‹‹የዓመቱ አነጋገሪ ሰዎች››

ለማ መገርሳ
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት አቶ ለማ መገርሳ በአንድ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር ሌላኛው የአመቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡
አወዛጋቢ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ፌስ ቡክ እና ትዊተርን በመሰሉ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በሚዘወተሩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሳምንት ከሳምንት አይጠፉም። አንዱ ሲሄድ ሌላ ይመጣል። አንዱ ገና በቅጡ ሳይረግብ ሌላው በእግሩ ተተክቶ ያከራክራል፣ ያፋጫል፣ ያነታርካል ባስ ሲልም ያሰዳድባል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ንግግር ከፍ ያለ ውዝግብን የወለደ ጉዳይ ነበር።
አቶ ለማ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለሰፈሩ የኦሮሞ ተወላጆች ለታዳሚያኑ በኦሮምኛ ያቀረቡት ማብራሪያ ነበር የውዝግቡ መነሻ። “ርዕዮት” በተሰኘ የብዙሃን መገናኛ ወደ አማርኛ የተመለሰው ይሄው የፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ “ቲም ለማ” ተብለው የሚታወቁትን የኢህአዴግ አመራሮች “ድብቅ አጀንዳ ያጋለጠ ነው” በሚል ብዙዎች ተቀባብለውታል። ከአተረጓጎሙ ትክክለኛነት እስከ ከአውድ ውጭ የመወሰድ ጉዳይ አንስተው የተከራከሩም ነበሩ።
በጉዳዩ ላይ የነበረው ውዝግብ እና አተካሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው የሚባልለትን የኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የውይይት ባህል አንድ ማሳያ ሆኗል። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን መምህር አቶ ክብሮም ብርሃነ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያተኮሩ ጥናት ቀመስ ጽሁፎችን ለንባብ አብቅተዋል። በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ባህል ፈረንጆቹ “confirmatory thought” የሚሉት አይነት መሆኑን ያስረዳሉ። ከአቶ ለማ ንግግር ጋር ተያይዞ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተስተዋለውም ይህንኑ አካሄድ የተከተለ ነው ይላሉ።
በአቶ ለማ ንግግር ውስጥ የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ እንቀይረዋለን የሚል ሃሳብ እንዳለበትም ሲገለጽ ነበር፡፡ እሳቸው ግን ጉዳዩን አስተባብለዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ መቼም ቢሆን ሊጠራጠረን አይገባም›› ብለዋል፡፡
“ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዋጣው አንድነት ፣ መተማመንና መተሳሰብ ነው፤ ህዝቡ ነገም ቢሆን ሊጠራጠረን አይገባም” ያሉት አቶ ለማ ”ኢትዮጵያዊነት ሱስ መሆኑን ምንጊዜም ያለ ሀፍረት እናገራለሁ” ብለዋል።
“ለኢትዮጵያ ህዝብ ለኦሮሞ ህዝብ አንድነቱ ነው የሚጠቅመው። አንድነቱ ምርጫ አይደለም ለኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ አይደለም ስንፈልግ የምንወስደው ስንፈልግ የምንጥለው አይደለም አምንበታለሁ። ማመን ብቻ አይደለም ለዚህ ሰርቻለሁ፣ ለፍቻለሁ፣ ዋጋ ከፍያለሁ፤ የኔ ባልደረቦች ዋጋ ከፍለውበታል። ስንሰራ ዝናን ለመፈለግ አይደለም እውቅና በመፈለግ አይደለም ዕውቅና ተሰጠን አልተሰጠን ህሊናዬ ንጹ እስከሆነ ድረስ ለኔ በቂዬ ነው። ስለዚህ አሁንም ኢትዮጵያዊነት ያለ ሀፍረት እናገራለሁ ነገም ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው። ለኦሮሞ ህዝብም የሚጠቅመው እንደኛ አይነት ደሃ ብዙ ድሪቶ ያለብን ህዝብ መከፋፈል አይጠቅመንም። የሚያዋጣን የሚጠቅመን አንድነት ነው። መተማመን፣ መተሳሰብ፣ መቻቻል ነው የሚጠቅመን›› ብለዋል፡፡
እሳቸውም ሆኑ ባልደረቦቻቸው ትልቅ የሆነችውን ሀገር ኢትዮጵያን በማፍረስ ቆሻሻ ታሪክ ጥለው ማለፍ የማይፈልጉ መሆናቸውን አመልክተው ሃይማኖት፣ ጎሳና ዘር በመቁጠር አንዱን ለመጥቀም፣ ሌላውን ለመጉዳት እንደማይሰሩ አረጋግጠዋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብን አንድ ለማድረግ ከምንም በላይ ታሪክ ሃላፊነት የጣለብን። በአማራና በኦሮሞ መካከል የተቀበረውን ለማምከን የእኛ ሃላፊነት ነው ብለን እናምናለን። እነኚህ ሁለት ግንድ ህዝቦች አንድ ሆነው ሌላውን ኢትዮጵያዊ አቅፈው ወደፊት አምጥተው ይህች አገር ሰላም እንድትሆን ማድረግ አለባቸው። ዛሬ ሳይሆን ነገ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን እነኚህ ህዝቦች አንድ መሆን አለባቸው። እራሳቸው አንድ ሆነው ሌላውንም አንድ ማድረግ አለባቸው ብለን በጽኑ እናምናለን። እኛና የአማራ አማሮች ትናንት ስንስማማ በሆነ ወቅት ላይ የሆነ ነገር ሲከሰት ስልጣን እንደቅርጫ እንከፋፈላለን ብለን አናውቅም። እውነቱን ለመነጋገር ያጋመደን ፍቅር አይደለም፤ ችግር ነው። መከራ ነው ያገናኘን እኛ ትናንት ስንገናኝ ነገ ስልጣን አግኝተን ፕሬዚዳንት እንሆናለን ሚኒስትር እንሆናለን የሚል ህልም አልነበረንም እኛ ሞተን ይህቺ አገር ከመፍረስ ማዳን ነው” ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe