‹‹የዓመቱ አነጋገሪ ሰዎች››

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ምናልባት በኢትዮጵያ ዘመናይ ታሪክ በገዛ-ፍቃድና ፍላጎቱ በነቂስ አደባባይ የወጣዉ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን የለዉጥ እርምጃ በመደገፍ ነዉ። ኢትዮጵያ የሚኖረዉ አይደለም አሜሪካና አዉሮጳ የተሰደደዉ ኢትዮጵያዊ ከዋሽግተን ዲሲ-እስከ ፍራንክፈርት የሚገኙ አደባባዮችን ያጥለቀለቀዉ ጠቅላይ ሚንስትሩን አወድሶ፣ ጅምር ሥራቸዉን አሞግሶ ነዉ። የኤርትራ ሕዝብ ሳይቀር የአስመራ አዉራ ጎዳናዎችን በሰልፍ የሞላዉ ለአዲሱ የኢትዮጵያ መሪን ሥራና እርምጃን በማድነቅናማወደስ ነዉ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በ2011 የመንግስታቸዉን አሰራርና ዓላማን የሚጠቁም ዕቅድ ወይም ፍኖተ ካርታ አለማሳወቃቸው ግን እያስተቻቸው ነው።ህዝቡ ፊቱን ማዞር ጀምሯል፡፡ ከአዲስ አበባ ዉዝግብ እስከ ምዕራብ ጎንደር ግጭት፣ ከምዕራብ ወለጋ እስከ ድሬዳዋ፣ ከመተሐራ እስከ ጌዲኦ የየዋሕ ኢትዮጵያዉያን ሞት፣ መፈናቀልና ሥጋት ህዝቡን ያሳስበዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ሁሉም የሚሳተፍበት አግባቢ ድርድር ማድረግና ሕግና ሥርዓት ማስከበር ያስፈልጋል የሚሉ ድምጾች አሁንም እየሰተሙ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ፈተና እየተደቀነባቸው የመጣው ከዓመቱ መጀመሪያ መስከረም ወር ጀምሮ ነው፡፡ የግንቦት 7ና የኦነግ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት የጀመረው ረብሻና የሰዎች ግድያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፀጥታ የማስከበር ብቃት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተተው ብዙም ሳይቆይ ነው፡፡ በተለይም የኦነግ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት በቡራዩ አካባቢ የተፈፀመው ዘግናኝ ድርጊት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደማንኛውም ግለሰብ ቦታውንና ጥቃት የተፈፀመባቸውን ሰዎች ጎብኝተው አይናቸው እንባ አቅሮ ከመታየቱ በቀር ይህ ነው የተባለ በፈፃሚዎቹ ላይ የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ ጥርጣሬን ፈጥሯል፡፡
ብዙም ሳይቆይ በህዳር ወር አጋማሽ ላይ የታጠቀው የኦነግ ሰራዊትን በተለያዩ አካባቢዎች ችግር መፍጠሩ ሲነገርና ሊቀመንበሩም ‹ ትጥቅ ፈቺም አስፈቺም የሚባል ነገር የለም› የሚል መግለጫ መስጠታቸው የኦነግና የመንግስት ስምምነት ምንነት ላይ ጥያቄ ያላቸው ወገኖችን ፈጥሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በያዙ ማግስት ወደ ሰሜን አሜሪካ ሄደው ባለደጉት ንግግር ከፍተኛ የሆነ የዲያስፖራው አቀባበል የተደረገላቸው ቢሆንም በዓመቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶችና መፈላቅሎች ተጠያቂ የሆኑ ወገኖችን ለፍርድ በማቅረብ በኩል የታየው ዳተኝነትና ጣት የመጠቋቆም ሂደት የለውጥ ሂደቱን ወደኋላ እየመለሰው ነው በሚል ሀሳብ የሚሰነዝሩ ሰዎች እንዲበራከቱ አድርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በ2011 መጀመሪያ ላይ ፖርላማውን ሲከፈት የካቢኔ አባላቶቻቸውንና የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን ቁጥር ወደ ሃያ ዝቅ በማድረግ ግማሽ የሚሆኑ የካቢኔ አባላትን ሴቶች በማድረጋቸው ከሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ ያም ሆኖ የተሾሙት ሴቶች የብቃት ችግር ቀደም ሲል ይነሳባቸው የነበሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ ዳግመኛ ቦታ ማግኘታቸው ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ሹመቱን ተጠቅመውበታል በሚል ቅሬታ ያሳሙ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ የሴቶቹ መሾም ብቻውን የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ፤ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ችግር ይፈታል የሚለው ተስፋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨፍገጉን የሚጠቅሱት ወገኖች ሃምሳ ከመቶ ሴቶች ሚኒስተር ከሆኑ በኋላ መጣ የተባለ ለውጥ አለመኖሩ የተሾሙት ሴቶች በብቃት ሳይሆን በኮታ የተደረገ አስመስሎታል የሚል ትችት አስከትሎባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለስለስ ባሉ ቃላቶችና ተስፋ የተሞላባቸው ንግግሮች በማግረግ የሚታወቁ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተከታታይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንደተደረገባቸውና ፀጥታን ለማደፍረስ ሌት ከቀን የሚሰራ ሀይል እንዳለ ለፖርላማው መናገራቸው የአመራራቸውን ድክመት ማሳያ ተደርጎ ተወስዳል፡፡ ከዚህም አልፈው ‹በሀይል መንግስትን ከስልጣን አስወግዳለሁ ማለት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዜጋና የህይወት መስዋዕትነት ያስከፍላል› በማለት መናገራቸው ቀደም ሲል ይዘውት የመጡት የመደመር ፍልስፍና የአቃፊነት ፖለቲካ ተቀባይነቱ እየቀነሰ ስለመምጣቱ ማሳያ አድርገው የሚወስዱ ወገኖች አሉ፡፡
ዓመቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎ የሚባል እንዳልሆነ ማሳያዎች ብዙ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባን ጉዳይ ይመለከተናል ብለው የተሰባሰቡ የባልደራስ አባላት ላይ ዛቻ ከሰነዘሩበት ጊዜ ጀምሮ በየክልሎቹ በሚፈጠሩ መፈናቅሎች ሳቢያ ሀገሪቱ በዓለም ላይ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር ቀዳሚ የመሆኗ ጉዳይ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም መንግስታቸው ያሳየው ቸልተኝነት ፤ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ከ20 በላይ ባንኮች ሲዘረፉ ጉዳዮን ‹ያልታወቁ ሃይሎች› የሚል ስያሜ በመስጠት ይህ ነው የተባለ አስተማሪ እርምጃ ያለመውሰዳቸው እንዲሁም የሲዳማ ህዝብ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄና አብዛኛዎቹ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳታቸው ፈተናቸውን ያጎሉ ክስተቶች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲፈጠር በመስራታቸው ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር ምስጋናና ውዳሴ ያገኙበት ዓመት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ሌላ የምርጫ ቦርድን፤ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነትንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አመራሮችን ቀደም ሲል በኢህአዴግ ውስጥ ከተለመደው አሰራር ወጥተው የፖርቲያቸው አባል ያልሆኑ ሰዎችን መሾማቸው ሀገሪቱ የሁሉም ናት የሚለውን የመተባባር መንፈስ ማሳያ ተደርጎ ተወስዶላቸዋል፡፡ ያም ሆኖ የሰብዓዊ መብትን በማስከበር በኩል መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢናገሩም በተለይ ከሰኔ 15ቱ የከፍተኛ አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ የጅምላ እስር መታየቱ ነገሩ እንዴት ነው የሚል ጥያቄ በመንግስታቸው ላይ አስነስቶባቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ27 ዓመቱን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተቹበት የፖርላማ ንግግራቸው ላይ እኛ እንደከዚህ ቀደሙ ‹አስረን አንመረምርም፤ መርምረን ነው የምናስረው› ያሉትን ንግግራቸውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የከተቱ የፍርድ ቤት ውሎዎች አሁንም መታየታቸው መንግስታቸውን ለትችት አጋልጦባቸዋል ፡፡
በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራና ሀገራዊ ምርጫ እንዲሁም የሲዳማ ህዝበ ውሳኔና ተያያዥ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ2011 ወደ 2012 የሚተላለፍ መንግስታቸውን የሚፈተንበት ዋና ዋና ጉዳይ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe