ወደ ውጊያ ሜዳ ከመውጣቱ በፊት በሰከነ መንፈስ ያስባል፡፡ ያቅዳል፤ ወታደሮቹንም በውጊያ ታክቲኮች ላይ ያሰለጥናል፡፡ ወደ ውጊያ ሲገቡም በድል አድረጊነት ይመለሱለታል፡፡
ታላቁ እስክድንድር በወታደሮቹ መሀከል መከፋፈል እንዳይኖር አጥብቆ ይሰራ ነበር፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ወታደሮችን ለውጊያ ቢያሰልፍም ለአንድ ኣላማ መቆማቸውን ማረጋገጥ ይፈልግ ነበር፡፡ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወታደሮቹን እንኳ በወታደራዊ ዲስፕሊን ያንጻቸው ስለነበር የዓላማ አንድነታቸው በተግባር ይገለፅ እንደነበር ተፅፏል፤
ታላቁ እስክንድር የመጀመሪያ ጦርነቱን ሲያካሂድ እንኳ ካሉት ወታደሮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን አላሰለፈም ነበር፡፡ 13 ሺ ወታደሮቹን ይዞ ከ40 ሺ በላይ የሆነውን የፐርሺያ ግዙፍ ጦር ማርኳል፡፡ በጦርነት ለማሸነፍ የወታደሮች ብዛት ሳይሆን ጠንካራ የውጊያ ብቃት፤ ዓላና ዲስፕሊን ነው የሚያስፈልገው የሚል እምነት አለው፤
እስክንድር ባደረጋቸው ውጊያዎች ሁሉ በመርታት ግሪክን ከመላው ዓለም ጋር ለማገናኘት ችሏል፡፡ ህዝቦቿም የንግድ መስመር አግኝተው እንዲገበያዩ በር ከፍቷል፡፡ ለግሪክ ስልጣኔ መሠረት የሆነውን የንግድ ልውውጥ እስከ ሜዲትራንያ ባህር ድረስ ከ200 እስከ 300 ዓመታት ድረስ እንዲዘልቅ ያደረገው እስክንድር እንደሆነ ይታመናል፡፡
‹የዳግማዊ እስክንድር› ተጋድሎ
‹አዲስ አበባ ባለቤት አልባ ከተማ› ሲል ፖለቲካኛው ኤርሚያስ ለገሠ ታሪኳን የዘረዘረላትን አዲስ አበባ ባለፈው መጋቢት ወር በዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት ለውጥ በመላ ሀገሪቱ ከመጣ በኋላ እንኳ ከተማዋ ባለቤት ያላት አትመስልም ነበር፡፡ ማንም እየተነሳ ‹የእኛ ናት!› የሚል መግለጫ ሲሰጥ የከተማዋ ነዋሪ እንዴት የሚል ሲቪል ማህበረሰብ ወይም የፖለቲካ ፖርቲ ብቅ አላለም፡፡ ከ‹ታላቁ› እስክንድር ነጋ በቀር፡፡
የታላቁ እስክንድርን ወኔና ፍትሐዊ ዓላማ አንግቦ ለከተማዋ ነዋሪዎች ድምጽ መሆኑን እያስመሰከረ ያለው እስክንድር ነጋ በረጋና በሰለጠነ መንገድ የአዲስ አበባ ከተማን የነዋሪዋቿ የማድረግ ሰላማዊ ትግሉን ሚሊዮኖችን ከጀርባው አሰልፎ ጀምሯል፡፡ እስክንድር ነጋ በውጊያ ብቃቱ ዓለም እንደመሰከረለት እንደ ታላቁ እስክንድር ጦር ሰባቂና ዘገር ነቅናቂ ባይሆንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚና ፖለቲካ መናህሪያ ለሆነችው ለአዲስ አበባ የሚመጥን የሰለጠነ የሀሳብ ትግል ለማድረግ ውሎው አደባባይ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
እስክንድር ከወራት በኋላ ሲብላላ የቆየውን የአዲስ አበባ ነዋሪ ጥያቄ ይዞ አደባባይ ሲወጣ በመጀመሪያ የባልደራስ ስብሰባው ላይ ሚሊዮኖች ተገኝተውለታል፤ ‹ከተማዋ የሁላችን ናት› ሲል ድምጹን ያስተጋባው የከተማው ነዋሪ መብት የሌለው ግዑዝ ፍጥረት አድርገው መግለጫ ሲያወጡበት የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ቆም ብለው ጥያቄያቸውን እንዲያጤኑት አስቸሏቸዋል፡፡ በፀና አቋሙ የሚታወቀው እስክንድር ማንም ሊያስፈራራው ፤ ማንም ከአቋሙ ሊያናጥበው የማይችል ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እንደሆነ ተመስክሮለታል፡፡ ለአዲስ አበባ ነዋሪ የትግል አርማ መሆኑን የሚጠቅሱ አስተያየቶች ከተለያዩ አካባቢዎች እየተሰሙ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከተማዋና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህገ ወጦች መረን የለቀቀ ስራቸውን በአደባባይ ሲፈፅሙና ሲናገሩ አንዳችም ምላሽ ያልሰጡት ዶ/ር አብይ አህመድ ለእስክንድር ሲሆን ‹ወደ ግልፅ ጦርነት እንገባለን› ማለታቸው የታላቁ እስክንድርን ሰላማዊ አካሄድን ያላገናዘበ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
‹‹መብቴን አሳልፌ አልሰጥም፤ የትም ብሆን ስለመብቴና ሀገሬ ያገባኛል፡፡ እዚህ ከሚጠይቁኝ ሰዎች ጋር የፈለኩትን ማውራት እችላለሁ፡፡ እናንተ ከፈለጋችሁ በር ላይ መልሷቸው እንጂ እኔ ጋር ከመጡ በኋላ ስለሀገሬ ከእነሱ ጋር መነጋገር መብቴ ነው፡፡ አዎ የትም ቦታ ብሆን፣ መቼም ቢሆን ስለ ሀገሬ ያገባኛል!›› እስክንድር ነጋ እስር ቤቴ ሳለ የተናገረው ነው፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከ1993 ጀምሮ ለኢትዮጵያዊያን ነጻነት፤ መብትና ክብር ሲታገል የቆየ ታላቅና ደፋር ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ሁሉም ይመሰከርለታል። በየአካባቢ ሲደረጉ በነበሩ የተቃውሞ ሰልፎች ከእስር እንዲለቀቁ ህዝቡ ጥያቄውን ሲያቀርብላቸው ከነበሩት ታጋዮች አንዱ ነው፡፡ ጋዜጠኛውና የሰብአዊ መብቶች ጠበቃው እስክንድር ነጋ፤ የራሱንና የቤተሰቡን የግል ጥቅም ወደ ጎን ትቶ፤ ህይወቱን ለአደጋ አጋልጦ ዘውግና ኃይማኖት ሳይለይ ለቆመለት የታገለ ኢትዮጵያዊ ነው።
ህወሓት በበላይነት ይመራው በነበረው ጨካኝና አፋኝ የኢህአዴግ መንግሥት በፈጠራ ወሬ “ሽብርተኛ ነህ” ተብሎ ተከስሶ ለ18 ዓመታት እንዲታሰር ተፈረደበት። ለ7 ዓመታት በቃሊቲ እስር ቤት ሲሰቃይ ከቆየ በኋላ የዶ/ር አብይ ወደስልጣን መምጣትን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ተፈታ። አንድ ወር ሳይሞላ በመጋቢት ወር እንደ ገና ታሰረ። የታሰረበት ዋና ምክንያት ብዙ ሚሊየን የኢትዮጵያ ሕዝብ መለያ አድርጎ የተቀበለውን “አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ” በስብሰባው አዳራሽ ስለተጠቀመ ነው።
የሰብአዊ መብት አክቲቪስትና የመናገር ነጻነት “ጀግና” ተብሎ የተጠራው እስክንድር ነጋ ዓለም ያከበረው ኢትዮጵያዊ ነው። እስክንድር ነጋ በዓለም ደረጃ የታወቀውን የPen/Barbara Goldsmith Freedom ሜዳል ተሸልሟል። እንደገና የInternational Press Institute (IPI)’s 69th World FreedomHero Awardንም ተሸልሟል። Amnesty International, the Committee to Protect Journalists (CPJ), Freedom House, Human Rights Watch እና ሌሎች የታወቁ ድርጅቶችና ግለሰቦች ይህ ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ሕዝብ ሰብአዊ መብት ተሟጋች መሆኑን መስክረውለታል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከሌሎች የአዲስ አበባ ተቆርቋሪዎች ጋር በመሆን በ2011 “ለአዲስ አበባ ምን ይደረግ?” በሚል አንድ ታላቅ ውይይት ጠርቶ ነበር፡፡ በውይይቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው አዲስ አበቤ ታድሟል፡፡ ታዳሚያኑ የከተማዋን አስተዳደር በብርቱ ወቅሰዋል። የከተማዋ አስተዳደር “በእርግጥ የነዋሪዎቹን ጥቅም እያስከበረ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የሚመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሌላ አካልን ጥቅም ለማስጠበቅ የቆመ ነው” ሲሉ በህዝባዊ ስብሰባው ላይ የተሳተፉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም አሁን ያለውን የከተማዋን አስተዳድር “እንደማይቀበለው” ለተሳታፊዎች ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማይቱ “ጥቅም ላይ የመደራደር ህጋዊም፣ ፖለቲካዊም ስብዕና የለውም” ሲል እስክንድር አቋሙን ለታዳሚያኑ በንባብ አሰምቷል፡፡ “አዲስ አበባ የተሰራችው በፍቅር፣ በአንድነት እና በወንድማማችነት ስሜት በመሆኑ ይህችን የጋራ ቤታችን የምንመኛት የአፍሪካ መዲና እንድትሆን ነው” ሲል ጋዜጠኛ እስክንድር ተናግሯል።
ተሳታፊዎቹም “ከተማዋ ባለቤቶቿ ነዋሪዎቿ እንደሆኑ እና በነዋሪዎቿ የተመረጡ ወኪሎች ሊኖሯት እንደሚገባም” በመስማማት ሙሉ ውክልናቸውን ለውይይቱ አዘጋጆች ሰጥተዋል፡፡ ቁጥሩ በርከት ያለ የከተማዋ ነዋሪ በተሳተፈበት በዚህ ውይይት ላይ ስለ ህግ፣ ፍትህ እና ሰብአዊ መብት እንዲሁም ስለ ምርጫ ነዋሪው የነቃ ተሳትፎ እና ክትትል እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የውይይቱ አዘጋጆች ህዝባዊ ስብሰባውን በሰፊ አዳራሽ ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ መከልከሉን ገልጸዋል። በቀጣይ መሰል የውይይት መርሃ ግብር በመስቀል አደባባይ እንደሚያደርጉም አሳውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ሆኖ ያደረገው ውይይትና አቤቱታ እስክንድር ልክ ያልሆነ ነገር ከተመለከተ ትግሉን መቼም እንደማያቋርጥ ማሳያ ነው፡፡ ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአደባባይ ቢነቅፉትም ብዙዎች ግን በጨዋነት ተቃውሞውን ማሰማቱና ከህዝቡ ጋር መወያየቱ ሊከበርለት ይገባል ሲሉ ተሟግተዋል፡፡
በራስ ሆቴል በተደጋጋሚ የጠራው ስብሰባ የተደናቀፈበት እስክንድር የሳተላይት ቴሌቪዥን ለመመስረት የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫም ተሰርዞበታል፡፡ያም ሆኖ እስክንድር ከ6 ሚሊየን በላይ የሚገመተው የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር፤ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን የማሻሻል መብት እንዳለው በማመን የአዲስ አበባ ሕዝብ መመራትና መተዳደር ያለበት ነዋሪው ሕዝብ በመረጣቸው ሃላፊዎች መሆን አለበት ብሎ ያምናል። ጋዜጠኛ እስክንድር ደጋግሞ የተናገረው የነዋሪዎቹ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ይጠበቅ ነው። ስለዚህ፤ መንግስት በእስክንድር ነጋ ላይ የሚካሄደው ማስፈራራትና አላስፈላጊ ዛቻና በአስቸኳይ እንዲቆምና በዚህ የታወቀና ጨዋ ኢትዮጵያዊ ላይ አደጋ እንዳይደርስበት ትኩረት እንዲሰጡልን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር ድጋፍ ማግኘቱ ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ዝምታን በመረጡበት በዚህ ወቅት የእስክንድር ብቻውን መቆም በ2011 አነጋገሪ ከነበሩ ክስተቶች መሀከል አንዱ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe