የጁንታው አባላት ጨካኝና ሲበዛ ፈሪ መሆናቸውን በድርጊቶቻቸው ማረጋገጥ መቻላቸውን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ አስታወቁ። የህውሓት ጁንታ አባላት ሲፈጽሙት በነበረው ግፍና በደልም ሲገረፉ የሞቱ፤ አካላቸው የጎደለ፤ የአእምሮ በሽተኞች የሆኑ መኖራቸውን አመለከቱ ።
አቶ ማሙሸት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ የህውሓት ጁንታ አባላት ኢትዮጵያውያን ላይ የሰሩት በደልና ግፍ እንዲሁም የራሳቸውን ምቾት ለማስቀጠል ሲሉ በጭካኔ መስዋዕት ያደረጓቸውን ወጣቶች ለተመለከተ ጭካኔቸው ጥግ የደረሰ መሆኑን ለመረዳት አይከብደውም። በዚያው ልክ የራሳቸው ህይወት የሚያሳሳቸው ፈሪዎች መሆናቸውን ደግሞ ሰሞኑን በገሃድ እየታየ ነው።
የህውሓት ጁንታ 30 ዓመት ሙሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በደል ሲፈጽም ኖሯል ያሉት አቶ ማሙሸት፣ ብሄርን ከብሄር ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ሀገር እንድትፈርስና የንጹህን ዜጎችም ደም በከንቱ እንዲፈስ ሲያደርግ መቆየቱንም አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም በጉራፈርዳ፤ በሶማሌ፤ በጋምቤላ፤ በመተከል በአጠቃለይ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የቡድኑ አባላት በሚፈጥሩት ሴራ የንጹሃን ዜጎች ህይወት እንዲቀጠፍና ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሲሆኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።
በጁንታው ቡድን ከተሰቃዩትና በደል ከደረሰባቸው ሰዎች ከመጀመርያዎቹ ተርታ እሰለፋለሁ ያሉት አቶ ማሙሸት፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በስቃይና በእስር እንዲኖሩ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።
“በአጠቃላይ ለ12 ዓመታት ያህል እስር ቤት የቆየሁ ሰው በመሆኔ እስረኛ ላይ ሲፈጸም የነበረው በደልና ግፍ ሁሉ ተፈጽሞብኛል። በታሰርኩባቸው ዓመታት ኢትዮጵያዊ ሆኖ በኢትዮጵያውያን ላይ፣ ሰው ሆኖ በሰው ላይ ይፈጸማሉ ተብለው የማይገመቱ ግፎች ደርሰውብኛል፤ በሌሎችም ላይ ሲደርስ አይቻለሁ” ብለዋል።
አቶ ማሙሸት እንደገለጹት፣ የህውሓት ጁንታ አባላት ሲፈጽሙት በነበረው ግፍና በደልም ሲገረፉ የሞቱ፤አካላቸው የጎደለ፤ በሚደርስባቸው እንግልት እራሳቸውን የሚስቱ፤ የአእምሮ በሽተኞች የሆኑ ፤የኤች አይቪ ቫይረስ በመርፌ የተሰጣቸውና ቶርች ተገልብጠው ነርቫቸው የተነካ ሰዎች በርካታ ናቸው። በአጠቃላይ ዓለም ያለ ግፍ ሁሉ በማአዕከላዊ እስር ቤት ተፈጽሟል።
የጁንታው አባላት በጀግናው የመከካከያ ሰራዊቱ ተይዘው አዲስ አበባ ሲገቡ የተሰማቸውን ስሜት ‹‹እነዚህ ሰዎች ከሰውነት ተራ ወጥተውና ተጎሳቁለው ሳያቸው እንደሰው በጣም አዝኛለሁ። ከዘመኑ የራቁና ትናንት ላይ የቆሙ ፤ ለነገ ግድ የሌላቸው ደንታቢሶች ናቸው። 80 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ቢያንስ ለሌላው ክብር ባኖራቸው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ክብር ይኖራቸዋል ብዬ አስብ ነበር። ሆኖም ግን መጨረሻቸው ከንቱ የሆነ ከንቱ ሰዎች ናቸው›› ሲሉ ገልጸውታል።
27 ዓመታት ህዝብና ሀገር ያስተዳድሩ የነበሩ ሰዎች እንደገና ጫካ ገብቼ ወደ ስልጣን እመጣለሁ ብለው ነፍጥ ማንሳታቸው ሰዎቹ ዛሬን ያልተረዱ የትናንት ሰዎች መሆናቸውን እንድረዳ አድርጎኛል ያሉት አቶ ማሙሸት፣ ሀገሪቱንም ሲመሩ የነበረው በትናንት አስተሳሰብ እንደነበርም ለማንም ግልጽ ሆኗል ብለዋል።
ሀገር የመሩ ሰዎች በመጨረሻው ሰአት ተዋርደውና ተጎሳቁለው መታየታቸው እንደሀገር የሚያሳፍርና በምን አይነት ሰዎች ስንተዳደር እንደቆየን ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ነው ያሉት አቶ ማሙሸት፣ ክስተቱ በመጨረሻም እነዚህ ሰዎች እንደገና አንሰራርተው ኢትዮጵያን ይገዛሉ ብለው የሚመኙ ደጋፊዎቻቸውን ቅስም የሰበረ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በነበረው የፍርድ ሂደት ከሳሽ እነሱ፤ መርማሪ እነሱ፤ ገራፊ እነሱ፤ ፈራጅ እነሱ የነበሩ ቢሆንም አሁን በሀገራችን ነጻ የፍትህ ሥርዓት በመኖሩ እነሱ ሲሰሩት ከነበረው በተቃራኒ ነጻ ፍትህ የሚያገኙ ዕድለኞች ናቸው ብለዋል።
የህውሓት ጁንታ እንደሰው በአካል ለፈጸሙት በደል ለህግ መቅረባቸው ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ነው ያሉት አቶ ማሙሸት፣ ለህግ የመቅረባቸው እውነታ ሰዎች ወንጀል ሰርተው ሊዘገይ ይችላል እንጂ ከህግ እንደማያመልጥ ተጨባጭ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል። በስልጣን ላይ ያለውም ይሁን ወደፊት የሚመጣውም አካል ወንጀል ሰርቶ ተደላድሎ መቆየት እንደማይቻል ያመላከተ እንደሆነም ጠቁመዋል።