የዝሆኖቹ ፍልሚያ የት ድረስ ይዘልቃል?

ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መወዛገብ የጀመሩት አሁን አይደለም፡፡ ከኦሎምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚዎች ምርጫ ጋር ተያይዞ ዘንድሮ በእጅጉ ተካርሮ እና በተቃውሞ ሰልፍ፣ በፖሊስ አጀብ፣ በጋዜጣዊ መግለጫና በብዙ ግርግሮች ታጀበ እንጂ ከዚህ ቀደምም የሁለቱ ስፖርት ተቋማት ውዝግብ አደባባይ ላይ ታይቷል፡፡ ደጅ ወጥቶ እንደ አራስ ህጻን ፀሐይ ሲሞቅ ነበር፡፡ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ሲል ከርሞ በመጨረሻ እስከ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ድረስ ጉዳዩ እስኪታወቅ ዘልቋል፡፡ ከድብብቆሽ ምርጫ እስከ አደባባይ ሰልፍ ድረስ አስመልክቶናል፡፡

ሁኔታው ብዙ ኢትዮጵያውያንን በተለያየ መንገድ ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሊካሄድ ጥቂት ወራት ብቻ በቀሩበት በዚህ ወቅት ውዝግብ ውስጥ መግባት በስፖርተኞቹ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ጫና ውጤታችንን ያበላሸዋል በሚል የሰጉ አሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ውዝግቡ ጭራሽ ከተሳትፎም እንዳያስቀረን በአስቸኳይ መላ ይፈለግለት ሲሉ የተደመጡም ነበሩ፡፡

<45 ከመቶ መራጮች የመረጃ ምንጫቸው ቴሌቪዥን መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ …>

ከድብብቆሽ ምርጫ እስከ አደባባይ ሰልፍ

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ተቋሙን የሚመሩ ስራ አስፈጻሚዎችን ለመምረጥ ጉባኤውን በባህርዳር ከተማ መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም ለማድረግ መዘጋጀቱ ተሰማ፡፡ ይሁን እንጂ በመጨረሻ የጉባኤው ቀን ባለበት ሆኖ ቦታው ግን እንደተቀየረ ታወቀ፡፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተናጋጅነት በሀዋሳ ከተማ ሊከናወን መሆኑን ኮሚቴውም በማህበራዊ ገጹ አስታወቀ፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎችና ጋዜጠኞች ወደስፍራው አመሩ፡፡ በኦሎምፒክ ስፖርት የኢትዮጵያ የሜዳሊያ ምንጭ የሆነው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወደስፍራው አንድም ተወካይ ሳይልክ ቀረ፡፡ እንዲያውም በዚያው ዕለት የባርሴሎና ኦሎምፒክ ባለድሏ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የምትመሰገንበት ትልቅ ድግስ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል መዘጋጀቱን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ በሀዋሳ ጉባኤው ህገ ወጥ ነው በሚል በፖሊሶች አማካኝነት እንዳይካሄድ ተከለከለ፡፡ አዲስ አበባ የባርሴሎናዋ ኮከብ ደራርቱ ቱሉ ተሸለመች፤ ተወደሰች፡፡

በቀጣዩ ቀን ማለትም ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም በማለዳ በዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የሚመራው ኦሎምፒክ ኮሚቴ የጉባኤውን ተሳታፊዎች በአንድ አውሮፕላን ሰብስቦ ወደአዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ ከዚያም ወሎ ሰፈር በሚገኘው የተቋሙ ግቢ ድንኳን በመጣል ምርጫው እንዲካሄድ ተደረገ፡፡

ጥቂት ሰዓታትን ቆይቶ አካባቢው የሰልፍ ግርግር ሊያስተናግድ ግድ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ለቶኪዮ ኦሎምፒክ በዝግጅት ላይ ያሉ አትሌቶች በኮሚቴው በር ላይ ተገኝተው ምርጫውን ተቋወሙ፡፡ ሁኔታው ያልተለመደ በመሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቃውሞ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቀጣዩ ቀን ከሰዓት በኋላ በኔክሰስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለይ በብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ላይ ያለውን ተቃውሞ በዝርዝር አንስቷል፡፡

<ይልቅ ወሬ ልንገርህ:- ስለ ታማኝ በየነ ‹ሿ ሿ›>

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማደር ደራርቱ ቱሉ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ ሌሎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የህክምና ቡድን አባላት፣ አሰልጣኞች አትሌቶች እና ሌሎች የቴክኒን ሰዎችም በተገኙበት እና ሶስት ሰዓታን በፈጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሚከተሉት ዋናዋና ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትም ሆኑ ሌሎቹ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አሁን በግልጽ ወደ ግጪት ያስገቧቸውን እና ከህግ እና አሰራር ውጭ ተፈጸሙ ያሏቸውን ህጸጾች አንድ በአንድ አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንን መምረጥ ማሰልጠን እና ለውድድር የማዘጀት ሀላፊነት በግልጽ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ሆኖ ሳለ፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ከተሰጠው ስልጣን እና ሀላፊነት ውጭ በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ጣልቃ በመግባት የቡድኑን ዝግጅት እና የአንድነት መንፈስ እንዲረበሽ አድርጓል፡፡

ከአምአቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያልተላለፉ መመሪያዎችን እንደተላለፉ በማስመሰል ፌዴሬሽኑ ተረጋግቶ በእቅዱ መሰረት ዝግጅቱን እንዳይሰራ እና አትሌቶቹም እንዲረበሹ አድርጓል፡፡ ለአብነትም ከመሬት ተነስቶ የማራቶን ተሳታፊዎች የመጨረሻ ዝርዝርን በቶሎ አስገቡ ተብላችኋል በማለት፣ አትሌቶቻችን ሳይዘጋጁ ወደ ውድድር ልንገባ ነው በሚል ስሜት አላስፈላጊ መረበሽ እንዲፈጠርባቸው አድርጓል፡፡

ኮሚቴው ላለፉት አራት ወራት አትሌቶቻችን ላረፉባቸው ሆቴሎች ምንም አይነት ክፍያ ባለፈጸሙ እና ለአትሌቶቻችንም በቂ የልምምድ መስሪያ አቅርቦቶችን ባለማሟላቱ ፌዴሬሽኑ ለሆቴሎቹ የመተማማኛ ቃል በመግባት፡ ከነገ ጀምሮ የተሻለ ዝግጅት ወደሚያደርጉበት ሆቴል በራሱ ውሳኔ እንዲዛወሩ ለማድረግ መገደዱ

ላለፉት አራት ወራት ለአትሌቶች እና አሰልጣኞች መከፈል የነበረበት የውሎ አበል ክፍያን ኦሊምፒክ ኮሚቴው መክፈል ባለመቻሉ ፌዴሬሽኑ 3.5ሚ (ሶስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ) ብር ለመክፈል ተገዷል፡፡ እነዚህ እና ሌሎች በኦሊምፒክ ኮሚቴው በዝግጂቱ ወቅት መሟላት የሚገባቸው ነገሮች መጓደል በአትሌቶቹ እና አሰልጣኞቹ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ሄዶ ሄዶ ሀገርን ዋጋ ከማስከፈሉ በፊት ፌዴሬሽኑ ሀላፊነት ስለሚሰማው በጊዜ ለማስተካካል ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ሀላፊዎች ከዝግጅቱ ጋር በተያያዘ ከተፈጠሩት እክሎች ባለፈ ከኦሊምፒክ ኮሚቴው እና በተለይም ከፕሬዝዳንቱ ጋር ያላግባቧቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴው በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ሰባት ጠቅላላ ጉባኤዎችን ያካሄደ ሲሆን ከመጀመሪያው ጉባኤ ውጭ አብዛኞቹ ወጪ ከማባከን ያለፈ ትረጉም የሌላቸው እና መደበኛ የጠቅላላ ጉባኤ አጠራር እና አካሄድን ያልተከተሉ በጥቅሉ ህጋዊ ያልሆኑ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌም፡ የጉባኤው አጀንዳዎች በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያልተመከረባቸው ነበሩ፣ አጀንዳዎቹ ህጉ እንደሚያዘው ቀደም ብለው ለጉባኤው አባላት ተልከው አያውቁም ወዘተ…

የብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሀፊ በጠቅላላ ጉባኤው ወይንም በግልፅ የስራ ቅጥር ማስታወቂያ ተወዳድሮ መሾም/መቀጠር ሲገባው፡ ከሁለቱም ውጭ በፕሬዝዳንቱ የግል ውሳኔ ብቻ በሀላፊነት መቀመጣቸው፤የብሄራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ዓቃቤ ነዋይም እንዲሁ በፕሬዝዳንቱ የግል ምርጫ ሀላፊነት ላይ መቀመጣቸው እና ከላይ የተጠቀሱት ሀላፊነቶች ደግሞ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በመሆን በተቋሙ ሂሳብ ላይ ቼክ ፈራሚዎች መሆናቸው፣ በተቋሙ ውስጥ ላለው አላስፈላጊ የገንዘብ ብክነት አስተዋጽኦ ስለሚኖረ፤

<አየለ ማሞ (ማንዶሊን) በቀን አንድ ግጥም ወይም ዜማ ሳይሰራ ውሎ…>

በዚህ አመት ታህሳስ ወር ላይ በሀዋሳ በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የኦሊምፒክ ኮሚቴ የአስፈጻሚ አካላት ምርጫን በሚቀጥለው አመት ከኦሊምፒክ ውድድሩ በኋላ ለማድረግ እና አሁን ሙሉ ትኩረታችን ለውድድሩ ዝግጂት እናድርግ ተብሎ ከተስማማን በኋላ ምርጫው በአስቸኳይ እንዲደረግ የተወሰነበት ምክንያት አሳማኝ ባለመሆኑ፤

በቅርቡ ሊካሄድ ለተሳበው ምርጫ እጩ ለማቅረብ ተብለው የቀረቡት መስፈርቶች ከኦሊምፒክ መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ ጋር የሚጋጩ በመሆናቸው፤እንዲሁም በአጠቃላይ በኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዝዳነት እየተተገበረ ባለው የምን ታመጣላችሁ እና አምባገነናዊ አካሄድ መማረራቸውን ገልጸዋል፡፡በመሆኑም የፌዴሬሽኑ መሪዎች እነዚህን እና ሌሎቹንም ቅሬታዎቻቸውን በመዘርዘር ለአለምአቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለአለም አትሌቲክስ እና ሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የከረመ ውዝግብ

የኢትጵያን ስፖርት በቅርበት ለሚከታተል ማንኛውም ግለሰብ በቀላሉ የሚረዳወ ነገር ቢኖር፡ በሁለቱ ተቋማት እና መሪዎቻቸው መካከል ያለው አለመግባባት ዛሬ ያልተፈጠረና በቶሎ የሚፈታ አለመሆኑን ነው፡፡የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 44ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በደብረብርሃን ጌትቫ ሆቴል ያካሄደው 2011 ዓ.ም ነበር፡፡ በጊዜው በጉባኤው አዘገጃጀት እና አጠራር ሂደት ላይ ቅሬታ ያላቸው እንደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያሉ የጉባኤው አባላት ቅሬታቸውን በጉልህ አንጸባርቀዋል፡፡

በወቅቱ የፌዴሬሽኑ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት እና የኦሎምፒክ ኮሚቴው ስራ አስፈጻሚ አባል የነበረችው ደራርቱ ቱሉ፡ በእለቱ ለጉባኤው አባላት የቀረቡት የ2011 ዓ.ም  የስራ አፈጻጸም፣ የ2012 ዓ.ም የባጀት እና የስራ እቅድ ሪፖርቶች በሙሉ፡ በስራ አስፈጻሚው አባላት ምንም አይነት ግምገማ ያልተካሄደባቸው እና ለእርሷም እንደስራ አስፈጻሚ አባልነቷ የጉባኤው ጥሪ ያልደረሳት መሆኑን ገልጻ በእነዚህ ምክንያቶች ራሷን ከስራ አስፈጻሚነቷ ማግለሏን በጉባኤው ፊት አስታውቃለች፡፡

ጉባኤው በውሳኔዋ ያልተስማማ ሲሆን፡ የጉባኤው ሰብሳቢ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ካለ ደራርቱ ኦሎምፒክ አይታሰብም የቤት ስራውን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ይወስዳል እናግባባታለን በሚል ጉባኤውን አረጋግተዋል፡፡

“ከጉባኤው አባላት እና ከልዩልዩ ወገኖች ውሳኔየን እንድቀለብሰው በቀረበልኝ ተደጋጋሚ ጥያቄ መሠረት ኦሊምፒክ ኮሚቴው ያሉበትን የአሰራር ችግሮች የሚቀርፍ ከሆነ ብቻ፡ ስፖርቱን ለማገልገል ስል በድጋሚ በሀላፊነት ለመቆየት ወስኛለሁ” በማለት ገልጻ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በበኩላቸው በመመሪያው መሠረት የጉባኤው አጀንዳዎች፡  ከአንድ ወር በፊት ባለመላካቸው ሪፖርቶቹንም ሆነ እቅዶቹን በደምብ እንዳልተመለከቷቸው፡ በተጨማሪም ጽ/ቤታቸው ለጉባኤው ይፋዊ ጥሪ እንዳልደረሰው በመግለጽ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

በአሸብር ወልደጊዮርጊስ የሚመራው ኮሚቴው በጊዜው ያሳተመው መጽሔትም ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የኦሎምፒክ ኮሚቴው አባላት ፎቶ በመጽሔቱ ላይ ሲታተም የደራርቱ ምስል ተቆርጦ ወጥቶ ነበር።

ኮሮና ተኮር ጠብ

ኮሮና በገባ ሰሞን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚ አባላት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ (ኮሎኔል) እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር) እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ በጃፓን መዲና ቶኪዮ አምና ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን በተመለከተ ሁለቱ የሃገሪቱ የስፖርት ተቋማት ለሁለት ተከፍለው ሲወዛገቡ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) የቶኪዮ ኦሎምፒክ በእርግጠኝነት እንደሚካሄድ እና ለዚህም አሰልጣኞች ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በዓለም ከፍተኛ የጤና ሥጋት የሆነው የኮሮና ቫይረስን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አብዛኞቹ ውድድሮች በመሰረዛቸው አትሌቶች ዕድል አግኝተው ብሔራዊ ቡድን ላይ ያተኩራሉም ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ “በመጪው የሐምሌ ወር ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት አትሌቶች ሆቴል ገብተው መሰልጠን አለባቸው” ሲሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ደራርቱ ቱሉ ደግሞ “ከ100 በላይ አትሌቶቻችን በአንድ ሆቴል መግባት የለባቸውም” በሚል ሀሳቡን ተቃውማለች፡፡

ኮሎኔል ደራርቱ “የአትሌቶቹ ዝግጅት አካላዊ ንክኪ የበዛበት ነው፤ በዝግጅት፣ በምግብና በአውቶብስ እንቅስቃሴ ወቅትም ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነታቸው የበዛ ነውም” ብላለች፡፡ “የኦሎምፒክ ኮሚቴው ሎጅስቲክስ ይመለከተዋል እንጂ እንደዚህ አይነት ውሳኔ መስጠት አይችልም፤ አትሌቶቹ ልጆቼ ናቸው፤ ባሉበት ልምምድ መስራታቸውን ይቀጥላሉ፤ እኔ የተቋም መሪ ነኝ እንጂ አሻንጉሊት አይደለሁም” ስትልም ኮሎኔል ደራርቱ ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር አያሌው ጥላሁን “በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም ውድድሮችን ዘግቷል፣ እኔም ብሆን ስለ ውድድር ከማውራቴ በፊት ስለ ኮሮና ነው ማወራው፣ በመሆኑም አትሌቶች በአንድ ላይ ሆነው ሆቴል መግባት የለባቸውም” ብለዋል፡፡

በጊዜው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን “አትሌቶች አንድ ሆቴል ይቀመጡና ልምምድ ይስሩ ማለት ለኮቪዲ 19 ቫይረስ ተጋላጭ መሆን ነው የሚል አቋም የያዘ ሲሆን፣ ኮሚቴው (የቶኪዮ ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ) አትሌቶቹ አንድ ላይ ቢሆኑ ለጤናቸው የበለጠ ጥሩ ነው ብሏል፡፡

አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴን እና አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማሪያምን በአባልነት ያካተተው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ አትሌቶቹ ሆቴል ገብተው መሰባሰብ አለባቸው ብለዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት እሰጥ አገባ ውስጥ በገቡበት በዚያወቅት የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ የቶኪዮ ኦሎምፒክ እንዲራዘም ጥያቄ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የኋላ ኋላ ደግሞ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የቶኪዮ ኦሎምፒክን በአንድ ዓመት ማራዘሙን አስታወቀ፡፡

ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ጋር በተያያዘ ውዝግብ መከሰቱ ሲነገር ቆይቶ ሰኞ ዕለት በኮሚቴው ጽህፈት ቤት ውስጥ ተካሄደ የተባለን ስብሰባ ተከትሎ በአካባቢው ተቃውሞ እንደነበር ተሰምቷል።

የኮሚቴው የምርጫ ውጤት

ኦሊምፒክ ኮሚቴ በግቢው ውስጥ ድንኳን ዘርግቶ ምርጫውን ካካሄደ በኋላ ከአትሌቲከስ ፌዴሬሽን የተቃውሞ ሰልፍ በተጨማሪ ሌሎች እርምጃዎችም ነበሩ፡፡ የኮሚቴው አመራሮች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ተስምቷል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም መጋቢት 20/2013 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለማድረግ ከተገኘበት አቢጃ ኮትዲቯር ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ፤ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውክልና ሳይሰጣቸው ጉባኤው ላይ የተገኙ ስራ አስፈጻሚዎቹን አግዷል፡፡

ይሄ ሁሉ ሆኖ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በፌስቡክ ገጹ ላይ ኮሚቴውን ለቀጣይ አራት ዓመታት እንዲመሩ ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በፕሬዝደንትነት፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ በተቀዳሚ ም/ፕሬዝደንት፣ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በምክትል ፕሬዝደንትነት መመረጣቸውን አስፍሯል። ለአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚዎቹ ዝርዝር መላኩንም የሚያሳይ ደብዳቤ ተለጥፎ ነበር፡፡

ከዚያም በኋላ ኮሚቴው በፌስቡክ ገጹ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ብርሃኔ አደሬ ከነዶር አሸብር ጋር በአንድ ጠረጴዛ ከበው ተቀምጠው የሚያሳይ ፎቶ እንዲህ ከሚል ጽሁፍ ጋር ለጥፎ ነበር፡- ‹‹አዲሱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራአስፈፃሚ በቀጣይ ስራዎች ላይ መከረ። የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ  አዲሱ የስራአስኪያጅ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ የተለያዩ ጉዳዮችን አንስቷል። በቀጣይም የሚሰሩ ስራዎች ላይም በሰፊው  የመከረ ሲሆን  የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ  ልዩ ትኩረት እደሚያስፈልገው እና በሙሉ አቅም ከወዲሁ ለመስራት ተስማምቷል።››

ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ፎቶው ተነስቶ በኮሚቴው አርማ የተተካ ሲሆን ጽሑፉን ግን አሁንም በዚያው ሁኔታ ይነበባል፡፡

የሁለቱ አትሌቶች በምርጫው ውስጥ መካተትን በተመለከተ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ ሂደቱ ሕጋዊ መስመርንና አሰራርን ያልተከተለ ነው በማለት ተቃውሞታል። ፌዴሬሽኑ በመግለጫው ላይ የኃይሌ ገብረሥላሴና የብርሃኔ አደሬ በኦሎምፒክ ኮሚቴው ከፍተኛ አመራርነት ውስጥ መግባታቸው ለአገር ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንፃር ተገቢ መሆኑን ጠቅሶ፤ ነገር ግን “በማኅበር ወይም በፌዴሬሽን የተወከሉ ባለመሆናቸው ህጋዊ መስመሩን ያልተከተለ ነው” ብሏል።

የአሁኑ ውዝግብ መነሻ የሆነው ከዚህ ቀደም አዲስ አመራሮችን መሰየምን በተመለከተ በኮሚቴው የተሰጠው ውሳኔ ባላከበረ ሁኔታ ምርጫ እንዲካሄድ መደረጉ እንደሆነ ይነገራል። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባወጣው መግለጫ ላይ እንደሰፈረው ከዚህ ቀደም በታኅሣሥ ወር ሐዋሳ ላይ በተደረገ ጉባኤ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ማግስት በመስከረም 2014 ዓ.ም ላይ እንዲደረግ መወሰኑን በማስታወስ፣ ይህንን የጣሰ ተግባር በኮሚቴው መፈፀሙን የፌዴሬሽኑ አመራሮች ይናገራሉ።

በመጨረሻም

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ጃፓን ቶኪዮ ውስጥ እንዲካሄድ ታቅዶ የነበረው የ2020 የኦሊምፒክ ውድድር በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በዚህ ዓመት ማብቂያ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያም በሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ በሚካሄደው የዓለማችን ትልቁ የስፖርት ውድድር ላይ የምትሳታፍ ሲሆን፤ ነገር ግን ይህ በኦሊምፒክ ኮሚቴውና በፌዴሬሽኖች እንዲሁም በማኅበራት መካከል የተከሰተው ውዝግብ በቶሎ መፍትሔ ካላገኘ በአገሪቱ ተሳትፎ ላይ ምን ውጤት እንደሚኖረው ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

የዝሆኖች ጠብ ለሳሩ ይተርፋል እንደሚባለው በመጨረሻ ውዝግቡ ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞችን እንዳይጎዳ አስቸኳይ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡ ኦሎምፒክ በሚካሄድባቸው ዓመታት ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን፤ ከአትሌቶች፤ ከአሰልጣኞች  እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ አጀንዳዎች መወዛገቡ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ላይ ተፅእኖዎችን እንደሚፈጥር ይታወቃል፡፡ በኦሎምፒክ በመሳተፍ ራሳቸውንና አገራቸውን ለማስጠራት ፍላጎት ያላቸው  አትሌቶችና አሰልጣኞች በእነዚህ ውዝግቦች ፈታኝ ሁኔታዎች ይገባሉ፡፡  የኦሎምፒክ ዝግጅታቸውንም በሙሉ ልብ እንዳያከናውኑም ያደርጋቸዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትስስር ይፍጠሩ

325,851FansLike
49,039FollowersFollow
13,194SubscribersSubscribe