የዘረኝነቱን እሳት ማን ያጥፋው?

የዘረኝነቱን እሳት ማን ያጥፋው?

መነሻ

‹ቀጣዩ የኢትዮጵያ ስጋት የሀገሪቱ የብሔር ፖለቲካ ነው› የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ

“If we do not approach the problems in Africa with a common front and a common purpose, we shall be haggling and wrangling among ourselves until we are colonized again and become the tolls of a far greater colonialism than we suffered hitherto.”

ይህን የተናገሩት ጋናዊው የአንድነት አቀንቃኝ፣ የነጻነት ታጋይና አፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ክዋሜ ንክሩማህ ናቸው፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በአፍሪካ ህብረት ምስረታ ዕለት ካደረጉት ረጅም ንግግር ውስጥ የተገኘ ነው፡፡ አፍሪካውያን ለአንድነታቸው ዘብ እንዲቆሙ፣ በጋራ ሆነው ከገቡበት ጨለማ በፍጥነት እንዲወጡ መክረው ነበር፡፡ ሁሉም የአፍሪካ ሃገራት ኢትዮጵያን በምሳሌነት እንዲከተሉ ሰብከዋል፡፡ ‹Ethiopia shall rise› የሚል ግጥም ጽፈው ማንበባቸውም ይታወሳል፡፡

የኩዋሜ ንክሩማህ ግጥም በ1950ዎቹ ስለነበረችው ኢትዮጵያ ታላቅነትና በዘመኑ በቅኝ ግዛትና በሌሎችም ችግሮች ውስጥ ተተብትበው ለነበሩት ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ከጨለማው መውጪያ ብርሃን እንደሆነች የሚገልጽ ነበር፡፡ ከነዚያ ሁሉ ዓመታት በኋላ ታዲያ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ጥለውን ወደፊት ሲገሰግሱ እኛ በአንጻሩ ወደኋላ ተመልሰናል፡፡ አርአያ የምንሆን ሳይሆን አርአያ የሚያስፈልገን ሆነናል፡፡ ሌሎችን ከችግራቸው የምናወጣ ሳይሆን ረዳት ፈላጊዎች ለመሆን ተገደናል፡፡

ከሰሞኑ በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ የተከሰቱት ነገሮች ለዚህ አንድ ማሳያ ይሆናሉ፡፡ የእሳት አደጋ ማጥፊያ ሄሊኮፕተር ኢትዮጵያ የላትም፡፡ በዚህም ሳቢያ የአካባቢው ሰዎች በዘልማድ እሳቱን ለማጥፋት ሞከሩ፡፡ አልተሳካላቸውም፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት ጩኸት ተጀመረ፡፡ መንግስት የለም ወይ ተባለ፡፡ በመጨረሻም አለሁ ያለው መንግስት ሄሊኮፕተር ልመና ወጣ፡፡ ወደ ጎረቤት ኬንያ እና ወደ ደቡብ አፍሪካ፡፡ ‹ከፊት የነበርነው ከሰው ኋላ ቀርተን› እንዲል ድምጻዊው ሊለምኑን የሚገባቸውን ለመንናቸው፡፡ የልመናችን ድምጽ ሩቅ ድረስ ተሰምቶ ነበርና እስራኤል ሄሊኮፕተሯን ልካ የእኛን እሳት አጠፋች፡፡

ስር እየሰደደ የመጣውና በፍጥነት እየተቀጣጠለ ያለው የሰሞኑ ሌላኛው ‹እሳት› ደግሞ ዘረኝነት ነው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው የዘር ፖለቲካ ማቀንቀኛ መድረክ ሆኗል፡፡ ጎራ ለይቶ አጸያፊ በሆነ መንገድ መዘላለፍ ያገር ልማድ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ፖለቲከኞች ያለጥንቃቄ ዘረኝነትን የሚያባብስ፣ ሀገርን የሚያፈርስ ንግግር ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ምሁራን የሚባሉትም ይህንኑ ሲያራግቡ ውለው ያድራሉ፡፡ እሳቱ ላይ ጋዝ ያረከፈክፋሉ፡፡ ጥቂቶች ብቻ እሳቱን ለማጥፋት ጭራሮ ይዘው ባላቸው አቅም ጥረት ያደርጋሉ፡፡ እሳቱ ግን መቀጣጠሉን ቀጥሏል፡፡ ያስፈራል፡፡

ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተከሰተውን እሳት ለማጥፋት የውጭ ሀገራትን እርዳታ ጠየቅን፡፡ በነሱ ድጋፍ ተሳካ፡፡ የዘረኝነት እሳቱን ለማጥፋትስ የማንን እርዳታ እንጠይቅ?

ውድመት

ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የእሳት ቃጠሎ ከፍተኛ የሥነ-ምዳር ጉዳት ማስከተሉን የፓርኩ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከ420 በላይ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰው የእሳት አደጋ በብርቅየ እና አጥቢ እንስሳት ላይ ጉዳት ባያስከትልም በብርቅየ እና የፓርኩ መለያ በሆኑ ዛፎች፡ የወፍ ማደርያ ጎጆዎች፡ አይጥ እና ሳር ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል ተብሎ ይታመናል፡፡ 220 ኪሎሜትር ካሬ ስፋት ያለው የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እ.ኤ.አ በ1969 የተመሰረተ ሲሆን በ1978 ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡ ብዙ የጮህንለትና በመጨረሻም መፍትሔ ያገኘው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ እሳት ለአይጦች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ የአይጦቹ መሞት ቀይ ቀበሮዎቹን ለጊዜውም ቢሆን ምግብ ያሳጣቸዋል፡፡ የሳሮቹ መቃጠልና መውደም ጭላዳ ዝንጀሮዎቹን ለረሃብ ያጋልጣቸው ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ እሳቱ በፓርኩ ስነ ምህዳር ላይ ጉዳትን ያደርሳል፡፡ ነገር ግን የፓርኩ እሳት ያደረሰው ውድመት ‹ክቡር› በምንለው የሰው ልጅ ህይወት ላይ የከፋ ነገርን አላስከተለም፡፡ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አላለፈም፡፡ መፍራትና መጠንቀቅ ያለብን ይሄኛውን እሳት ነው፡፡ የዘረኝነቱ እሳት የሚያደርሰው ውድመት፣ ጥሎት የሚሄደው ጠባሳ ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሌም እንደሚነሳው ሩዋንዳ ጥሩ ምሳሌ ነች፡፡ የዘረኝነት እሳት ሩዋንዳውንን አቃጥሏቸዋል፡፡ ትውልድ አልቋል፡፡ በሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ እንደዋዛ ህይወቱን ተነጥቋል፡፡ እሳቱን የሚያጠፋ ሳይሆን ነዳጅ እየጨመረ የሚያባብሰው በመብዛቱ ሁለቱ ጎሳዎች ሁቱና ቱትሲዎች በዘረኝነት ተቃጥለዋል፡፡

በሩዋንዳ በከፍተኛ እብሪት እና ዘረኝነት የታወሩ ሃይሎች በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የተዘራው አሰቃቂ የዘር ቅስቀሳ፣ “እነዚህን በረሮዎች ጠርጎ ለማጥፋት የመጨረሻው ጦርነት” በማለት የተረጨው መርዝ በቱትሲዎች ላይ አሰቃቂ ዘር ማጥፋት እንዲፈፀም አድርጓል፡፡ ኢንተርሃሞይ ተብሎ በሚታወቀው በዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለብዙ ዘመናት አብረው የኖሩት ሁቱዎችና ቱትሲዎች እርስ በእርስ ተላለቁ፡፡ እናም አሁን ሩዋንዳውያን በዚያ አሳፋሪ የኋላ ቀርነት ድርጊታቸው በማፈር ይጸጸታሉ፡፡ የዘር ጉዳይ እንዲነሳባቸውም አይፈልጉም፡፡ በህግም ታግዘው ዘረኝነትን ወደጎን ገሸሽ አድርገውታል፡፡ በዘር መቧደን፣ በጎሳ መጠራት ቀርቷል፡፡

በደቡብ ሱዳንም ተመሳሳይ የጎሳ ግጭት ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ ለሰዎች እልቂትና ስደት ምክንያት ሆኗል፡፡ ዲንቃ እና ኑዌር በተባሉ ጎሳዎች መሃከል በተፈጠረው ግጭት ከ300 ሺህ ሰው በላይ ህይወቱን አጥቷል፡፡ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡

‹‹ሰው መሆን ከዘር ይቀድማል››

ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ አቶ ኦባንግ ሜቶ አንድ ጥሩ ንግግር አላቸው፡፡ እንዲህ ይላል፡- “ሰው መሆን ከዘር ይቀድማል። ስንወለድ ቋንቋ አልነበረንም። ሰው ሆነን ነው የተወለድነው። ኢትዮጵያዊነት የማይገባቸው አሉ። እንዚህ ራሳቸውን ስለማያከብሩ ሌላውንም አያከብሩም። ዘረኝነትን የሚሰብኩ ሰዎች ውስጣቸው ፍቅርና ክብር ለራሳቸው የሌላቸው ናቸው”

ዘረኝነት የሰው ልጆች ባሉበት ቦታ ሁሉ አለ፡፡ በሌሎችም ሃገራት እንደችግር ይነሳል፡፡ ለዚያም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የጸረ ዘረኝነት ቀን በየዓመቱ እንዲታሰብ የወሰነው፡፡ እኩልነትና የሰው ልጅ ክብር በሰብዓዊ መብቶች ማስከበሪያ መመሪያ ውስጥ ተዘርዝሮ ተቀምጧል፤ ይሁን እንጅ የሰብዓዊ መብት ሁሌም የመጣስ ሥጋት እንደተደቀነበት ነው የሚገኘው። በዚህም የተነሳ ነው የዓለም መንግሥታት በዘረኝነት አንፃር የሚሠራ አንድ ብሔራዊ የተግባር ዕቅድ እንዲያወጡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው። ይህን ትግሉን ለማጉላትም በያመቱ መጋቢት ሀያ አንድ ቀን የፀረ ዘረኝነት ቀን ተብሎ እንዲታሰብ ወስኗል።

እንደተባለው የዘረኝነት እሳት የሰው ልጆች ባሉበት ቦታ ሁሉ የሚነድ ቢሆንም ሌሎቹ ሃገራት በቀላሉ ያጠፉታል፡፡ ይቆጣጠሩታል፡፡ ምክንያቱም እሳቱን የሚለኩሱት ጥቂት ሰዎች ሲሆኑ ብዙሃኑ ግን እሳቱን ለማጥፋት ውሃ ሆነው ይወጣሉ፡፡ እናም የሰው ህይወት ሳይጠፋ ነገሩ ይቋጫል፡፡

ማንም ሰው ብሄር መርጦ አይወለድም፡፡ የምርጫ ጉዳይ ኣይደለም፤ የሰው ልጅ የመጣበትን ሃረግ የመወሰን ስልጣን የለውም። ለዚያም ነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የዘርና የዘር ጥላቻ በሚለው አዋጅ “ሁሉም የሰው ልጆች ዝርያቸው አንድ ሲሆን ሁሉም ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ ናቸው” ሲል ያስቀመጠው።

የራሳቸውን ወገን የተለየ አድርገው በሚያስቡ የእኛና የእነሱ ህዝቦች ብለው ለይተው መስመር የሚያበጁ የመጡበትን ወገን ከፍ አድርገው ወይም ለይተው በሚያዪ ሰዎችና ቡድኖች ምክንያት የሰው ልጅ በታሪክ የማይረሱና አሰቃቂ እልቂቶችን (Holocaust) አይቷል፡፡ ግን አሁንም ዘርን ወይም የመጡበትን አካባቢ መሰረት አድርገው ሌሎችን በተለየ መንገድ የሚመለከቱ ሰዎች አልጠፉም፡፡ ይሁን እንጅ ድርጊቱ በአብዛኞቹ የአለም ሀገራት የሚያስነቅፍና ከሰው አስተሳሰብ በታች የሚመደብ ድርጊት ነው፡፡ ነብዩ መሀመድ እንደተናገሩት ‹ዘረኝነት ጥንብ ናትና› ጥንብነቷን እያሸተተ የሚከተል ሰው የተናቀ ነው፡፡ የተዋረደ ነው፡፡

‹የዘረኝነት እሳት› በኢትዮጵያ

እሳቱ መቀጣጠል የጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ 27 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዘረኝነት ላይ የተመረኮዘው የኢህአዴግ መንግሥት ሌሎቹ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተባብረው እንዳያምፁበት ከሚጠቀምባቸው አንዱና ዋነኛው ዘይቤ የሃገሪቱን ዘውጎች በየክልላቸው አጉሮ ከፋፍሎ መግዛት ነው። ዘረኝነትን እንደቋሚ የመንግሥት ፖሊሲ አድርጎ ማስፋፋትና ዘላለማዊ ማድረግ ለገዢው መንግሥት በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ለዚህም የተቋቋሙትን የትምህርት መዋቅሮችና በጊዜው የሚሰራውን ሶሻል ሚዲያ መሳሪያዎችን ዘርግቶ ለራሱ ጥቅም ማራዘሚያ ይጠቀምባቸዋል።

ዘረኝነት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ተሰበጣጥሮ የብዙ ዘውጎች ስብስብስ ለሆነች ሐገራችን አጅግ አስቃቂ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሥልጣንን በአንድ ፓርቲ ወይም ቡድን ሥር አካብቶ ፍፁማዊ የፓርቲውን የበላይነት (hegemony) ሲፈጥር፣ የዘረኝነት ፖሊሲ ሕዝቡን በማለያየትና በማቃቃር ይህ የፓርቲ የበላይነትን ሕልውና ያረጋግጣል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለፉት ብዙ ዘመናት በተለያዩ ገዢዎች ሥር በዘውግና በቋንቋ እንዲከፋፈል ተደርጓል፤ ተገፋፍቶም እርስበርስ እንዲጠላላና እንዲገዳደል ተገዷል። አነስተኛ የመንደር ሽኩቻ ወደትልቅ ሀገር አቀፍ ጠብ ተዛምቷል። ይህ የከፋፍሎ መግዛት ሥርዓት ወደከፍተኛው ደረጃ የደረሰው ባለፉት 27 ዓመታት የኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ነው። በዚህም ምክንያት በክልልና በዘውግ እንዲከፋፈል የተደረገው ሕዝብ የድንበር ጦርነት መፍጠር፤ በክልሉ የሚኖሩትን “ሌሎች” ዘሮችንና ዘውጎችን በማጥቃትና ከኑሮዋቸው ተፈናቅለው እንዲሰደዱ ማድረግ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አሁን ለደረሱበት የዘረኝነት ተፅዕኖ ዳርጓቸዋል።

እንደ አብነት በሶማሊያ የተፈጸመው ፀረ-አማራ ጥቃት ቤተ እምነቶችን እስከማቃጠል የዘለቀ፤ በጋምቤላ የተከናወነው ጥቃትና የኦሮሞዎች መፈናቀል፤ በቤኒሻንጉል ያሉ አማሮችና ኦሮሞውች መፈናቀልና ግድያ፣ የጌዲኦዎቸ ከኦሮሚያ መፈናቀልን ማንሳት ይቻላል፡፡ በየጊዜው የሚነሱ “እኛም ክልል እንሁን” የሚሉ ዘውጎች ጥያቄም ሌላው የዘረኝነት መገለጫ ነው።

በጊዜና በትክክለኛው ዴሞክራሲያዊ ፖሊሲ ላይ ተመርኩዞ መፍትሄ ካላገኘ፤ በአንድ ፓርቲ አምባገነናዊ አገዛዝ የተዘረጋ የዘረኝነት መርሆ የሕዝብን እርስበርስ ጥላቻ ወደዘር ማጥፋት ደረጃ ሊያራምደው ይችላል። የአንድ ሕዝብ በዘር መጠላላት ወደ ዘር ማጥፋት የደረሰባቸው ሐገሮች ብዙ ናቸው። የጀርመንን፣ የሩዋንዳንና የዩጎስላቪያን ማንሳት ብቻ ይበቃል። በኢትዮጵያም ውስጥ እስካሁን የተፈፀሙት ሐገርን በዘርና በቋንቋ የመላያየትና እርስበርስ የማበጣበጥ እኩይ ተግባሮች ዘረኝነት ሥር ሰዶ እንዲንሰራፋ ብቻ ሳይሆን አንዱ ዘር ሌላውን የሚያጠፋበትን ጥርጊያ መንገድም እያዘጋጁ ነበር። በአሁኑ ሰዓት በየቦታው እየተፈፀሙ ያሉ የክልል ግጭቶች፤ ሕዝብን ከኑሮው አስፈንቅሎ ማባረር፤ በጅምላ መግደልና መገዳደል ሥር የሰደደ ዘረኝነት ፖሊሲ ውጤት ነው። ነገሩ በጊዜው ካልተቋጨ፣ እሳቱን በፍጥነት ካላጠፋነው ሁኔታው አስፈሪ ነው፡፡

ዘረኝነት ምንድነው?

ዘረኝነት አንድ ዘር ወይም ዘውግ ወይም የህዝብ ክፍል በራሱ የበላይነት አምኖ ሌላውን ዘር ወይም ዘውግ በቋንቋው በመልኩ ወይም በተለየ ዘርነቱ ከራሱ ዝቅ አድርጎ አንቋሾና አጥላልቶ የሚያይበት ርዕዮተ ዓለም ነው። በዚህም መልኩ ዘረኝነት አድልዎንና በጭፍን አግልሎ መፍረድን ያመጣል።

ዘረኝነት ሰፋ ባለው ትርጉሙና ተልእኮው ሲታይ፤ የገዢው ወይም የልሂቃኑ ክፍል ከላይ የተጠቀሱትን የዘር፣ የዘውግ፣ የቋንቋ ልዩነቶችን በመጠቀምና በመከፋፈል የራሱ ዘር ወይም ዘውግ ያልሆነውን ሕዝብ ዝቅ አድርጎ በማስቀመጥ መሠረታዊ መብታቸው የሆኑትን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ መዋቅሮች ተካፋዮችና ተጠቃሚዎች እንዳይሆኑ መንፈግ ነው። መንግስቱን የሚቆጣጠረው ዘር ቁልፍ ቁልፍ የመንግሥት መዋቅሮችን በመያዝና ለራሱ ዘር ብልፅግና እንዲውሉ በማድረግ፤ የሌላው ሕዝብ ንብረት የሆኑትን የማምረቻ መሳሪያዎችንና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለራሱ በመዝረፍ፤ እውነተኛ ባለቤቶቹ በሁሉም ዘርፍ ከራሱ ዘር ወይም ዘውግ ወይም ሕዝብ እንዲያንሱ በማድረግ የዘረኝነት መርሆውን ይተገብራል።

ሰው ዘረኝነትን ይማራል እንጂ አብሮት አይወለድም። ሰውን ዘረኝነት ከሚያስተምሩት ጥቂቶቹ፤ ዘረኛ ቤተሰብ፣ ዘረኛ አብሮ አደጎች፤ በዘርኝነት ተግባር ጥቅም ሲሆኑ ከሁሉም በላይ ዘረኝነትን ለማስፋፋት ከፍተኛ ሚና የሚጫወተው በሥልጣን ላይ ያለው ሥርዓት የሃገሩን ሕዝብ ለመለያየት ዘረኝነትን እንደመሳሪያ ለመጠቀም በትምሕርትና በመሳሰሉት የመንግሥት ተቋሞች አማካይነት ሥር እንዲሰድ ሲያደርግ ነው።

‹ብዙ ነን፣ አንድም ነን›

ባለብዙ ዘውጎችና ባሕሎች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች አብሮ ተቋቁሞ፣ ተከባብሮ ፣ተጋብቶና ተዋልዶ፤ አብሮ በልቶ፤ አብሮ ጠጥቶ፤ አብሮ ተርቦ፤ አብሮ ስቆ፤ አብሮ አልቅሶ፤ አብሮ ጨፍሮ፤ አብሮ ሞቶ፤ አብሮ ተቀብሮ፤ አብሮ ጠላትን ተጋፍጦ ደሙን አፍስሶና አሸንፎ የኖረ ሕዝብ ነው። ብዙ ሆኖም፣ አንድ ሆኖም ነው የዘለቀው፡፡

በኢትዮጵያ ባህሎች ተደበላልቀዋል፤ ቋንቋዎች ጉራማይሌ ሆነዋል፤ እምነቶችም ይፈራረቃሉ። ሆኖም ጠላቶቻችን እና ወራሪዎቻችን ልዩነቶቻችንን እንጂ አንድነታችንን ባለመገንዘብ ሊቀራመቱን ያልሞከሩበት ጊዜ የለም። እንግሊዝ ከግብጾች ጋር አብራ ያደረገችንን የአሉላ አባ ነጋ ጀግንነት ይመሰክራል። ጣሊያን በባለብዙ ዘውግ አርበኞች አባቶቻችን አድዋ ላይ ተዋርዳ የተሸነፈችበትን ቁስሏን ለአርባ ዓመታት ስታመግል ቆይታ ጊዜዋን ጠብቃ የመከፋፈልና ቀጥቅጦ የመግዛት ሕልሟን ለመተግበርና ቅኝ ለመያዝ መጥታ የአምሥት ዓመታት ሰቆቃና የዘረኝነት አረም ትታልን ተመለሰች።

ኢትዮጵያውያንን ከሁሉም በላይ ታላቅ ከሚያደርጉን ብዙ ባሕሪዎቻችን አንዱ፣ ከሌሎች ሃገሮች በዘረኝነትና በሌሎች እኩይ ተግባራት ሰቆቃ ለደረሰባቸው እጆቻችንን ዘርግተን ተቀብለን ተዋህደን አንድ ሕዝብ የመሆን ችሎታችን ነው። ከታሪክ እንደምንማረው የነብዩ መሐመድ ቤተሰብ፣ የአውሮፓ አይሁዶች፣ ግሪኮች፣ አርመኖች እና ሌሎችም በዘርም ሆነ በሌሎች እኩይ ምክንያቶች ሊያጠፉዋቸው ከሞከሩ አምባገነኖች ሸሽተው ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ መኖርያ ያገኙት ኢትዮጵያ ነው። ከግሪክ አገር የፈለሱና ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ ተቀብላቸው የራሷ ዜጎች ያደረገቻቸው የፋኑሪስ ቤተሰብ ልብ የሚነካ ታሪክ መጥቀስም ይቻላል። የፋኑሪስ ቤተሰብ ወደኢትዮጵያ የተሰደደው አባታቸው በመጀመሪያ የስደተኞች መናኸሪያ ተብላ ወደምትታወቀው አሜሪካ አገር ተሰዶ በተጓዘበት መርከብ ላይ በተላለፈበት በሽታ ምክንያት አሜሪካን እንዳይገባ ተከልክሎ ኤለስ አይላንድን ሳይረግጥ በመጣበት መርከብ ወደሐገሩ ከመለሱት በኋላ ነው።

ህግ እሳቱን ያጠፋው ይሆን?

ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ብቻ በኢትዮጵያ የተከሰቱት ነገሮች ያስደነግጣሉ፡፡ በተለያዩ በይነ መረቦችና ማህበራዊ ገፆችም ላይ የተለያዩ ማህበረሰቦችን ለጥቃት የሚያነሳሱ፣ ግድያንና መፈናቀልን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶች ተዛምተዋል። በዚህ ደግሞ ተራ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ማህበረሰቡን የሚመሩ የመብት አራማጆች ማህበረሰቡን እርስ በርስ በማጋጨት በመወቀስ ላይ ናቸው።

የመንግሥት ኅላፊዎች ንግግርም በተፈጠረው መከፋፈል ላይ ቤንዚን በእሳት ላይ እንደ ማርከፍከፍ ሆኖ ለአንዳንድ ጥላቻዎችና መፈራቀቆች መቀጣጠል ምክንያት ሆኗል። ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መልሶች በሙሉ ጥላቻንና ጥቃትን ምላሽ ያደረጉና ሃይ ባይ ያጡ መልዕክቶች ለፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት እንዳይሆኑ ያሰጋል። በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ግድያ፣ ጦርነት፣ ዘር ማጥፋት እንደተለመደ ነገር ተደርጎ መቀስቀሱ ቀጥሏል።

በዚህም ምክንያት ሀገሪቷ ውስጥ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለዋል፤ በርካቶች ለሞት ሲዳረጉ እንዲሁም ለብዙዎች በስጋት ውስጥ ለመኖር ምክንያት ሆኗል። የተለያዩ ሰብአዊ መብት ድርጅቶችና እንዲሁም የጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥናት እንደሚያሳየው ለዚህ ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የጥላቻ ንግግር ነው። ዘርን መሰረት ያደረገ መሆኑ ደግሞ ነገሩን ያባብሰዋል፡፡ በቅርቡ ታዲያ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል ያስችላል በሚል ረቂቅ አዋጅ ወጥቷል።

ረቂቅ አዋጁ የጥላቻ ንግግር ትርጉም ብሎ ሲያስቀምጥ “ሆን ብሎ የሌላ ግለሰብን፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን አካል ጉዳኝነትን ዜግነትን፣ ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጫዊ ገፅታን መሰረት በማድረግ ሆነ ብሎ እኩይ አድርጎ የሚስል የሚያንኳስስ፣ የሚያስፈራራ፣ መድልዎ እንዲፈፀም፣ ወይም ጥቃት እንዲፈፀም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልዕክቶችን በመናገር፣ ፅሁፍ በመፃፍ፤ በኪነ ጥበብ እና እደ ጥበብ፣ የድምፅ ቅጂ ወይም ቪዲዮ፣ መልእክቶችን ብሮድካስት ማድረግ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨትን ይመለከታል።”

ከዚህም በተጨማሪ ረቂቅ ሕጉ የሐሰት መረጃን በተመለከተም “የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው፤ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልፅ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ መረጃን ሆን ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ” እንደሆነ አስቀምጧል ።

እነዚህን ድርጊቶች የፈጸመ ሰው በህጉ በተቀመጠው አግባብ መሰረትም በእስራትና በገንዘብ መዋጮ እንደሚቀጣ አስቀምጧል። ምንም እንኳን የጥላቻ ንግግር አደገኛነት ሳይታለም የተፈታ ነው ቢባልም መፍትሄው አዲስ ህግ ማውጣት ነው ወይ? በማለት ጥያቄዎችን የሚያነሱ አሉ፡፡

በመጨረሻም

ለዚህ ጽሁፍ ማጠቃለያ እንዲሆን አንድ ታሪክ እነሆ፡፡ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም ዘረኝነትን አስመልክቶ ባሰፈሩት ጽሁፍ ላይ ጠቅሰውት ያነበብኩት ነው፡፡ ስለአንድ ብልህ ሽማግሌ እና ስለአንድ አጭበርባሪ ልጅ የሚያወሳ ታሪክ ነው፡፡ አጭበርባሪው ልጅ ሽማግሌው ምን ያህል ሞኝ እንደሆኑ ለማሳየት ዕቅድ ነበረው፡፡ አጭበርባሪው ልጅ ከጫካ ውስጥ አንዲት ወፍ ያዘ፡፡ እርሷንም በእጆቹ ያዛት፡፡ የትንሿ ወፍ ጅራት ከጁ አልፋ ትታይ ነበር፡፡ በእጆቹ ላይ ያለችው ወፍ በህይወት ነበረች፡፡ ዕቅዱ እንዲህ የሚል ነበር፡ ወደ ሽማግሌው እያመላከተ “ሽማግሌው በእጆቼ  ላይ ምንድን ነው ያለው?“ ሽማግሌው ሰው እንዲህ አሉ፣ “ልጄ ወፍ ይዘሀል“ ከዚያም ልጁ እንዲህ ይላል፣ “ሽማግሌው ወፏ በህይወት አለች ወይስ በህይወት የለችም?“ ሽማግሌው ወፏ በህይወት የለችም ሞታለች የሚል መልስ የሚሰጡ ከሆነ ልጁ እጆቹን ግራና ቀኝ በመክፈት ወፏ በነጻነት እንድትበር ሆኖ በዛፍ ላይ ታርፍ እና በደስታ መኖር ትጀምራለች፡፡ ሆኖም ግን ሽማግሌው ሰው ወፏ በህይወት አለች የሚል መልስ የሚሰጡ ከሆነ አጭበርባሪው ልጅ በእጆቹ መካከል ወፏን አጣብቆ እና ደፍጥጦ እንድትሞት በማድረግ “ሽማግሌው ይመልከቱ ወፏ ሞታለች“ ይላል፡፡  እቅዱ ይህ ነበር፡፡

ሽማግሌው ይህን ተረድተዋል፡፡ አጭር መልስ ነው የሰጡት፡፡ “ልጄ ወፏ በእጅህ ላይ ናት“ የሚል፡፡ ኢትዮጵያም በእጃችን ላይ ናት፡፡ የሚቀጣጠለውን የዘረኝነት እሳት ማጥፋት ወይም ይበልጥ እንዲቀጣጠል ነዳጅ ማርከፍከፍ እንችላለን፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe