የየመን ሃውቲ ሃይሎች በቀይ ባህር እና ኤደን ባህረ ሰላጤ የፈጠሩት የጸጥታ ስጋት በሞንባሳ በኩል የሚደረገው የኢትዮጵያ ገቢ/ወጪ ጭነት እንዲጨምር ማድረጉ ተሰማ!
ይሁን እና በመኪኖች እንቅስቃሴ ረገድ በሁለቱ አገራት ማለትም በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል ወጥ የሆነ ስምምነት የሌለ በመሆኑ በስራ ላይ ጫና እየፈጠረ ነው ተብሏል፡፡በቀይ ባህር እና ኤደን ባህረ ሰላጤ የውሃ መስመር በተፈጠረው የደህንነት ስጋት የመርከብ ድርጅቶች አካባቢው ላይ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንሱ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ለኢትዮጵያ ዋነኛ የወደብ መዳረሻ ለሆነችው ጅቡቲ በገቢዋ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በተመሳሳይ ይህንኑ መስመር ተከትለው የሚገቡ የኢትዮጵያ ጭነቶችም የመዘግየት ሁኔታ እንዳለባቸው ነው ዘርፉን የሚከታተሉ የሚገልፁት፡፡በመሆኑም አንዳንድ የኢኮኖሚ አከናዋኞች በተለይም በኢንደስትሪ ፓርኮች የሚገኙ አምራቾች ጥሬ እቃ ማስገባትም ሆነ ምርት ለማውጣት በአማርጭነት በህንድ ውቅያኖስ ላይ የሚገኘውን የኬንያ ሞንባሳ ወደብ እየተጠቀሙ መሆኑ ታውቋል፡፡
በዚሁ ወደብ እየሰፋ ባለው እንቅስቃሴ ዛሬ ላይ በሳምንት እስከ 15 ተሸከርካሪዎች ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ እያስገቡ ወይም እያስወጡ እንደሚገኙ ነው ለካፒታል መረጃ ያጋሩ የጭነት አስተላላፊዎች የገለፁት፡፡ምንም እንኳ ከመሃል አገር ወደ ሞንባሳ የሚደረገው እንቅስቃሴ በርቀት የተነሳ ከጅቡቲ አንፃር እስከ 80 በመቶ የወጪ ጭማሪ ያለበት ቢሆንም ስራን ከማቆም ትርፍን በመቀነስ አምራቾች የሞንባሳ ወደብን በመጠቀም ስራቸውን መቀጠል መርጠዋል የሚሉት የእቃ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች የተጠቃሚነት መጠኑ እየጨመረ እንደሚመጣ ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡

