በ1957 ዓ ም በሐረር ከተማ ልዩ ስሙ ሸንኮር በሚባለው መንደር ውስጥ ኩራባቸው ደነቀ ተወለደ። በቤተሰቦቹ የሥራ ዝውውር ምክንያት ወደ አሰበ ተፈሪ የአሁኗ ጭሮ ከተማ በህፃንነቱ በመምጣቱ የቄስ ትምህርቱን ፣ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚገባ ተከታትሎ ወደ ከፍተኛ ትምሀርት መግባት የሚያስችል ውጤት በማግኘት በ1975 ዓ ም አጠናቅቋል።
በ1976 ዓ ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናውን ግቢ ስድስት ኪሎ ሲቀላቀል የቴአትር ጥበባት ዲፓርትመንት መኖሩን እንኳ የማያውቀው ኩራባቸው ደነቀ ቀደም ካሉት የዩኒቨርስቲው ተማሪ ከሆኑት የአሰበ ተፈሪ ልጆች ‘ አንተማ ቴአትር አርትስ ነው መግባት ያለብህ ‘ በሚል በርካታ አስተያየት ነበር አቀባበል የተደረገለት።በዓመቱ የዲፓርትመንት ምርጫ ሲያደርግም ሳያወላውል አንደኛ ምርጫው አድርጎ በሞላው የቴአትር ጥበባት የትምህርት ክፍል ተመድቦ በመማር በ1979 ዓ ም በጥሩ ውጤት ለመመረቅ በቅቷል።
በዩኒቨርስቲ ቆይታው ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን የባህል ማዕከል አባል በመሆን በተለያዩ ቴአትሮች ላይ በተዋናይነት በመሳተፍ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ማቅረቡን ይገልፃል።
በ1980 ዓ ም ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀለው ከዘመቻ መምሪያ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ተመድቦ በዕጣ ወደ ደረሰው ጋሞ ጎፋ ክፍለ ሀገር አርባምንጭ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በጀማሪ የቴአትር ኤክስፐርትነት በመሄድ ነበር።
አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በትወና በመድረክ ቴአትሮች ላይ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ መሳተፍ የጀመረ ሲሆን በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ‘የዝናቧ እመቤት ‘ እና ‘የገንፎ ተራራ‘ ቴአትሮች ፤ በሀገር ፍቅር ቴአትር ‘የጨረቃ ቤት‘ ፣ ‘ዓይነ ሞራ‘ ፣ ‘ንጉሥ ሊር‘ ፣ ‘ፍሬህይወት‘ ፣ ‘ጥሎሽ‘ ፣ ‘አሉ‘ ፣ ‘ጣውንቶቹ‘ ፣ ‘ከራስ በላይ ራስ‘ እና ‘የሸክላ ጌጥ‘ ቴአትሮች ፤ በቴአትርና ባህል አዳራሽ ‘የጫጉላ ሽርሽር‘ ቴአትር ፤ በራስ ቴአትር ‘ቅርጫው‘ ቴአትር ይገኙበታል።
በተሳተፈባቸው የተመረጡ ጥቂት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ‘ገመና 1′ እና ‘ገመና 2′ ድራማዎች ብዙ አድናቂዎች ያፈሩለት መሆኑንና በተለይም በቅርቡ በአርትስ ቴሌቪዥን በሳምንት ሦስት ቀናት በ48 ክፍሎች ቀርቦ ያለ ልዩነት በሁሉም ተመልካች ዘንድ ከስምምነት የተደረሰበት ነው ማለት በሚቻል ደረጃ ተወዳጅነትን ባተረፈው ‘እረኛዬ‘ በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ያሳየውን የትወና ብቃት ብዙዎች እንደመሰከሩ፣የእረኛዬ አባላት በሰሜን አሜሪካ የእውቅና ሽልማት ለመቀበል ባቀኑበት ጊዜም ከቨርጂኒያ፣ ከዋሺንግተን ዲሲ እና ሜሪላንድ ስቴቶች ከንቲባዎች በተሰጣቸው የምስክር ወረቀት እና እዚያ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበልና በተሰጣቸው የሞራል ድጋፍ እንዳስደሰተውም በአክብሮት ይገልፃል።
በዳይሬክቲንግ ሥራዎች ካዘጋጃቸው የመድረክ ቴአትሮች መካከል በሀገር ፍቅር ቴአትር ‘ስጦታ‘፣‘ጥሎሽ‘ እና ‘መዳኛ‘ ቴአትሮች ፤ በቴአትርና ባህል አዳራሽ ‘ሶስና‘፣‘አንድ ክረምት‘፣ጥቁሩ መናኝ‘ እና የጫጉላ ሽርሽርና ሌሎች በርካታ ቲያትሮች ይገኙበታል፡፡አርቲስት ኩራባቸው ደነቀ በ1979 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በቲያትር ትምህርት አግኝቷል፡፡
የሦስት ልጆች አባት የነበረው ኩራባቸው ደነቀ ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም በቀጨኔ መድኃኒዓለም ስርዓተ ቀብሩ ተፈጸማል ።

