የዘንድሮ ምርጫ ለአስፈጻሚዎች ብቻ ሁለት ቢሊዮን ብር ያስወጣል

በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተራዘመውና ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲደረግ ቀን የተቆረጠለት የዘንድሮ አጠቃላይ ምርጫ፣ በ49,407 የምርጫ ጣቢያዎች ለሚሠማሩ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ሁለት ቢሊዮን ብር ገደማ እንደሚወጣ ታወቀ፡፡ ለዘንድሮ ምርጫ በጠቅላላ 152,201 የምርጫ አስፈጻሚዎች ሲኖሩ፣ 150,000ዎቹ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ሲሆኑ፣ የተቀሩት 2,201 የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎችና የዞን አስተባባሪዎች ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ለ150,000 አስፈጻሚዎች ለእያንዳንዳቸው በቀን 200 ብር አበል የሚከፈላቸው ሲሆን፣ የሚቀጠሩትም ለሁለት ወራት ይሆናል፡፡ ስለዚህም ምርጫ ቦርድ ለእነዚህ አስፈጻሚዎች 1.8 ቢሊዮን ብር ይከፍላል፡፡ የተቀሩት 182 የዞን አስተባባሪዎችና 2,019 የምርጫ ክልል አስተባባሪዎች፣ እያንዳንዳቸው በቀን 400 ብር አበል የሚከፈላቸው ሲሆን፣ ለአራት ወራት ይቀጠራሉ፡፡ ምርጫ ቦርድ ለ2,201 አስፈጻሚዎችና አስተባባሪዎች 105,648,000 ብር ይከፍላል፡፡

ስለዚህ ለዘንድሮ አጠቃላይ ምርጫ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድምሩ 1,905,648,000 ብር ያወጣል፡፡ ይኼም ክፍያ ከአሁን ቀደም ለምርጫ አስፈጻሚዎች በጠቅላላው ይከፈላቸው ከነበረው 600 ብር ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ነው፡፡

ይሁንና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫው ከመራዘሙ አስቀድሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ3.7 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ ያቀረበው ቦርዱ፣ የፀደቀለት 2.5 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫው ከተራዘመ በኋላ ደግሞ ቦርዱ የ1.1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ጠይቆ ነበር፡፡ ይሁንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዚህ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡

ስለዚህም ቦርዱ ከፀደቀለት በጀት በርካታውን ለዚህ ተግባር የሚያውል ሲሆን፣ ሌላው ከፍተኛ ወጪው ደግሞ ለድምፅ መስጫ ወረቀት ኅትመት ይሆናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በዓይነት የ40,004,000 ዶላር ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፣ የዚህም ዓላማ ቦርዱን ብቁ፣ ግልጽና የሚታመን ተቋም ለማድረግና አካታች፣ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ማድረግ እንዲችል ለማገዝ ነው፡፡

ለዘንድሮ ምርጫ ለክልልና ለፌዴራል ምክር ቤቶች በ673 የምርጫ ክልሎች 8,209 ዕጩዎች የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በተጨማሪም 125 የግል ዕጩዎች ለተለያዩ ምክር ቤቶች ይወዳደራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም የምርጫ ክልሎች 2,432 ዕጩዎችን አቅርቦ የሚወዳደር ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) በ370 የምርጫ ክልሎች 1,385 ዕጩዎችን በማቅረብ በሁለተኝነት ይከተላል፡፡ እናት ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የሲዳማ አንድነት ፓርቲ፣ እንዲሁም ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በቅደም ተከተል በርካታ ዕጩዎችን በማቅረብ ከአንድ እስከ አሥር ያለውን ደረጃ ይይዛሉ፡፡

ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጠናቀቀውን የዕጩዎች ምዝገባ አስመልከቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ አጠቃላይ ሒደቱ መልካም የሚባል ቢሆንም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የዕጩዎች መታሰርና የተወሰኑ ፓርቲዎች አባላትን ላለመመዝገብ እንቢተኝነት እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ለምርጫ ዕጩ ሆነው የሚወዳደሩ ግለሰቦች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ያላቸው ዓይነት ያለመታሰር የሕግ ጥበቃ ያላቸው በመሆኑ፣ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ እስካልተያዙ ድረስ መታሰር የለባቸውም ሲሉም አስረግጠዋል፡፡

ይሁንና በተለይ በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች ከዘገዩ የዕጩዎች ምዝገባ በስተቀር፣ የሁሉም ፓርቲዎች ጥያቄዎች መፍትሔ ተሰጥቷቸው ዕጩዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡

Kumneger Media
Kumneger Media
Kumneger Media is a News and Entertainment Website & Channel. Kumneger Media in addition to News and Entertainment it is the hub of Politics, Movies, Drama, Music, Comedy, Documentary and More!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe